ፈልግ

የሰኔ 17/2010 ዓ.ም ዘኣስተምህሮ 1ኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ክርማቸው ተስፋዬ የሰኔ 17/2010 ዓ.ም ዘኣስተምህሮ 1ኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ክርማቸው ተስፋዬ 

የሰኔ 17/2010 ዓ.ም ዘኣስተምህሮ 1ኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

ወንድሞችን ሆነ እህቶችን ለመርዳት ሁል ጊዜ በመልካምነትና በመልካም ፈቃድ የተደረገ ምፅዋት በእግዚኣብሔር ዘንድ ትልቅ በረከት እንደሚያስገኝ ይናገራል፣

የሰኔ 17/2010 ዓ.ም ዘኣስተምህሮ 1ኛ ሰንበትን ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ በክቡር አባ ክርማቸው ተስፋዬ

 

2ኛ ቆሮ 9፡ 1-15, 1ኛ ጴጥ 2፡1-12

ሓዋ ሥ 4፡31-37, ማር 2፡14-28

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር  ዘኣስተምህሮ 1ኛ ሰንበትን እናከብራለን። በዚህም ዕለት የእግዚኣብሔር ቃል በተለያዩ ንባባት ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን ይመጣል በቃሉም ያስተምረናል በቃሉ ያበረታናል። የእግዚኣብሔር ቃል ኃይል ኣለው እግዚኣብሔር ዓለምን በቃሉ እንደፈጠረ ይኸው ቃል ዛሬ ለእያንዳዳችን ብርታትና ኃይል ያላብሰናል የሕይወታችን ኣቅጣጫ ምን መሆንና ምን መምሰል እንዳለበት ያመላክተናል። በዚሁም መሠረት እንግዲህ በመጀመሪያው መልዕክት ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንጦስ ሰዎች በጻፈው በሁለተኛ መልዕክቱ ምዕራፍ 9 ላይ በመልካም ፈቃድና ፍላጎት እንዲሁም በደስታ ለእግዚኣብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ትልቅ በረከትን ያስገኛል ይለናል። እንዲሁ ደግሞ ወንድሞችን ሆነ እህቶችን ለመርዳት ሁል ጊዜ በመልካምነትና በመልካም ፈቃድ የተደረገ ምፅዋት በእግዚኣብሔር ዘንድ ትልቅ በረከት እንደሚያስገኝ ይናገራል፣ በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር 8-9 እንዲህ ይላል በተነ ለምስኪኖች ሰጠ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል ተብሎ እንደተጻፈ እግዚኣብሔር ሁል ጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ ኣግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል ይለናል። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ ዛሬ በእነዚህ በቆሮንጦስ ሰዎች በኩል ኣድርጎ ለእያንዳዳችን መልዕክቱን ሲያስተላልፍ ይህንንም ሓሳብ ያሰምርበታል፣ በመልካም ፈቃድ ለምንሰጠው ልገሳ በሙሉ እግዚኣብሔር የሰጠነውንም በእጃችን የሚቀረውንም ይባርካል ሥማችንንም በሕይወት መዝገብ ላይ ያሰፍራል። እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር በመጀመሪያ ወደ እዚህ ምድር ስንመጣ ምንም ነገር ይዘን ኣልመጣንም በኋላ ግን በእጃችን ያለ ሁሉ በእግዚኣብሔር መልካም ፈቃድ ያገኘነው ነው፣ በኋላም ወደ እግዚኣብሔር ስንመለስ ይዘነው የምንሄደው ኣንዳችም ነገር የለም ስለዚህ በእጃችን ያለ ነገር ሁሉ በዚህ ምርድ ላይ ስንኖር የምንጠቀምበት ነው፣ ያ ደግሞ ለእኛ ለግላችን ብጫ ሳይሆን ለወንድሞቻችንና እህቶቻችን ካለን ነገር ላይ እንድናካፈል የእምነታችን መመሪያ ያሳስባል። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል 10፡42 ላይ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለኣንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዘሙሩ ሥም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለው ዋጋው እይጠፋበትም ይለናል። እንግዲህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንደሚለን በእርሱ ሥም ላደረግናት ትንሽ ነገር ሁሉ በረከት ይኖረናል ለእኛም የቀረው ይባረካል በማቴዎስ ወንጌል 25፡40 ላይ እንደተፃፈው ደግሞ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞች ለኣንዱ እንኳን ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል በሚለው ቃል መሠረት እናም የዚህ ቃል ታዳሚዎች ነንና ወደ ዘለዓለማዊ ደስታ ይመራናል። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ላይ እንደተገለፀ የሰው ልጅ በቅዱሳን መላእክቱ ታጅቦ በክብር በሚመጣበት ጊዜ የሚጠይቀን ጥያቄ  ኣንድና ኣንድ ነው ይኸውም ተርቤ ኣብልታችሁኛልን?ተጠምቼስ ኣጠጥታችሁኛልን?እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልን?ታርዤ ኣልብሳችሁኛልን?ታመሜ ጠይቃችሁኛልን?ታስሬስ ወደእኔ ምጥታችኋልን?ነው እንግዲህ መልሳችንን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርብናል። መልሳችን ኣዎ ከሆነ እናንተ ያባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ ይለናል። ይህ ሆኖ በማይገኘበት ቦታ ደግሞ እናንተ እርጉማን ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘለዓለም እሳት ከእኔ ወዲያ ሂዱ ይለናል። ለእነዚህ ሁሉ ማለትም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለሚጠይቀን ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምንጀምረው ከኣሁን ጀምሮ ነውና መልሳችንን በጊዜ በሚገባ መልኩ እንስጥ። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እግዚኣብሔር ለሌላ የምንሰጠውንም ሆነ ለራሳችን የምንጠቀመውን የሚሰጥ እርሱ ነውና ከሰጠን ላይ ለሌላ ለማካፈል ኣንሰስት ምክንያቱም ያለንን ለሌላ ባካፈልን ቁጥር የእግዚኣብሔር ቡራኬ ስለሚያርፍበት ከማነስ ይልቅ እጅግ ይበዛል። በዮሓንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ላይ ያለውን የኣምስቱን እንጀራና የሁለቱ ዓሣን ታሪክ እናስታውስ 5 ሺህ ሕዝብ ያዉም ሴቶችና ሕፃናት ሳይቆጠሩ ጠግበው 12 መሶብ ሙሉ ተፎኣቸው ተነስቷል። የእግዚኣብሔር ቡራኬ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁሉ ነገር በእጥፍ ይበዛል። የእግዚኣብሔር ቡራኬ ባለበት ቦታ ሁሉ ሁሉ የሚያንስ ነገር የለም ከመብቃትም ኣልፎ ይትረፈረፋል። በሁለተኛው መልዕክት ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያ መልዕክቱ እግዚኣብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆነ እንግዲህ ክፋትንም ሁሉ ተንኮልንም ሁሉ ግብዝነትንም ሁሉ ቅንዓትንም ሁሉ ሓሜትንም ሁሉ ኣስወግዱ ይለናል። በእርሱ የማያምን ሁሉ እላይ የተዘረዘሩትን ነግሮች ሁሉ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ኣይችልም፣ ምክንያቱም እነዚህን የሥጋ ፍሬዎች  ከሥጋ ምኞቶች የሚመነጩ ኃጢኣቶች ለማስወገድ የግድ መንፈሳዊ በረከት ያስፈልጋል ይህ ደግሞ የሚገኘው የማዕዘን ራስ ከሆነው ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ከምንቀበለው ጸጋ፣ የሚጠነክረውና የሚያድገው ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ከምንቀበለው በረከት ብቻ ነው። በዚህ መልኩ ስንኖር ብቻ ነው ሥጋንና  የሥጋን ምኞቶች ሁሉ ኣሽቀንጥረን መጣል የምንችለው፣ በዚህ መልኩ ስንኖር ብቻ ነው ሥጋንና  የሥጋን ምኞቶች ሁሉ በሙሉ ኃይል መዋጋትና ማሸነፍ የምንችለው። በዛሬው በማቴዎስ ወንጌል 14፡2 ላይ ያለው ስለ ሌዊ ወይንም ወንጌላዊው ማቴዎስ መጠራት ይናገራል። ሁላችንም እንደምናውቀው ማቴዎስ ቀራጭ ነበር ስለዚህ ሃብት ነበረው ገንዘብ ነበረው ነገር ግን የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጥሪ ወደ እሱ በመጣ ጊዜ ሁሉን ትቶ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተከተለው። በቤቱም ከእየሱስና ከደቀመዛምርቱ ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ ከእርሱ ጋር ብዙ ቀራጮችና ኃጢኣተኞች ነበሩ ይህንንም ተመልክተው ጻፎችና ፈሪሳውያን ከቀራጮችና ከኃጢያተኞች ጋር ይበላል ብለው ወነጀሉት፣ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን ሕመምተኞች እንጂ ብርቱዎች ባለ መድኃኒት ኣያስፈልጋቸውም፣ ኃጢያተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ ኣልመጣሁም ኣላቸው። እውነት ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣው በሉቃስ ወንጌል 4፡17-19 ላይ በግልፅ እንደተፃፈው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሰሩት መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን የተጠቁትን ነጻ ኣወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል እንዳለው ወደ እዚህ ምድር ኣመጣጡ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ነው። ምን ኣልባት በተለያየ ዓለማዊና ክፉ ሓሳብ ታስረን ከነበረ ከዚህ ጭቆናና እስራት ነፃ ሊያወጣን፣ ልክ እንደ ፈሪሳዉያኑ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የኣብ ኣንድያ ልጅ መሆኑን በቃልና በሥራ እያስመሰከረ በዓይናቸው ተመልክተው ይህንን እውነታ ላለመቀበል መንፈሳዊ ዓይናቸው እንደታወረ የእኛም በተለያዩ ምክንያቶች መንፈሳዊ ዓይናችን ታዉሮ ከሆነ ዳግመኛ ብርሃንን ሊሰጠን፣ በተለያየ የሰይጣን ወጥመድ የተጠቃነውን  እውነተኛና ዘላቂ ነፃነት ሊያጎናፅፈን ነው ሰማያዊ ክብሩን ትቶ በመሓከላችን የተገኘው። እኛም ልክ እንደ ሌዊ ወይንም ወንጌላዊው ማቴዎስ መንፈሳዊ ዓይኑ በርቶለት ያለምንም ማቅማማት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እንደተከተለው ያለምንም ማወላዳት በቃልና በተግባር ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ልንከተለው ይገባል። ምናልባትም ወንጌላዊው ማቴዎስ በቤቱ የነበሩት ቀራጮችና ኃጢኣተኞች ልክ እንደ እሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሙሉ ልብ እንዲቀበሉና እንዲለወጡ ኣስቦ የጋበዛቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እኛም የእርሱን ኣብነት በመከተል የእኛ መለወጥ የኣሕዛብ መለወጥ እንዲሆን ከልባችን መሥራት ይጠበቅብናል፣ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደኅንነት በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መጋበዝ ይጠበቅብናል። በመቀጠልም የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለምን ልክ እንደ መጥምቁ ዮሓንስ ደቀመዛሙርት ኣይጾሙም በማለትና በእርሻ መካከል ሲያልፉ እሸት እየቀጠፉ በመብላታቸው ሰንበትን እንዳፈረሱ ተቆጥሮ እንድተከሰሱ ሰምተናል።  ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ለዚህ የሰጣቸው መልስ በመጀሪያ ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ስላለ ሊጾሙ ኣይገባም ነው። ለሁለተኛው ክስም የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው የሚል ነበር። እነዚህ የሙሴ ሕግ መምሕራንና ፈሪሳዉያን ውስጣቸው ንጹህ ስላልሆነ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ቢያውቁም ሊቀበሉት ኣልፈለጉም፣ በተቻላቸው ኣቅምና ኣጋጣሚ ሁሉ እርሱን መወንጀልና እርሱ የሚጠፋበትን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው ይሚፈልጉት፣ ምክንያቱም እርሱን በተመለከቱ ቁጥር በውስጣቸው ያለውን ክፋት፣ ለታይታ የሚያደጓቸውን ነግሮች፣ ስህተታቸውንና ማንነታቸውን ልክ እንደ መስታወት ግልፅ ኣድርጎ ስለሚያሳያቸው፣ ሊያዩትም ሆነ ሊቀበሉት በፍጹም ኣይፈልጉም ነበር። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ግን የመጣው ከዚህ ሁኔታቸው ሊያላቅቃቸው ነው እነሱ ግን መታመማቸውን ኣላወቁም መታወራቸውን ኣላውቁም በኣጉል ሕግ መታሰራቸውንም ኣላወቁም ወደ ህክምናም ኣይሄዱም ስለዚህ ምርጫቸው በጨለማ ውስጥ መኖር ነውና በጨለማ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ። ይህም የሚሰጠን ትምህርት ምንድን ነው ዛሬ እኛም ብንሆን በኣኗኗራችን ከፈጣሪና በዙሪያችን ካሉ እህት ወንድሞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ግንኙነታችን የተስተካከለ ካልሆነ ዓይናችንን ከፍተን በማየትና በመመርመር ታመንም ከሆነ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የመጣሁት በሽተኞችን ፍለጋ ነው ብሏልና መታመማችንን ኣውቀን ወደ እርሱ እንሂድ፣ ይህንንም በማድረጋችን ከህማማችን እንፈወሳለን ከእስራታችንም እንፈታለን። በዚህ መልኩ ዘወትር ጤነኞች ሆነን በፍቅርና በደስታ የተሞላ ሕይወት መኖር እንችላለን። በዚህም ወዳሰብንበት ቦታ እንደርስ ዘንድ የዘወትር ኣጋዣችንና ረዳታችን እንዲሁም በእግዚኣብሔር ፊት ጠበቃችን የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ጸጋና በረከትን ታሰጠን የሰማነውን ቃል ሁሉ በተግባር ለማዋል እንድንችል ልባችንን ከልቧ ጋር ታመሳስልልን። 

24 June 2018, 15:34