ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በቫቲካን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “ከፍተኛ የሆነ ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት እግዚኣብሔር ብቻችንን አይተወንም

ዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ወይም በቫቲካን በሚገኘው የጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሻ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በተለያዩ አርእስቶች ላይ ተመርኩዘው የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በዛሬው እለት ማለትም በሚያዝያ 23/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ በተከታታይ ሲያደርጉት የነበረው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በዚህ “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላያ በሚያዝያ 23/2011 ዓ.ም ያደረጉት የክፍል 14 የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረቱን አድርጎ የነበረው “ወደ ፈተና አትጋባን” በሚለው የመማጸኛ ጸሎት ላይ እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን “እኛ ከፍተኛ በሆነ ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት እግዚአብሔር ብቻችንን አይተወንም” ማለታቸው ተገልጹዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሚያዝያ 23/2011 ዓ.ም ያደረጉትን የጠቅላላ የትምሕርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ቀደም ሲል “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ዙሪያ የጀመርነውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ “ወደ ፈተና አታግባን” (ማቴ 6፡13) የሚለውን በዚህ ጸሎት ውስጥ የሚገኘውን የመጨረሻውን የመማጸኛ ጸሎት እንመለከታለን። “አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት"አባታችን" የሚለውን ቃል በመጠቀም አስደሳች በሆነ መንገድ ይጀምራል፦ የእግዚአብሄር ታላቅ እቅድ በእኛ መካከል ይከናወን ዘንድ እንድንመኝ ያደርገናል። ከዚያም ህይወትን ይመለከታል፣ በየእለቱ የሚያስፈልገንን "የዕለት እንጀራ" እንድንጠይቅ ያደርገናል። ከዛም በመቀጥል ብዙ ጊዜ እኛ በራስ ወዳድነት መንፈስ ውስጥ በመገኘታችን የተነሳ እኛ ከሌሎች ግለሰቦች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት በመግለጽ ይቅርታ እንድንጠይቅ እና እኛም ይቅር ማለት እንደ ሚገባን ይገልጻል። ነገር ግን በዚህ ከሰማያዊው አባታችን ጋር በምናደርገው ውይይት ውስጥ በሚገኘው የመጨረሻው የመማጸኛ ጸሎት ውስጥ እኛ በተሰጠን ነጻነት እና የክፋት አደጋ መካከል የተጋረጠውን ግጭት ያመለክታል።

እንደሚታወቀው በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተካተተው የመጀመሪያው የግሪክ ቃል በትክክለኛው መንገድ ለመመልከት አስቸጋሪ ነው፣ ሁሉም ዘመናዊ የሆኑ ትርጉሞች ትንሽ ድክመት አላቸው። በአንዱ ዓረፍተ ነገር ላይ ሁላችንም መስማማት ግን እንችላለን፣ ምንም እንኳን ይህንን ዓረፍተ ነገር ብንገነዘብም ነገር ግን በሰዎች የሕይወት ጉዞ መንገድ ላይ አንገላታች የሆኑ ፈተናዎች በዋነኝነት እንዲከሰቱ የሚያደርገው እግዚአብሔር ነው የሚለውን ግንዛቤ ግን ማካተት አይኖርብንም። አምላክ በልጆቹ ላይ ወጥመድና አደጋዎች እንዲከሰቱ ያደርጋል የሚለውን አሰተሳሰብ ማስወገድ ይኖርብናል። የዚህ ዓይነቱ ትርጓሜ በቅድሚያ እርስ በእርሱ የሚጣረዝ ሲሆን በኢየሱስ አማካይነት ከተገለጠው የእግዚአብሔር አምሳል እጅግ የራቀ ነው። “አባታችን ሆይ” የሚለው ጸሎት “አባት” በሚለው ቃል እንደ ሚጀምር መዘንጋት የለብንም። አንድ አባት ደግሞ በልጆቹ ላይ አደገኛ የሆነ ነገር አይፈጽምም። ክርስቲያኖች ምቀኛ ከሆነ፣ ከሰው ጋር ከሚወዳደር፣ ወይም ሰውን ከሚፈታተን አምላክ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። እነዚህ የአረማውያን አማልክት ምስሎች ናቸው። ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ “ማንም ሲፈተን፣ “እግዚአብሔር ፈተነኝ” አይበል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንም፤ እርሱም ማንንም አይፈትንም” (ያዕቆብ 1፡13) በማለት ያናገራል። እርሱ ግን በተቃራኒው የክፉ ነገሮች ምንጭ አይደለም፣ ኢየሱስ እንደ ሚያስተምረን ዓሳ ለሚጠይቀው ልጁ እባብ የሚሰጥ አባት የለምና። ሰው በሕይወቱ ውስጥ ለክፉ ነገር በሚገለጥበት ጊዜ ከዚህ ክፉ ነገር እንዲላቀቅ ከእርሱ ጋር ሆኖ ይዋጋል። ለእኛ ሁልጊዜ የሚዋጋ አምላክ ነው እንጂ የእኛ ተቃዋሚ አይደለም። እርሱ አባት ነው! በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው ታዲያ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት የምንጸልያው።

እነዚህ ፈተና እና መከራ የሚሉት ሁለት ቃላት ምስጢራዊ በሆነ መልኩ በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ ተከስተው ያለፉ ነገሮች ናቸው። በእዚህ ተሞክሮ ውስጥ የእግዚአብሔር ልጅ ክፉ ነገር እንዳያሸንፈን ሙሉ በሙሉ ወንድማችን ይሆናል። እናም "አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ የሚገኘው ከባድ የሚባሉት የመመጸኛ ጸሎቶች ቀደም ሲል መልስ እንደ ተሰጣቸው ቅዱስ ወንጌል ያሳየናል፣ እግዚኣብሔር ብቻችንን አይተወንም፣ ነገር ግን በኢየሱስ አምካይነት “እግዚኣብሔር ከእኛ ጋር እንደ ሆነ” በመግለጽ እስከ መጨረሻው ድረስ ከእኛ ጋር እንደ ሚሆን አሳይቶናል። ሕይወት ሲሰጠን ከእኛ ጋር ነበር፣ በህይወታችን ዘመን ከኛ ጋር ነው፣ በደስታችን ወቅት ከእኛ ጋር ነው፣ በፈተናችን ወቅት ከእኛ ጋር ነው፣ እርሱ በሀዘናችን ጊዜ ከእኛ ጋር ነው፣ ስንሸነፍም ከእኛ ጋር ነው፣ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ሁሉ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው፣ ምክንያቱም እርሱ አባታችን ስለሆነ ሊተወን አይችልምና።

የወንድማማችነት መንፈስን ክደን በሁሉም ነገር እና በሁሉም ሰው ላይ የበላይ ሆነን ለመታየት በማሰብ በሌሎች ላይ ክፉ የሆነ ነገር ለመፈጸም ስንሞክር ከእንደነዚህ ዓይነት ፈተና እንወጣ ዘንድ ኢየሱስ ቀደም ሲል ታግሎልን እንደ ነበረ የመጀመሪያዎቹ የቅዱስ ወንጌል ገጾች ይመሰክራሉ። በኃጢአተኞች መካከል ገብቶ በመጥመቁ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኃላ ኢየሱስ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ በሰይጣን ተፈተነ። ኢየሱስ ይፋዊ የሆነ አስተምህሮውን የጀመረው በሰይጣን ከተፈተነ በኋላ ነበር። ሰይጣን በዚያን ወቅት ነበር። በጣም ብዙ ሰዎች “ለምንድነው እሱ በጥንት ጊዜ ስለነበረው ስለስይጣን የሚወራው? ሰይጣን እኮ በፍጹም የለም” ብለው ያናገራሉ። በዚህ ረገድ ቅዱስ ወንጌል የሚያስተምረንን አስተምህሮ መመልከት ይገባል፣ ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ግብግብ ፈጥሮ ነበር፣ በሰይጣን ተፈትኖ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ሁሉንም ፈተናዎች ውድቅ አድርጎ በአሸናፊነት አጠናቁዋል። የማቴዎስ ወንጌል አንድ አስደናቂ የሆነ ማስታወሻ በማቅረብ በኢየሱስና በጠላት መካከል የነበረውን ውጊያ በተመለከተ ባቀረበው ታሪክ ማጠቃለያ ላይ “ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት” (ማቴ 4፡11) በማለት ያጠቃልላል።

ነገር ግን እኛ ከፍተኛ በሆነ ፈተና ውስጥ በምንገባበት ወቅት እግዚአብሔር ብቻችንን አይተወንም። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ለመጸለይ በሄደበት ወቅት ልቡ በቃላት ሊገለጽ በማይቻል የስቃይ ስሜት ውስጥ እንደ ገባ ለደቀ-መዛሙርቱ ነግሮዋቸው ነበር - እሱም የብቸኛነት እና የመገለል ተሞክሮ አጋጥሞት ነበር። የዓለምን ኃጢአት ሁሉ ኃላፊነት ወስዶ በትክሻው ላይ የተሸከመ፣ ሊነግር በማይችል ጭንቀት ውስጥ የገባው እርሱ ብቻ ነው። ፈተና አንድ ያልተጠበቀ ነገር እንዲከሰት ያደርጋል። ኢየሱስ ለእራሱ የሚሆን ፍቅር በፍጹም ለምኖ አያውቅም፣ ሆኖም በዚያው ምሽት እስከ ሞት ድረስ ነፍሱ በጣም አዝና ነበር፣ በዚህም የተነሳ ለደቀ-መዛሙርቱ “እዚህ ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ይናገራል። እንደምናውቀው ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት በመደንዘዛቸው የተነሳ እንቅልፍ ወስዶዋቸው ነበር። በስቃይ ወቅት ሰው በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ሌላ ሰው ብቻውን ትቶት መተኛት እንደ ሌለበት እግዚኣብሔር ያሳስባል። ሰው የራሱን መከራ በሚያውቅበት ጊዜ እግዚአብሔር ይመለከተዋል። በህይወታችን አስጨናቂ ወቅቶች፣ በታላላቅ መከራዎች ውስጥ፣ እጅግ በጣም በምንጨነቅባቸው ጊዜያት ውስጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይገናኛል፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይዋጋል፣ እርሱ ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ነው። ለምን? ምክንያቱም እርሱ አባት ስለሆነ። ይህንን ጸሎት “አባታችን ሆይ” ብለን የጀመርነው በዚሁ ምክንያት ነው። አንድ አባት ልጆቹን ብቻቸውን አይተዋቸውም። የኢየሱስ የዚያ ምሽት ትግል ክርስቶስ ሥጋ የለበሰበት የመጨረሻው ማህተም ነው፡ እግዚአብሔር እኛን ለማግኘት ወደ ጥልቅ ሸለቆ ወረደ በታሪክ ውስጥ እኛን ያጋጠሙንን ችግሮች መጋፈጥ እንችል ዘንድ ወደ ታች ወረደ።

በፈተናው ሰዓት የእኛ መፅናኛ የሚሆነው: ኢየሱስ ሸለቆውን ስለተሻገረ ከእንግዲህ ወዲያ ባዶነት አይኖርም ነገር ግን የእግዚኣብሔር ልጅ ከእኛ ጋር ስለሚሆን ሁሉም ነገር የተባረከ ይሆናል። እርሱ መቸም ቢሆን ብቻችንን አይተወንም!

ስለዚህ አምላክ ሆይ የመከራ እና የፈተና ወቅቶችን ከእኛ አርቅ። ነገር ግን በእነዚህ ወቅቶች ውስጥ በምንገባበት ጊዜ አባት ሆይ ብቻችንን አለመሆናችንን አሳየን። አንተ አባታችን ነህ። ክርስቶስ ከባድ የሆነውን መስቀል ተሸክሞ እንደ ነበረም አሳየን። በአንተ አባታዊ ፍቅር ተማምነን ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ሆነን መስቀሉን እንድንሸከም የሚያቀርብልንን ጥሪ እንድንቀበል አድርገን።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
01 May 2019, 16:06