ፈልግ

የሰኔ 3/2010 ዓ.ም ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማ የሰኔ 3/2010 ዓ.ም ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማ 

የሰኔ 3/2010 ዓ.ም ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማ

ጸጋም ስጦታም ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን ኣንድ ነው፣

የሰኔ 3/2010 ዓ.ም ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ ሰንበት ቃል እግዚኣብሔር በክቡር አባ ግርማቸው ተስፋዬ

የእለቱ ምንባባት

  1. 1ቆሮ 12፡1-11
  2. 1ኛ ዮሓ 2፡20-29
  3. ሓዋ ሥ 2፡14-21
  4.  ዮ ሓ14፡22-31

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ከጰራቅሊጦስ በኋላ ያለውን ሁለተኛ ሰንበት እናከብራለን። በዚህም ዕለት ቅድስት ቤተክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የእየሱስ ክርስቶስን ቃል ለዕለቱ ባዘጋጀችው ንባባት ኣማካኝነት ወደ እያንዳዳችን እንዲደርስ ታደርጋለች። በይበልጥ ደግሞ ይህንን የምንሰማውን ቃል ወደ ተግባር በመለወጥ ለእኛም ሆነ ለሌሎች የደኅንነታችን ምንጭ እንዲሆን ያበረታታናለች። በዚሁም መሠረት እንግዲህ ዛሬ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንጦስ ምዕራፍ 12 ላይ ስለ መንፈሳዊ ነገርና ከእግዚኣብሔር ስለሚመጣ መልካም ስጦታ በደንብ ማወቅ እንዳለብን ያስታውሰናል። ማንኛውም ሰው በእግዚኣብሔር ጸጋ ኣማካኝነት መንፈሳዊ የሆኑትን ነገሮች ከተረዳ በእነዚህ መንፈሳዊ ነገሮች ውስጥ ይኖራል፣ መንፈሳዊ ነገሮችን የሚፃረር ነገር ኣያስብም ኣያደርግም፣ ምክንያቱም እርሱን የሚመራው በውስጡ ያለው የእግዚኣብሔር መንፈስ እንጂ የራሱ ሓሳብና ስሜት እንዲሁም የራሱ ኣመለካከት ብቻ ኣይደለም። ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ይህንን መንፈሳዊነታችንን የምንገልፅበት የተለያየ ስጦታ ለእያንዳዳችን ይሰጠናል፣ እዚህ ጋር ማስተዋል ያለብን ጉዳይ ይህንን ስጦታችንን የምንገልፅበት መንገዱ እንጂ የስጦታዎቹ ምንጭ ግን ኣንድ ነው እሱም እግዚኣብሔር ኣብ እግዚኣብሔር ወልድና እግዚኣብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህም ነው ዛሬ  ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው በቆሮንጦስ መልዕክቱ ጸጋም ስጦታም ልዩልዩ ነው መንፈስ ግን ኣንድ ነው፣ ኣገልግሎትም ልዩልዩ ነው ጌታ ግን ኣንድ ነው፣ ኣሠራርም ልዩልዩ ነው ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚኣብሔር ግን ኣንድ ነው እያለ የሚያስረዳን። ቅዱስ ሓዋርያው ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ይለናል፣ ለኣንዱ ጥበብን የመናገር ስጦታ በመንፈስ ይሰጠዋል ለኣንዱም በዚሁ መንፈስ እውቀትን የመናገር ስጦታ በመንፈስ ይሰጠዋል። እንግዲህ ስጦታችን ጥበብን የመናገር ይሁን እውነትን የመዝራት በሁለቱም መልኩ ለኣሕዛብ ሁሉ በሚጠቅምና ሰውን ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወቱ በሚያንፅ መልኩ ከልባችን ስጦታችንን ማካፈል ይገባናል። ምን ኣልባት የተቀበልነው ስጦታ የመፈወስ ከሆነ በምንም መልኩ ሳንታበይ የትዕቢት መንፈስ ሳይሰማን እግዚኣብሔር የሰጠንን ስጦታ መድረስ ወዳለበት ቦታ ሁሉ እናድርስ ማካፈል ባለብን ቦታ ሁሉ እናካፍል። ስጦታችን ተዓምር የማድረግ ከሆነ እንደው ተዓምረኛ ለመባልና በሰዎች ዘንድ ኣድናቆትን ለማግኘት ሳይሆን በሚገባው ቦታ ለሕዝበ እግዚኣብሔር መታነፅና ጥቅም ሲባል ተዓምራትን እንድናደርግ ይገባል። ስጦታችን ቀደም ሲል እንደተዘረዘረው ትንቢት የመናገር ወይም በልሳን የመናገር ወይንም በልሳን የተነገረውን የመተርጎም ከሆነ ለሕዝበ እግዚኣብሔር ጥቅምና መታነፅ ሲባል ከልባችን ልናደርገው ይገባል። በዛሬው በሁለተኛ ንባብ ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በመጀመሪያ መልዕክቱ በቅዱስ ቅባት ተቀብታችኋልና የእውነት መንፈስ ተቀብላችኋል ይህም እውነት ሁሉን ነገር ስለሚገልፅላችሁ እውነትን በሚገባ ተረድታችሁታል ይለናል። እውነት ነው ገና ከጅምሩ ምስጢረ ጥምቀት ስንቀበል በቅዱስ ቅባት ተቀብተናል የእውነትንም መንፈስ ተላብሰናል ነገር ግን ይህን የተቀበልነውን ቅባት ወም ዘይት ከውስጣችን እንዳይጎል ዘወትር ልንጠነቀቅለትና በጎደለም ጊዜ እየተከታተልን በምስጢረ ንሰሃ ኣማካኝነት ልንሞላው ይገባል፣ ይህንን ካደረግን በእርግጥም በዚህ ቅዱስ ቅባት ኣማካኝነት ያገኘነው እውነት ሁሌም ኣብሮን ይቆያል። ሁሌም እውነትን ይዞ የሚጓዝ ሰው ደግሞ ቅዱስ ሓዋርያው ዮሓንስ በዚሁ በመጀመሪያ መልዕክቱ 2፡ 25 ላይ እንደሚለው ሽልማቱ የዘለዓለምን ሕይወት መውረስ ነው። ሁሌም እውነትን ይዞ የማይጓዝ ሰው ደግሞ ጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እውነትን ባለመያዙ በውስጡ በሚሰማው እፍረት  ምክንያት በፊቱ ሊቆም ኣይችልም። ዛሬ እኛም እያዳዳችን በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምንኖር ልብ ልንል ይገባል። ጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜም ቢሆን በፍቅሩ እንድንመላለስ የእርሱን እውነት ይዘን እንድንጓዝና ይህንንም እውነት በሄድንበት ቦታ ሁሉ እንድንመሰክር ይፈልጋል። ይህንን ምስክርነት ስንሰጥም እርሱ ራሱ ከእኛ ጋር ኣብሮ በመሆን ያበረታታናል ኃይልም ይሰጠናል። ታዲያ እኛ ልክ እሱ እንደሚፈልገው ከእርሱ በሚመነጨው ኃይል ይህንን እውነት ይዘን ወደፊት እየተጓዝን እንገኛለን ወይስ ይህ የተሰጠንን የእውነት ብርሃን ለእኛም ሆነ ለሌሎች እንዳያበራ እንቅብ ደፍተንበት እንጓዛለን?ይህ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን እውነት ይዘን ወደፊት መቀጠል ካልቻልን እኛም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻ ጊዜ ሲገለጥ በፊቱ በጽናት የመቆም ደፍረት ኣይኖረንም ቀና ብለን ፊቱን ለማየት ኣቅማችን ኣይፈቅድልንም። እንዲሁ በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻ ግልፀት ብቻ ሳይሆን እንዲሁም በዕለታዊ ኑሮኣችንም የተረጋጋና ሰላም የሞላበት ኑሮ ልንመራ ኣንችልም፣ ምክንያቱም እውነተኛ ሰላም የሚመነጨው እውነትንና የእውነትን መንገድ ይዘን መጓዝ ስንችል ብቻ ነው። እውነት ባለበት ቦታ ሁሉ እውነተኛ ሰላም ኣለ፣ እውነተኛ ሰላም ባለበት ቦታ ሁሉ እውነተኛ ፍቅር ኣለ፣ እውነተኛ ፍቅር ባለበት ቦታ ሁሉ እውነተኛ መተሳሰብ ኣለ፣ እውነተኛ መተሳሰብ ባለነት ቦታ ሁሉ እውነተኛ መከባበር ኣለ፣ እውነተኛ መከባበር ባለበት ቦታ ሁሉ ራሱ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣለ።

እውነት የዘለዓለም ሕይወት መገኛ መንገድ ናት ለዚህ ነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዮሓንስ ወንጌል 14፡6 እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ እያለ ራሱን የሚገልፅለን። በእርሱ የሚኖር ሁሌም በእርሱ እውነት ውስጥ ይመላለሳልና የዘለዓለምን ሕይወት ይወርሳል ስለዚህ እኛም ይህንን እውነት ተከትለን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ወደደረሰበት ቦታ ለመድረስ እርሱ ወደገባበት ክብር እንድንገባ ተጋብዘናል፣ በእርሱም ብቻ ካልሆነ ወደ እግዚኣብሔር እንደማንደርስ ተረድተናልና በእውነት መንገድ እንራመድ እውነትን እንመስክር ስለ እውነትም እንሙት ምክንያቱም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዮሓንስ ወንጌል 8፡32 ላይ እንደሚለን ይህ እውነት ሁሌም ነፃ ያወጣናል። በዛሬው በዮሓንስ ወንጌል ምዕራፍ 14 ላይ ስለኣስቆርቱ ይሁዳ ሳይሆን ሌላኛው ይሁዳ ጌታ ሆይ እንዴት ነው ራስህን ለእኛ የምትገልፀው? ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጠው ሰምተናል። ይህም መልስ ዛሬ ለሁላችን የሚያስገነዝበን ነገር ኣለ ይኸውም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ፍጹም እውነት ነው ስለዚህ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጋር የሆነ ሁሉ ይህንን እውነት ጠብቆ ይህንን እውነት ተንተርሶ ይህንን እውነት ኣንግቦ ይጓዛል ይህንንም በማድረጉ የእግዚኣብሔር ኣብና ወልድ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ይሆናል። ይህንን ሁኔታ ወንጌላዊው ዮሓንስ በዚሁ ምዕራፍ ቁትር 23 ላይ ያረጋግጥልናል እንዲህም ይለናል። የሚወድኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል ኣባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን ይላል። ዘወትር በእውነት ውስጥ የሚመላለስ ሰው ሽልማቱ ይህ ነው ከእውነት ርቆ የሚኖር ሰው ደግሞ ልክ በጨለማ ውስጥ እንድሚጓዝ ሰው ሕይወቱ ሙሉ በምድርም ሆነ በሰማይ የተጭበረበረ ይሆናል። በእውነት ውስጥ የሚጓዝ ሰው ሁል ጊዜም ቢሆን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ነውና በስህተት ውስጥ ከመውድቅ የራቀ ነው፣ በልቡም ሆነ በኣእምሮው ደስተኛ ነው ሰላማዊ ነው የእውነት መልዕክተኛ ነው። ሰው ሁልጊዜም ቢሆን በውስጡ ያለውን ያካፍላል፣ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ሰው በውስጡ ያለውን ደስታ ፍቅር እውነት ሰላም እና የመሳሰሉትን ሁሉ ለሌሎች ያካፍላል፣ ሌሎችም በእውነት ውስጥ እንዲመላለሱ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ኣምባሳደር ይሆናል። እኛም ዛሬ ይህንን መንገድ እንድንከተል እውነትን ኣንግበን የእውነትም ኣምባሳደር በመሆን ከራሳችን ጀምረን በቤተሰባችን ብሎም በጎረቤትና በምንሰራበት ቦታም ሁሉ የዚህ እውነትና ሰላም ፍቅርና ደስታ መስካሪዎች እንሁን። ይህንንም ለማድረግ ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳትና ጠበቃ  የእውነት እናትና የእውነተኛ ደስታና ፍቅር ምንጭ የሆነች ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን ፀጋና በረከት ታማልደን የሰማነውን በልባችን ታኑርልን።

10 June 2018, 15:24