ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ ፓናማ ገቡ

ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ  የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን በፓናማ እንደሚከበር ይታወቃል። በዚህ በፓናማ በሚካሄደው 34ኛው ዓለማቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ረቡዕ ጥር 15/2011 ዓ.ም በሮም ከተማ ከሚገኘው እና በሌዮናርዶ ዳቪንቺ ስም ከተሰየመው ዓለማቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ተነስተው 9500 ኪሎ ሜትሮችን በአየር ላይ አቋርጠው 12፡55 ደቂቃ የሚወስድ በረራ አድርገው የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የስፔን፣ የፖርቱጋል፣ የሳንታ ማሪያ ደሴት፣ የአሜሪካ ውቅያኖሶችን፣ ፖርታሪኮን፣ የዶሜኒካን ሪፖብሊክን፣ አንቲሌ ኦልናደሲ ደሴትን፣ የኮሎምቢያን የበረራ የአየር ክልል አቋርጠው በፓናማ በሚገኘው ቶኩሜን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እንደ ደረሱ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

የዚህ ዘገባ አቅራቢዎች ዮሐንስ መኮንን እና መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ከሮም እስከ ፓናማ ቅዱስነታቸው በአውሮፕላን ያደርጉት ጉዞ 12 ሰዓት ከ55 ደቂቃ የፈጀ ረዘም ያለ በረራ እንደ ሆነ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን እንደ ተለመደው እና ቅዱስነታቸው ማነኛውንም ዓይነት ዓለማቀፍ ሐዋሪያው ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት በሚጓዙበት አውሮፓላን ውስጥ ሆነው ከጋዜጠኞች ለሚቀርብላቸው ጥያቄዎች መልስ እንደ ሚሰጡ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው ትላንትው እለት ማለትም በጥር 15/2011 ዓ.ም ወደ ፓናማ ባደርጉት ጎዞ ላይ ከጋዜጦች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች እና እርሳቸው የሰጡትን ምላሽ እንደ ሚከተለው እናቀርብላችኋለን ተከታተሉን።

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ወደ ፓናማ የተጓዙት የጃፓን ጋዜጠኞች ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ጉዞ እቅዳቸው መካከል ወደ ጃፓን የመምጣት ዕቅድ እንዳለ ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ቅዱስነታቸው ሲመልሱ በሕዳር ወር 2012 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጃፓን ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ገልጸው፣ ለዚህም ጋዜጠኛው እንዲዘጋጅበት አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጃፓን ለማድረግ ካላቸው እቅድ በተጨማሪ በኢራቅም ተመሳሳይ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ከዚህ በፊት የገለጹ ቢሆንም ነገር ግን ከኢራቅ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ በኩል የተሰጣቸው ማረጋገጫ ለጊዜው አልተገኘም ብለዋል።

ስደተኞችን በተመለከተ ከሌላ ጋዜጠኛ በኩል የቀረበላቸው ጥያቄ፣ በባሕር ላይ ጉዞ እያለ ሕይወቱን ያጣ አንድ ወጣት ጉዳይ ሲሆን ወጣቱ ከለበሰው ልብስ ጋር በጨርቅ ቋጥሮ የነበረው መልዕክት ለቅዱስነታቸው መቅረቡ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ስደተኞችን በተመለከተ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች በሙሉ መልስ የሚሰጡት የፓናማውን ጎዞ ፈጽመው ሲመለሱ እንደሚሆን ገልጸዋል።

ከሜክሲኮ ወደ ሰሜን አሜርካ የሚሰደዱትን ሰዎች ለማስቆም የሰሜን አሜርካ መንግሥት በሁለቱ አገሮች መካከል፣ ቲዩዋና በተበላ የሁለቱ አገሮች ወሰን ላይ ስለሚገነባው ግድግዳን በተመለከተ ከኢጣሊያ ቴለቪዥን ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲመልሱ፣ ፍርሃት የሰውን ልጅ ምን ያህል እንደጎዳው ገልጸው፣ የፍርሃት ግድግዳዎች በሚል ርዕስ የተጻፈ፣ ሰፋ ያለ ርዕስ፣ ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ በተባለ የቅድስት መንበር ጋዜጣ ላይ የተብራራ መሆኑን ገልጸው በጥንቃቄ እንዲመለከተው ጠይቀዋል።

የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተ የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ፣ ከተቀሩት ጋዜጠኞችም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ጊዜ እንደገለጹት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጃፓን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እየተጠና መሆኑን ገልጸው፣ ቅዱስነታቸው ያችን አገር ለመጎብኘት ያላቸው ምኞት ትልቅ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጻቸውን ተናግረዋል። ወደ ኢራቅ ስለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝትም፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን ባለፈው ታሕሳስ ወር የኢራቅ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ሲመለሱ እንደገለጹት፣ ቅዱስነታቸው ኢራቅን እንዲጎበኙ መንገድ የሚከፍት አጋጣሚ ለጊዜው እንዳልተመቻቸ መናገራቸውን አስታውሰዋል።           

ከጥር 14-19/2011 ዓ.ም “እነሆኝ  የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ” (ሉቃ 1፡38) በሚል መሪ ቃል 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በፓናማ እንደሚከበር ቀደም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን በዚህ 34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ወደ እዚያው ማቅናታቸውን ቀድም ሲል መግለጻችን ይታወሳል። በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በትልንትናው እለት ማለትም በጥር 15/2011 ዓ.ም በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 12፡30 ላይ በቶኩማን የፓናማ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሰላም መድረሳቸው ተገሉጹዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በ34ኛው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለመሳተፍ ፓናማ ገቡ
24 January 2019, 14:58