ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ከቫቲካን ተወካይ ጋር ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ከቫቲካን ተወካይ ጋር 

19ኛ የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ

19ኛ የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ጉባኤ ሐምሌ 6 – 162010 መክፈቻ ንግግር፣ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ

19ኛ የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ጉባኤ

ሐምሌ 6 – 162010

መክፈቻ ንግግር፣ ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ

‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፣ እነሆም ያማረ ነው!›› (መዝ 133፣ 1)

ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪቃ አባል አገራት በዚህ የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉበኤ ላይ በመሳተፍ ከኛ ጋር የወንጌል ደስታ ለመካፈል ወደዚህች የሰው ልጅ መገኛ አገር የመጣችሁ ሁላችሁንም ከልብ በሆነ በደስታ እንኳን ደህና መጣችሁ እላችኋለሁ፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ አገረ ስብከቶችና የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጣችሁ ካቶሊክ ምዕመንና ወዳጆች ሁሉ እንኳን በሰላም መጣችሁ፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ገዳማውያን፣ ምዕመናን እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሳያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ መላ ኢትዮጵያውያን፤ የአመሰያ ጉባኤ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ስለሆናችሁና ለዚህም ደግሞ እጅግ የሚያስደንቅ ዝግጅት ስላደረጋችሁ አመሰግናችኋለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች ለዚህ ጉባኤ ዝግጅት አድርገዋል፤ እኛም ወንድሞችና እህቶች አንድ ላይ ሆነው ሲሰሩ  እንዲህ አይነት ውብ ዝግጅት ማሰናዳት እንደሚችሉ አይተናል፡፡  ይህ ቀን ያማረ እንዲሆን ቀንና ማታ ለለፋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ፡፡

እንደምታወቀው የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በቁጥር አናሳ ናት፣ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች አንድ ከመቶ ቢሆኑ ነው፡፡ ይሁን አንጂ ቤተክርስቲናችን  ለብዙ ዘመናት ክርስቲያናዊ ወግ፣ ልማድ፣ መንፈሳዊነትና ባህል ጠብቃ ካቆየች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስተያን ጋር ብዙና ጥልቅ እሴቶን በመጋራት ትኖራለች፡፡ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እነዚህን ክርስቲናዊ ባህሎች ትጋራቸዋለች፡፡ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የገባው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደምናነበው በሐዋርያት ዘመን ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ክርስትናን በይፋ የተቀበለችው በ325 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡  ኢትዮጵያዊ ማንነት ያለው ጥልቅ ክርስቲያናዊ እምነት የክርስቲያን እምነት ባጠቃላይ ውብና ሕያው ሆኖ እንዲቆይ ረድቶአል፡፡ ዛሬ እንደምናየውም በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ በበጎ መልኩ ተጽዕኖ ማሳደር ችሎአል፡፡

በኢትዮጵያ ለምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና ባጠቃላይ ለሕብረተሰባችን ይህ ዝግጅት የጸጋና የበረከት ጊዜ ሆኖናል፡፡ የተለያዩ ዎርክሾፖችና ስብሰባዎችን በማዘጋጀት፣ በቀጠናችን ሰላም፣ አንድነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ይቅርታ   እንዲሰፍን የጸሎት ጊዜያትን በማሰናዳት ቤተክርስቲያን እነሆ በጸጋ የተሞሉ አራት ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ ልዩነትን በአግባቡ ማስተናገድ ባለመቻላችን ለመጣብን የመናወጥ ጊዜም ለአገራችን ጸሎት አድርገናል፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙባት አገር ናት፡፡  ብዝሃነትን ማድነቅና ውበት እንደሆነ መገንዘብ በፍጥረት ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን  እቅድ ማክበር ነው፡፡ ተፈጥሮ ብዙና የተያየ ነው፡፡ ሁሉንም በተለየየ  መንገድ ልዩ አድርጎ የፈጠረ የእግዚብሔር ጥበብ ምንኛ ጥልቅ ነው!

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እራሷ የብዝሃነት ተምሳሌት ናት፡፡ እዚህ ባለንበት ቦታ ሳይቀር ስንት ባህሎችና ቋንቋዎች አሉ! እንዴት እንደምናምር ተመልከቱ!  እግዚአብሔር ታላቅ ነው፡፡  የእኛ ኃላፊነት ይህን የእግዚብሔር ጥበብ መገለጫ መጠበቅ፣ ብዝሃነትን ማክበርና ማሳደግ ነው፡፡ የካቶሊክ ቤተክስርቲያን ሰብዓዊነትን ታገለግላች፣ ምክንያቱም ይህ ለእርሷ የተሰጠ መለኮታዊ ተልዕኮ  ነውና፡፡  እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ነው፣ ሕያው ለሆኑ ፍጥረታቱ ሁሉ የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣቸዋል፡፡ የካቶሊክ ተቋማት  የውብና ሕያው ብዝሃነት፣ በየነ-ባህላት  እና ማኅበራዊ ውይይት እንዲሁም የሰላማዊ አንድነት እና አብሮ መኖር ማዕከላት ናቸው፡፡

የዚህ ዓመት የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (አመሰያ) ጉባኤ መሪ-ቃል  ‹‹በእግዚአብሔር የተመሠረተ ሕያው ብዝሃነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት በአመሰያ አገራት›› ይላል፡፡ ይህ መሪ-ቃል በምስራቅ አፍሪቃ በዘር ልዩነቶችና በሌሎችም ምክንያቶች በግጭት ውስጥ ያሉ ብዙ ዜጎችን ለቅሶ ያስተጋባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ዓይነት ሁከትና ጠቦችን እያየን እንገኛለን፣ ስለሆነም ቤተክርስቲያን በጠብ ምክንያት የተፈጠሩትን ቁስሎች የመፈወስና የነቢይነት ሚናዋን የመጫወት ተልዕኮ አለባት፡፡  በዚህ ቀጠና ቤተክርስቲያን በሰላም ግንባታ፣ በፍትህና እርቅ ውስጥ ያላት ሚና እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

‹‹የዚህ ዘመን ሰዎች፣ በተለይም የድሆች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘንና መከራ የክርስቶስ ተከታዮች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘንና መከራም ናቸው፡፡  በእውነት ሰብዓዊ የሆነ ማንኛውም ድርጊት በልባቸው (በድሆች) ውስጥ ቦታ ሳያገኝ አያልፍም (Vatican II Guadium et Spes No. 1)፡፡

ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬኒያና ሌሎች በምስራቅ አፍሪቃ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ አገራት በተለያዩ ዘርና ነገዶች መካከል  በሚከሰት  ግጭት ምክንያት ይሰቃያሉ፡፡ ይህ  በዚህ ቀጠናችን የሚታይ ችግር ያሳስበናል፡፡ ብዙ ሥልጣኔዎች፣ የሰው ልጅ አዕሞሮአዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገቶች  በሚታዩባት ዓለም ውስጥ እንዲህ አይነት አስከፊ ሁኔታ ማየት እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ እንደ አንድ የሕያው ብዝሃነት፣ የሰብዓዊ ክብርና ሰላመዊ አንድነት የምታስፋፋ አካል ቤተክርስቲን በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእኔ ሥራ ምን ይሆን ብላ ራሷን እየጠየቀች ነው፡፡ 

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን  ኢትዮጵያን ጨምሮ በቅርብ ጊዜያት ግጭቶች በታዩባቸው አገራት ሰላም ማውረድ እንደሚቻል ታምናለች፡፡ በፖለቲካ መሪዎችና በመላው ሕብረተሰብ ዘንድ እውነተኛና ከልብ የመነጨ ውይይት ከእልህና ትምክህት አመለካከት ነጻ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ ቤተክርስቲያን ትማጸናለች፡፡  ልብን የሚያሸንፉ ፍቅር፣ ትህትናና ይቅርታ ብቻ ናቸው፡፡ ይህ  እንደሚቻል በፍጹም እናምናለን፡፡

የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እና ሌሎች ባለድርሻዎች በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲፈጠር  ሁለቱ ባለጋራዎችን አንድ ላይ ለማምጣት ያደረጉትን ጥረት እናደንቃለን፡፡ ፍትህ፣ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ሰላምና አንድነት የሁሉም ግጭቶች መፍትሔዎች መሆናቸውን ደግመን ደጋግመን  እናሳስባለን፡፡ የደቡብ ሱዳን ወንድሞችና እህቶቻችን እጅግ በጣም ተሰቃይተዋል፣ ጩኸታቸውም ወደ ሰማይ ይደርሳል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐቢይ አህመድና በመንግስታቸው ጥበብ የተሞላ አመራር የኢትዮጵያ ህዝብ እያየ ያለውን እናደንቃለን፡፡  ሁሉም ባለድርሻቸው ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታ፣ አንድነት፣ እኩልነትና ሰብዓዊ ክብርን እንዲያጎለብቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡  የሰው ልጅ ለቅሶ በሚሰማበት ቦታ ሁሉ ዘወትር መፍትሔ አለ፡፡ በትህትና እና በይቅርታ ልብ ተሞልተን ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበትና ድምጽ የሌላቸው ድምጻቸው የሚሰማበት ዲሞክራሲያዊ እሴቶች እንዲጠነክሩ መስራት አለብን፡፡  የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በዚህ የእውነተኛ ውይይት ሂደት ውስጥ ከታችኛው እርከን አንስታ በብርቱ ትሳተፋለች፡፡

ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን ‹‹ሠላም አልባና ጦርነት አልባ›› ሁኔታ እንዲያበቃ የተወሰዱ አዲስ የሰላምና የውይይት እርምጃዎችን በታላቅ ደስታ ተቀብለናል፡፡  ብዙዎች ውድ ህይወታቸውን አጥተውበታል፣ ብዙዎች ቀዬዎቻቸውን ለቀው ተሰደዋል፣ ብዙዎችም በተስፋ አስቆራጭና አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ነው፡፡  በሁለቱ አገራት ውስጥ የምትገኝ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሁልት ወንድማማቾች መካከል የተደረገውን ይህን ጦርነት ድምጹአን ከፍ አድርጋ ስታወግዝ፣ በአንድነት ስትጸልይና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ባሰየችው ጠንካራ አቋምና ለሁለቱም አገራት ህዝቦች ባሳየችው ወንድማማችነት ለህዝቡ ተስፋ ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በህዳር ወር 2017 ዓ.ም  ኤርትራን የጎበኘውን የአመሠያ የወንድማማችነት ልዑክ እናመሠግናለን፡፡

የዚህ የእርቅ ሂደት በሚካሄድበት ጊዜ ሁሉም ባለድርሻዎች ሰላምና ፍትህ እንዲመለስ ሁለቱም ህዝቦች በሂደቱ ውስጥ መካተታቸውና ድምጻቸው መሰማቱን እንዲያረጋግጡ እናሳስባለን፡፡

በኤርትራና ኢትዮጵያ የተወሰደው እርምጃ አፍሪቃውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት ጥበብ እንዳላቸው ማሳያ ነው፤  አፍሪቃውያን መፍትሔ በእጃቸው መዳፍ እንዳለ እያሳዩ ነው፡፡ የአመሰያ አገራትም ከዚህ የሰላም ሂደት መውሰድ የሚችሉ ትምህርት እንዳለ አምናለሁ፡፡

ይህ ጉባኤ የካቶሊክ ምዕመናን እንዴት ክርስቲያናዊ ህይወታቸውን ከወንጌል እሴቶች ጋር በሚገባ አስተሳስረው መኖርና የሰላም መሣርያ መሆን  እንደሚችሉ የሚያሳዩ የረዥም ጊዘ እቅዶችን  ይዞ ይመጣል፡፡ እቅዶቹ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ሆና  በሁሉም የቀጠናው ቦታዎች እንደሚገኝ  አንድ ተቋም በአፍሪቃ ቀንድና ምስራቅ አፍሪቃ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላምና  ስምምነት እንዲፈጠር ጉልህ ሚና እንዴት መጫወት እንደምትች አቅጣጫ ይጦቁማሉ፡፡

ቀጠናችን  ‹‹ሕያው ብዝሃነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ሰላማዊ አንድነት›› በሙላት የሰፈነበት ይሆን ዘንድ ቤተክርስቲያናችን  ከሁሉም ክልላዊ፣ አገር-በቀል፣ መንግሥታዊና መንግስታዊ-ያልሆኑ  ተቋማትና   የሲቪል ባለሥልጣናት  በጋራ ለመስራት ዝግጁ ናት፡፡

ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጋር ያላችሁን ወንድማማችነት ለማሳየት ዛሬ እዚህ የተገኛችሁትን በሙሉ አመሠግናችኋለሁ፡፡  ሁላችሁንም አመሠግናችኋለሁ፣ ለሁላችሁና ለወዳጆቻችሁ በሙሉ የአባታዊ ቡራኬዬ ይድረሳችሁ!

የምስራቅ አፍሪቃ ቀጠናም የሰላም፣ የፍትሕና የእርቅ ገነት ትሁን! 

የአፍሪቃ አመቤት፣ የሰላም ንግሥት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ለምኝልን፡፡ አሜን!

 

 

 

 

 

Photogallery

19ኛ የምስራቅ አፍሪቃ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ጉባኤ
15 July 2018, 09:21