ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀምረዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሁለቱ የመካከለኛው አውሮፓ አገሮች የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጀመራቸው ታውቋል። በሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉትን 34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ለመጀመር ከሮም ፊውሚቺኖ አውሮፕላን ማረፊፋ እሑድ ጥዋት መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ተነስተው ወደ ሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ገብተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

34ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን እሑድ የጀመሩት በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ሲሆን፣ በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 01:45 ደቂቃ ወደ ቡዳፔስት አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት እና ከሐይማኖት መሪዎች አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል። ቀጥለውም በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ከነሐሴ 30/2013 ዓ. ም. እስከ እሑድ መስከረም 2/2014 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ የቆየው 52ኛ ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል። በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር መሠረት በሃንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ያላቸውን የ7 ሰዓት ቆይታ ካጠናቀቁ በኋላ የጉብኝታቸው ሁለተኛ አገር ወደ ሆነችው ስሎቫኪያ ከሰዓት በኋላ መጓዛቸው ታውቋል። ቅዱነታቸው በሁለቱ አገሮች የጀመሩትን ሐዋርያዊ ጉብኝት መጭው ዕሮብ መስከረም 5/2014 ዓ. ም የሚፈጽሙት መሆኑን የጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያስረዳል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን መግለጫን ዋቢ በማድረግ ባስተላለፍነው ዜና መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ዋና ዓላማ፣ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰጧትን ክብር እና ውዳሴ በመጨመር ፣ በቅርቡ ባደረጉት የቀዶ ጥገና ሕክምና ዕርዳታ ወቅት ቅድስት ድንግል ማርያም ላደረገችላቸው ዕርዳታ ምስጋናቸውን ለማቅረብ መሆኑ ታውቋል። ምስጋናቸውንም የሚያቀርቡት፣ የስሎቫኪያ ባልደረባ በሆነች የሃዘንተኛይቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መሆኑ ታውቋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በመግለጫቸው፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በስሎቫኪያ የሚያደርጉት ንግደት ወይም መንፈሳዊ ጉዞ ተጨማሪ ዓላማ፣ ለመከራ እና ለስቃይ የተጋለጡትን፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ጨምሮ በሌሎች አካላዊ ሥቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ በአደራ ለማቅረብ መሆኑን አስረድተዋል።  

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት አራት ይዘቶች

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር፣ ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ለጋዜጠኖች ባደረጉት ገለጻ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት አራት ይዘቶች እንዳሉት ገልጸው፣ የመጀመርያው፥ በ52ኛው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ መዝጊያ ጸሎት ላይ መሳተፋቸው መንፈሳዊ ይዘትን እንደሚሰጠው፣ ሁለተኛው፣ ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ጋር መገናኘታቸው እና የቅዱስ ሲረልን እና የቅዱስ መቶድዮስን የወንጌል አገልግሎት የሚዘክሩ የሃንጋሪ እና የስሎቫኪያ ክርስቲያናዊ ቅርሶችን ማስታወሳቸው የክርስቲያኖችን ውህደት ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት እንደሚገልጽ፣ በሁለቱ አገሮች ዋና ከተሞች ውስጥ ከሚገኙ የአይሁድ እምነት መሪዎች ጋር መገናኘታቸው ከሌሎች ሐይማኖቶች ጋር ያለውን ግንኙት ለማሳደግ ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ በመሆኑ እና በ 20 ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው አንባ ገነናዊ አገዛዝ ስደት በደረሰባቸው የሃንጋሪ እና የስሎቫኪያ ካቶሊኮች የተሰጠውን የጀግንነት፣ የእምነት እና የሰማዕትነት ምስክርነት በማስታወስ የሚያስተላልፉት መልዕክት የወንጌል መልዕክተኛነት ይዘት ያለው መሆኑን፣ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ለጋዜጠኖች በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።         

13 September 2021, 00:29