ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ምልአት ያለን ክርስቲያኖች እንድንሆን ያደርገናል” አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 13/2012 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከእዚህ ቀደም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የሐዋርያት ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ ሲያደርጉት የነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገጸ ሲሆን በእዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው ባደረጉት የክፍል 21 የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን ያደርገው በደኅና ወደ ምድር ከደረስን በኋላ፣ ደሴቲቱ ማልታ ተብላ እንደምትጠራ ተረዳን። የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን” (የሐዋ 28፡1-2.10) በሚለው የእግዚኣብሔር ቃል ላይ መሰረቱን ያደርገ ሲሆን ““እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ምልአት ያለው ክርስቲያኖች እንድንሆን ያደርገናል” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በጥር 13/2012 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ!

የዛሬ የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ለክርስቲያኖች አንድነት ከሚቀርበው የፀሎት ሳምንት ጋር የተጣጣመ ነው። ለእዚህ አመት ለክርስቲያኖች አንድነት ለሚደርገው የጸሎት ሳምንት የተመረጠው የጸሎት መሪ ቃል የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያላቸው የማልታ እና የጎዞ ማኅበረሰብ ለሐዋርያው ጳውሎስ እና ለባልደረቦቹ በማልታ በሚገኙ ነዋሪዎች ዘንድ የተደረገውን የእንግዳ ተቀባይነት መስተንግዶ በሚገልጸው የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በተጠቀሰው ታሪክ ላይ ነው። ይህንን በተመለከተ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገዳም ባደረኩት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ውስጥ ገልጬ ነበር።

እንግዲያውስ ከዚያ የመርከብ መሰባበር አደጋ አስደናቂ ልምድ እንጀምር። ሐዋርያው ጳውሎስ ሲጓዝባት የነበረችሁ መርከብ በሁኔታዎች መልካምነት ላይ የተመረኮዘች ነበረች።  ለአስራ አራት ቀናት በባህር ላይ ስትጓዝ ስትንሳፈፍም ነበር፣ እናም ፀሀይም ሆነ ከዋክብት ስለማይታዩ ተጓዦቹ ግራ ተጋብተዋል፣ ጠፍተናል ብለው አስበዋል። ከእነሱ በታች የነበረው ባሕር በኃይለኛ ማዕበል እየተናወጠ ከመርከባቸው ጋር ሲላተም ይሰማቸው ነበር። ከላያቸው ደግሞ ነፋስ እና ዝናብ ይወርድባቸው ነበር። የባህሩ ኃይል እና ማዕበል ለተሳፋሪዎቹ ዕጣ ፈንታ እጅግ አደገኛ የነበረ ሲሆን በእዚህም የተነሳ የጉዞዋቸው እጣ ፈንታ መልካም እንደ ማይሆን የተገነዘቡ ሲሆን የመርከቧ ቀዛፊዎች ግን የግድዬለሽነት ስሜት ይሰማቸው ነበር፣ በመርከቡ ላይ 260 የሚሆኑ ተሳፋሪዎች ነበሩ።

ነገር ግን ሐዋርያው ጳውሎስ ነገሩ እንዲህ እንደ ማይጠናቀቅ በሚገባ ያውቅ ነበር። ሕይወቱ ኢየሱስን ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሔር እጅ ነው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ቅዱስ ወንጌልን እንዲያሰራጭ እንደጠራው እምነቱ ይነግረዋል። በተጨማሪም እምነቱ ኢየሱስ እንደገለጠው አፍቃሪ አባት መሆኑን ይነግረዋል። ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእርሱ ጋር ሲጓዙ ለነበሩ ጓደኞቹ በእምነቱ ተነሳስቶ እግዚአብሔር የራሳቸውን ፀጉር እንዲያጡ እንኳን እንደማይፈቅድላቸው ለእነሱ ይነግራቸዋል።

መርከቧ በማልታ የባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኘው ሰፊ ክብ ቦታ አከባቢ በተቃረበችበት ጊዜ እና ሁሉም ተሳፋሪዎች በሰላም እና በደህና ወደ ደረቅ መሬት ላይ በደረሱ ጊዜ ይህ ትንቢት ይፈጸማል። እዚያ አዲስ ነገር ያጋጥማቸዋል። በማዕበል በሚናወጠው ባሕር ላይ ካለው አሰቃቂ ሁኔታ በተቃራኒ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ያልተለመደ ሰብአዊነት” በማሳየት ምስክርነት ይሰጣሉ። እነዚህ ሰዎች የውጭ አገር ዜጎች ለሆኑ ሰዎች እርዳታ ያደርጋሉ። እንዲሞቃቸው እሳት ያንዳሉ ምክንያቱም በጣም ይበርድ ነበረና፣ እሳት ያቀጣጥላሉ፣ ከዝናብ እንዲጠለሉ መኖሪያ እና ምግብ ይሰጡዋቸዋል። የክርስቶስን ወንጌል ገና ያልተቀበሉ ቢሆኑም ፣ በተጨባጭ የደግነት ተግባራት የእግዚአብሔርን ፍቅር ይገልጣሉ። በእርግጥ ድንገተኛ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እና አካላዊ መግለጫዎች ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የሆነ ነገር ያስተላልፋሉ፣ እንዲሁም በማልታ ደሴት ነዋሪዎች ዘንድ በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የተደረገው መስተንግዶ እግዚአብሔር በሐዋርያው ጳውሎስ በኩል በደሴቲቱ ላይ በሚሠራው የመፈወስ ቅዱስ ተዓምራት ይሸለማሉ። ስለዚህ የማልታ ሕዝቦች እግዚአብሔር ለሐዋርያቱ የሰጠው ማረጋገጫ ምልክት ከሆኑ እርሱ ራሱ ለእነርሱም የእግዚአብሄር ርህራሄ ምስክር ነው ማለት ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!  የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥነ ምግባራዊ ባሕርይ ነው። በመጀመሪያ ሌሎች ክርስቲያኖች በእውነት በክርስቶስ ውስጥ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሆናቸውን መገንዘብ ማለት ነው። ብቸኛው የልግስና መንገድ አይደለም፣ ምክንያቱም ሌሎች ክርስቲያኖችን ስናስተናግድ የተሰጠን ስጦታ አድርገን እንቀበላቸዋለን። መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ በወንድሞቻችን እና በእህቶቻችን ውስጥ የዘራውን ዘር ለመቀበል እንግዶችን ተቀብለን ማስተናገድ ይኖርብናል፣ ምክንያቱም ይህ ለእኛም እንደ ስጦታ ይሆናል። ከእኛ ለየት ያለ ባህል ያላቸውን ክርስቲያኖች ተቀብሎ ማስተናገድ ማለት በቅድሚያ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለእነርሱ ማሳየት ማለት ነው፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፣ ደግሞም እግዚአብሔር በሕይወታቸው ያከናወነውን ነገር መቀበል ማለት ነው። እንግዳ ተቀባይነት ያለው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለማዳመጥ፣ ለእራሳቸው የእምነት ታሪኮች እና ለማህበረሰቡ ታሪክ ትኩረት በመስጠት ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። እንግዳ ተቀባይነት ያለው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ሌሎች ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ያዩትን ተሞክሮ እና ከእርሱ የሚመጡትን መንፈሳዊ ስጦታዎች የማግኘት ምኞት ያካትታል።

በእዚያን ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ በጀልባ በአደገኛ ሁኔታ ይቋረጡት ባሕር አሁንም ቢሆን በባሕር ላይ ጉዞ ለሚያደርጉ ሰዎች ሕይወት አደገኛ የሆነ ስፍራ ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ስደተኞች ወንዶች እና ሴቶች ከዓመፅ፣ ከጦርነትና ከድህነት ለማምለጥ በሚያደርጉት ጉዞ አደገኛ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥማቸዋል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ እና የጉዞ ጓደኞቹ በምድረ በዳ ውስጥ፣ በወንዞች እና በባሕሮች  ላይ በሚጓዙበት ወቅት ብቸኝነት ይሰማቸዋል። በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፣ ስደተኞች በአንዳንድ አገራት መሪዎች ዘንድ እንደ አደገኛ ሆነው ይቆጠራሉ።    እንደ ችግር ማዕበል ተደርገው ይቆጠራሉ።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለስደተኞች እንክብካቤ በማደረግ በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማሳየት አብረን መሥራት አለብን። የጥላቻ እና የግድየለሽነት ባሕሪይ ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ዘንድ ውድ እና በእርሱ የተወደደ መሆኑን መመስከር እንችላለን። የእኛ ጥሪ እና ተልዕኮ መሆን የሚገባው በእኛ መካከል ያሉት ክፍፍሎች ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ፍቅር ምልክት እንዳልሆኑ ተገንዝቦ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ መሥራት ይኖርብናል። የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በተላበሰ መልኩ በመኖር በተለይም ሕይወታቸው ይበልጡኑ ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች በመርዳት እና በማገዝ ይበልጡኑ የተሻልን የሰው ልጆች እንድንሆን የሚያደርገን ሲሆን የተሻለ የእርሱ ደቀ-መዛሙርት እና ይበልጡኑ ሙሉ የሆንን ክርስቲያኖች እንዲንሆን ያደርገናል፣በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እና ቅርበት እንድንፈጥር ያደርገናል፣ እርሱም  የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

Photogallery

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በጥር 13/2012 ዓ.ም ያደረጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ
22 January 2020, 13:17