ፈልግ

የአስመራ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም የአስመራ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም  

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያምን የሰላሙ ጥረት አስደስቷቸዋል

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም ለቫቲካን የዜና ማሰራጫ እንደገለጹት፣ የለውጥ አራማጅ የሆኑት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ በሁለቱ አገሮች በመካከል ለሃያ አመታት ያህል ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት አስተካክለው ሰላምንና ፍቅርን ለመዝራት መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የአስመራ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ በአስመራ ያደረጉት ግንኙነት እንዳስደሰታቸው ገለጹ።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም ለቫቲካን የዜና ማሰራጫ እንደገለጹት፣ የለውጥ አራማጅ የሆኑት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ በሁለቱ አገሮች በመካከል ለሃያ አመታት ያህል ተቋርጦ የቆየውን ግንኙነት አስተካክለው ሰላምንና ፍቅርን ለመዝራት መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በቁጥር እጅግ በርካታ የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች በደስታ እንደተቀበሏቸው ተናግረዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ጋር በአቀባበሉ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጓዙበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን፣ ከሃያ አመታት በኋላ በአስመራ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ አርፏል ብለዋል። ሁለቱ መሪዎች በፍቅር ሲተቃቀፉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም በማከልም፣ ከአስመራ እና ከአስመራ ውጭ ለሚኖሩት ነዋሪዎች ዕለቱ የደስታ እና የፈንጠዚያ ዕለት በመሆኑ ተዓምር የታየውን ያህል ይቆጠራል በማለት ለቫቲካን የዜና ማሰራጫ ገልጸዋል።

በ1992 ዓ. ም. በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተደረገው አሰቃቂ ጦርነት ከ70,000 እስከ 100,000 ያህል ሰው እንደሞተ ሲነገር፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ አቶ መለስ ዜናዊ እና የኤርትራው ፕሬዚደንት አቶ ኢሳይያስ አፈ ወርቂ፣ አስከፊውን ጦርነት ለማብቃት፣ በአልጀሪያ መዲና አልጀርስ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። ቢሆንም በጦርነቱ የበላይነትን የተቀዳጀች ኢትዮጵያ፣ በ1994 ዓ. ም. በተባበሩት መንግሥታት የተሰየመው ዓለም አቀፍ ኮሚሺን፣ አከራካሪው የባድሜ መሬት ለኤርትራ ይገባል ብሎ ቢወስንም ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከሥፍራው ሳታስነሳ በመቆየቷ ምክንያት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ተቋርጦ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ በ1992 ዓ. ም. በአልጀርስ የፈረመችውን ስምምነት ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደምትቀበለው፣ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ. ም. በድንገት ስታሳውቅ፣ ኤርትራም ተመሳሳይ አቋም እንድትውስድ መጠየቋ ይታወሳል። ይህን ከመጠየቋ ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በሃገራቸው የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ ለማቀዝቀዝ ተብሎ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አውጅ ማንሳታቸውም ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጦችን ለማምጣት ተስፋን የሰጡት በግንቦት ወር ስልጣን በተረከቡበት ወቅት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥረትም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኝነቶችን በማጠናከር፣ የባሕር ወደብ አልባ የሆነች ኢትዮጵያ፣ የኤርትራን የቀይ ባሕር ወደቦች መጠቀም የምትችልበትን መንገድ ማመቻቸት፣ በድንበሯ ያሰፈረቻቸው ሠራዊቶቿን መመለስ እና ሌሎች ቀጣይ ስምምነቶችን ለማጽደቅ እንደምትሻ፣ ንግሪዚያ የተሰኘ፣ የቅዱስ ኮምቦኒ ማሕበር ካቶሊካዊ መጽሔት ዳይረክተር የሆኑት ክቡር አባ ኤፍሬም ትረ ሶልዲ አስረድተዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት አለመቀበሏ ስጋት ላይ በመጣላቸ፣ ከአመታት በፊት ያወጁትን  ገደብ የለሽ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አዋጅ እንደሚያነሱት ያላቸውን እምነት፣ ክቡር አባ ኤፍሬም ትረ ሶልዲ ገልጸዋል። በኤርትራ የታወጀው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በርካታ ወጣቶች አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ክቡር አባ ኤፍሬም አክለው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ፣ ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣  ሁለቱ አገሮች ማለትም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ውይይት ለመጀመር የወሰዱት እርምጃ መልካም ዜና መሆኑን ተናግረው ይህም በሁለቱ አገሮች መካከል እንዲሁም በመላው የአፍሪቃ አህጉር የተስፋ ብርሃን እንዲፈነጥቅ አድርጓል  ብለዋል። የአስመራ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሁለቱን አገሮች በጸሎታቸው ስለ ማስታወሳቸው አመስግነው፣ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ መንግስተ አብ ተስፋ ማርያም በማከልም በኤርትራ እስከ ነሐሴ አጋማሽ የሚቆይ የአንድ ወር የጸሎት ዕቅድ መያዙን ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት በእርግጥም በሁለቱ አገሮች መካከል የሰላም ምልክት መታየቱን ገልጸው፣ ይህ ሰላም በሁለቱ አገሮች መካከል ብቻ ሳይሆን በአፍሪቃ ቀንድና በመላው አፍሪቃ ዘላቂና ፍሬያማ እንዲሆን ተመኝተዋል።

10 July 2018, 16:30