ፈልግ

የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ  

የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ

የአንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር፣ የሕይወት አካሄዱን ከመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ጋር ያዛመደ መሆን ይኖርበታል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ከቫቲካን

የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ በሚል አርዕስት አንድ ጽሑፍ መዘጋጀቱ ተነገረ።

ክቡር አባ ሴርጆ ላ ፓኛ፣ “የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እይታ” በሚል አርዕስት አንድ ጽሑፍ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል። ክቡር አባ ሴርጆ በጽሑፋቸው፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ማንነት ሲገልጹ፣ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያሳድግ፣ የግል ድክመቶቹን ለይቶ የሚያውቅ፣ ለቃሉ ታማኝ የሆነ፣ ሌሎችን የሚያዳምጥ፣ ለሌሎች ቅድሚያን የሚሰጥ፣ ለማስተማር የተዘጋጀ፣ መልዕክቶችን የማስተላለፍ ችሎታ ያለው፣ ሃላፊነትን የመወጣት ብቃት ያለው እና ጥሩ የማስተዋል ችሎታ ያለው እንደሆነ አስረድተው ትክክለኛ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር እነዚህ አሥር መገለጫዎች ሊኖሩት ይገባል ብለዋል።

ደራሲው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አስተምህሮችን እና ጽሑፎችን መሠረት በማድረግ ባሳተሙት መጣጥፍ፣ መሠረታዊ የሆኑ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ማንነት እና ተልዕኮን ለማብራራት ሞክረዋል። ደራሲው በጽሑፋቸው አማካይነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለዚህ አገልግሎት ራሳቸውን ያቀረቡት ሰዎች እግዚአብሔረን እና ምዕመናንን ለማገልገል የገቡትን ጥሪ በመንከባከብ፣ የበለጠ ለማሳደግ የሚችሉበትን መንገድ በግልጽ ጠቁመዋል። ማንም በራሱ ብቻ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም የሚሉ የጽሑፉ ደራሲ ክቡር አባ ሴርጆ፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር፣ ወንጌልን በማወጅ አገልግሎት ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከትውልድ አገራቸው ከሆነው ከአርጀንቲና ጀምሮ እስከ ሮም ድረስ ባደረጉት የመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ጊዜ ሁሉ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚያበረክተው አገልግሎት አድናቆትን ሲቸሩ እና ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። የትምህርተ ክርስቶስ መምህር፣ ከክርስቶስ ጋር የሚገናኙበት ስፍራ እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአርጀንቲና የቅዱስ ፒዮ አስረኛ፣ የአምልኮ ዕለት በሚከበርበት ጊዜ አንድ ልዩ የደብዳቤ መልዕክት ለትምህርተ ክርስቶስ መምህራን በየዓመቱ እንደሚልኩ ገልጸዋል።

የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን አባቶች ማሕበር መሥራች የሆኑት፣ ብጹዕ ቼዛሬ ዴ ቡስ፣ ለማሕበርተኞቻቸው በጽሑፍ አዘጋጅተው ባስቀመጡት መመሪያ እንደገለጹት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምሕር ተጨማሪ አምስት መገለጫዎች እንዳሉት ጠቁመዋል። አንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ትጉህ የወንጌል አብሳሪ፣ ለሚያገለግሏቸው ምዕመናን እና ለእግዚአብሔር ታማኝ፣ ትሁት እና ለአድማጮቹ በግልጽ ቋንቋ የሚናገር፣ የወንጌልን የምስራች ለማወጅ የሚያስችሉ የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቀም መሆን አለበት ብለዋል። ክቡር አባ ሴርጆ በጽሑፋቸው እንደገለጹት የትምህርተ ክርስቶስ መምህር፣ ከማስተማር ሥራ ውጭ ቢሆንም በዘወትር ሕይወቱ ምስክርነትን የሚሰጥ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። አንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ሕይወቱን በሙሉ ለማስተማር አገልግሎት እንደተጠራ በማሰብ፣ ከሰዎች ጋር በሚኖረው ዕለታዊ ግንኙነት መልካምን መናገር እና መሥራት ሳያቋርጥ፣ ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል ብለዋል። ብጹዕ ቼዛሬ ዴ ቡስ እንደተናገሩት የትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት ሕይወት፣ እርሱ በሚያስተምረው እውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።

የአንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር፣ የሕይወት አካሄዱን ከመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ጋር ያዛመደ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት የግል መልዕክት ወይም የቤተ ክርስቲያን ትዕዛዝ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ ነውና። ስለዚህ አንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር መገንዘብ ያለበት፣ በማስተማር ሂደቱ የግል አገላለጾችን ከመጠቀም ይልቅ ቅዱስ ቃልም ሆነ የቤተ ክርስቲያን መመሪያዎች፣ እግዚአብሔር ራሱ በሚገልጸው እና በሚመራው መንገድ ተተርጉመው ወደ ምዕመናን ዘንድ መቅረብ ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙን ጊዜ እንደሚያስታውሱን፣ መጀመሪያዎቹን የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን የሆኑትን ወላጆችን ወይም የዕድሜ ባለጸጋዎችን መዘንጋት የለብንም። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚሉት፣ የዕድሜ ባለ ጸጋነት፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጸጋ እንደሆነ፣ እግዚአብሔርም ይህን ጸጋ የሚሰጠው በሕይወታችን ውስጥ በየዕለቱ በመታደስ፣ እምነታችንን ለሌሎች እንድናካፍል፣ ለሌሎች እንድንጸልይ፣ በተለይም የእኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት እንደተጠራን መገንዘብ ነው። ስለዚህ የዕድሜ ባለጸጋዎችም የክርስቶስን ትምህርት ለሌሎች እንዲያዳርሱ፣ የሕይወት ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ፣ የቤተ ሰብን፣ የሕብረተ ሰብን፣ የሕዝብን የኑሮ ሁኔታዎችን ከሌሎች ጋር እንዲወያዩ እና ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በትህትና እምነታቸውን ለመመስከር ተጠርተዋል።

ብጹዕ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ፣ የአባ ቼዛሬ ደ ቡስ ብጽዕናን ይፋ ባደረጉበት በ1967 ዓ. ም. እንዳስታወሱት፣ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን፣ የመጀመሪያ የወንጌል ልዑካን ናቸው ብለዋል። ከዚህም ጋር ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን ለወንጌል አገልግሎት በመስጠት፣ እምነታችንን ለመገንባት እና የወደፊት ተስፋችንን ለመደገፍ ይረዳሉ ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም፣ በ2005 ዓ. ም. ስለ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ በማስመልከት በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኙትን እንግዶች ለአገልግሎታቸው አመስግነው በተለይም የቤተ ክርስቲያን አባል በመሆናቸው እና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር አብረው ለመጓዛቸው በመነሳታቸው አመስግነዋቸዋል።

26 July 2018, 15:51