ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ  

የሚሲዮናዊነት ሥራ የእርዳታ ሥራ ሳይሆን የወንጌል ምስክርነት ነው ተባለ

በቦሊቭያ ለአምስተኛው ጊዜ በተካሄደው የአሜሪካ ሚሲዮናዊያን ጉባኤ ላይ ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ፣ ከሁሉም አስቀድሞ ሚሲዮናዊነት መባረክ እና በሌሎች ዘንድ ታማኝ መሆን እንደሆነ አስታውሰዋል።

የሚሲዮናዊነት ሥራ የእርዳታ ሥራ ሳይሆን የወንጌል ምስክርነት ነው ተባለ።

ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ የሚስዮናዊነት ሥራ፣ የእርዳታ ሥራ ሳይሆን የወንጌል ምስክርነት እንደሆነ አስታወቁ። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ ይህን ያስታወቁት፣ በቦሊቭያ ለአምስተኛው ጊዜ በተካሄደው የአሜሪካ ሚሲዮናዊያን ጉባኤ ላይ እንደሆነ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል እንደገለጹት፣ ከሁሉም አስቀድሞ ሚሲዮናዊነት መባረክ እና በሌሎች ዘንድ ታማኝ መሆን እንደሆነ አስታውሰዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን

ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ እንደገለጹት የሚስዮናዊነት ሥራ፣ የእርዳታ ሥራ ወይም ከራሳችን በጎ ሃሳብ የሚመነጭ ሳይሆን በወንጌል የምስራች መባረክ ነው ብለዋል። የደቡብ አሜሪካ አገር በሆነችው በቦሊቪያ፣ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን የሚሲዮናዊያን ጉባኤ ለተሳተፉት አባላት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ እንደገልጹት፣ የሚሲዮናዊያን ሥራ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ ከስሙም ጋር የማይለያይ ውሕደት ስላለው፣ ይህም ማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድሆችን በመምረጥ የሚደረግ በመሆኑ የወንጌል ስርጭት እና ምስክርነት ነው ብለዋል። ይህም ማለት በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ መባረክ ነው ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ የሚሲዮናዊነት መሠረታዊ ትርጉሙን ሲያስረዱ የመጀመሪያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሐጢአታችን መሞቱን፣ በዚህም የዘለዓለም ምሕረትን እንዳስገኘልን ለዓለም መመስከር ነው ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለደህንነታችን ምን እንዳደረገ በሚገባ ካልተረዳን እምነታችንም ከንቱ እና ከአንገት በላይ ይሆናል ብለዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ለሌሎች በምንመሰክርበት ጊዜ፣ ምስክርነታችን እውነተኛ እና በሌሎች ዘንድ እምነት ያለው መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ የዘመናችን እውነተኛ ሚሲዮናዊ ያሏት እና በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ቅዱስ አጽም በመንበረ ታቦት የተቀመጠላት የስፔን አገር ተወላጅ ብጽዕት ማርያ ኢኛሲያን ጠቅሰው፣ ይህች ብጽዕት ከትውልድ አገሯ ከስፔን፣ ለወንጌል መስክርነት ወደ ደቡብ አሜሪካ አገር ወደ ቦሊቪያ በመሄድ ድሆችን የረዳች፣ ስደተኞችንም ተቀብላ የተንከባከበች ትጉ ሚሲዮናዊ እንደሆነች አስታውሰዋል። ብጽዕት ማርያ ኢኛሲያን፣ ድሆችን እና ስደተኞችን ለመርዳት ባላት ፍቅር፣ ደሆችን የሚረዱ የሚሲዮናዊያን ደናግል ማሕበር መስራች እንደሆነች ገልጸው፣ በሚቀጥለው ዓመት፣ በጥር ወር፣ 2011 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የብጽዕት ማርያ ኢኛሲያን ለቅድስና መብቃት ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

በብሉይ ኪዳን የአብርሃምን ታሪክ በማስታወስ፣ እግዚአብሔር የጀመረው መልካም ነገር ተፈጻሚነትን እንዲያገኝ የሰዎች ተሳትፎ ያስፈልጋል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፊሎኒ፣ በእግዚአብሔር እቅድ ለመሳተፍ በቅድሚያ በእርሱ መባረክ ያስፈልጋል። አንድ ልጅ ከመሰናበቱ የወላጆቹን ቡርኬ እንደሚጠይቅ ሁሉ፣ እንደ ሚሲዮናዊነት ሥራ ጅማሬ የመሰለ አገልግሎት ከመጀመራችን በፊት የእግዚአብሔርን ቡራኬ መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

“አሜሪካ በሚሲዮን እና በወንጌል ደስታ” በሚል ርዕስ፣ በቦሊቪያ የተካሄደው አምስተኛው የሚሲዮናዊያን ጉባኤ 2.500 አባላት የተካፈሉበት ሲሆን በጉባኤው መካከል ሐዋርያዊ ምስክርነት የሚሰማበት፣ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት፣ በቡድን፣ በቡድን ሆነው ውይይቶች የሚካሄዱበት እና የጋር ጸሎት የሚደረግበት እንደሆነ ታውቋል። በቦሊቪያ የሳንታ ክሩዝ ደ ላ ሴራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ሴርጆ ጓልበርቲ፣ ከቫቲካን የዜና ማሰራጫ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የጉባኤው ዓላማ ሚሲዮናዊነትን ማስፋፋት፣ ከወንጌል የሚገኝ ደስታን  ወደ መላው ዓለም ማዳረስ፣ በተለይም ልዩ ጥንቃቄ ለሚያሻው ለዛሬው ዓለም ወንጌልን መመስከር ነው ብለዋል።

ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደው የሚሲዮናዊያን ጉባኤ የሚጠናቀቀው መጭው ቅዳሜ ቀን ተከብሮ በሚውለው የተልዕኮ ቀን ሲሆን በዕለቱም የማሳረጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚደረግ ታውቋል።

የአሜሪካ ሚሲዮናዊያን ጉባኤ የተጀመረው በብሔራዊ ደረጃ በሜክስኮ፣ በ1989 ዓ. ም. ሲሆን  የሚካሄድባቸው አገሮችም ወደ ሌሎች የላቲን አሜሪካ በምስፋት፣ ቀጥሎም በመካከለኛው የላቲን አሜሪካ አገር በጓተማላ፣ በ1995 ዓ. ም. ተካሂዶ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በየ 5 ዓመቱ በተለያዩ የላቲን አሜሪካ አገሮች እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።

 

11 July 2018, 13:43