ፈልግ

የኒካራጓ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት የኒካራጓ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የላቲን አሜሪካ አገር፣ ኒካራጓን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የፖለቲካ መረጋጋት የማይታይባት የኒካራጓን ሁኔታ በቅርብ በመከታተል በጸሎታቸውም እያስታወሷት ሲሆን፣ የሀገሪቱ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳትም የዳንኤል ኦርቴጋ መንግሥት ለውይይት እንዲቀርብ ጥሪ አቀረቡ።

ዮሐንስ መኰንን - ከቫቲካን

የኒካራጓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ በዋና ከተማ ማናጓ ከተሰበሰቡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገሪቱ ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ እንድትወጣ፣ ብጥብጥ እና አመጽ ቆሞ ዜጎችዋም ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ለማድረግ፣ መንግሥት ከተቃዋሚ ሰልፈኞች ጋር ሰላማዊ ውይይት እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለቱን ወገኖች ለውይይት በመጥራት የአደራዳሪነት ሚናን ለመቀጠል ሙሉ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች። የማናጓ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሌዮፖልዶ ብረንስ፣ በማናጓ የተደረገው የጳጳሳት ዝግ ስብሰባ ዓላማ፣ በብሔራዊ የሰላም ውይይት ሂደት ውስጥ ቤተ ክርስቲያናቸው ትሳተፍ ወይም አትሳተፍ የሚለውን አቋም ለመወሰን እንደሆነ ገልጸዋል። በመጨረሻም የብጹዓን ጳጳሳት አቋም፣ በፖለቲካ ቀውስ እየተጎዳች ያለች አገራቸው ወደ መግባባት እና ሰላም ጎዳና እንድትመለስ እርቅን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ፣ ይህን ለማድረግ ከውይይት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለ ጳጳሳቱ ተስማምተዋል ብለዋል። ስለዚህ በአገሪቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሚና የሚሆነው መንግሥትን እና ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለሰላማዊ ውይይት በመጥራት እና ማግባባት ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት የማይታይባት የኒካራጓን ሁኔታ በቅርብ በመከታተል ላይ እንዳሉ እና ሰላም እንዲወርድላት በጸሎታቸውም እያስታወሷት እንደሆነ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኒካራጓ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እንዲያበቃ በማለት፣ ያለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዚህ ማሳሰቢያቸው፣ ቅድስት መንበር ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያን እንደምትሰጥ፣ ይህንን ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች የሰዎችን ነጻነት እንዲያከብሩ፣ ከሁሉም በላይ ለሰው ልጅ ሕይወት ክብርን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

በላቲን አሜሪካ እና በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንና ባሁኑ ጊዜ ለኒካርጓ በመጸለይ ላይ እንዳሉ፣ ባለፈው እሁድም የመላው ላቲን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በጸሎት መተባበራቸው ታውቋል። የማናጓ ረዳት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሲልቪዮ ሆሴ ባየዝ፣ በቲዊተር ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፋቸው እንደገለጹት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተቸግሩት እና ከሚሰቃዩት ጋር እንደቆመ ሁሉ የኒካራጓ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንም ባሁኑ ጊዜ መከራ፣ ስደት፣ ግርፊያ እና እስራት ከሚደርስበት ከኒካራጓ ሕዝብ ጋር እንድምትቆም ተናግረዋል።     

ኒካራጓ ካለፈው መጋቢት ወር ወዲህ ባጋጠማት የፖለቲካ ቀውስ፣ ይህም በሰላማዊ ሰልፈኛ ተማሪዎች እና በጸጥታ አስከባሪዎች መካከል በተከሰተው ብጥብጥ እና አመጽ ምክንያት የ360 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ታውቋል። የሰላማዊ ሰልፉ ዋና ምክንያትም፣ በፕሬዚዳንት ኦርቴጋ እና በባለ ቤታቸው፣ በቀዳማዊት ሮዛሪዮ ሙሪሎ ላይ የተነሳው ተቃውሞ እንደሆነ ታውቋል። የሰልፈኞቹ ጥያቄም ፕሬዚዳቱ ይወስዳሉ ተብሎ የተጠበቁት የማህበራዊ ደህንነት ማሻሻያዎች ተግባራዊ አለመሆናቸው፣ በሙስና እና በስልጣን መባለግ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ፕሬዚዳንት ኦርቴጋ ከስልጣን ይውረዱ የሚሉ እንደሆነ ታውቋል።

የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች በወሰዱት ሃይል የታከለበት እርምጃ፣ በኒካራጓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ላይ፣ በቅድስት ሐዋርያዊት መንበር ተጠሪ እና እንደዚሁም በተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቋማት ሠራተኞች ላይ ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ብጹዕ ካርዲናል ሌዮፖልዶ ገልጸዋል።

25 July 2018, 09:32