የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ከወንድማቸው ጆርጅ ራሲንጌር ጋር በጸሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ፤              የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ከወንድማቸው ጆርጅ ራሲንጌር ጋር በጸሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ፤  

ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር ማረፋቸው ተነገረ።

በጠና ታመው የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው የቆዩት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር ረቡዕ ሰኔ 24/2012 ዓ. ም. ተወልደው ባደጉባት የጀርመን ከተማ ራቲስቦና ውስጥ ማረፋቸው ተሰምቷል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ታላቅ ወንድም የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሕመማቸው ጸንቶባቸው ሆስፒታል በመግባት የሕክምና ዕርዳታ ሲደረግላቸው መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት ወንድማቸው እና የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከቫቲካን ወደ ጀርመን በመጓዝ ጠይቀው መመለሳቸው ይታወሳል።

የቫቲካን ዜና፤

የ96 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የነበሩት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር በወጣትነት ዕድሜያቸው በጀርመን ውስጥ ካፔልሚስቴር የተባለ የእውቁ መዘምራን ማኅበር መሪ የነበሩ ሲሆን፣ ታናሽ ወንድማቸው ዮሴፍ ራዚንገር፣ የስነ መለኮት ትምህርታቸውን ፈጽመው የጵጵስና ማዕረግ ቀጥሎም የካርዲናልነት ማዕረግ፣ በኋላም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በመሆን የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል። ሁለቱ ወንድማማቾች የምስጢረ ክህነት ጸጋን በተመሳሳይ ቀን የተቀበሉ መሆናቸው ታውቋል።

በጀርመን ውስጥ ባቫሪያ ግዛት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥር 15/1924 ዓ. ም. የተወለዱት አቡነ ጆርጅ፣ ዕድሜአቸው 11 ዓመት ሲሞላቸው የቁምስናቸውን መዘምራን ማኅበር በኦርጋን የሙዚቃ መሣሪያ በማጀብ ሲያገለገሉ መቆየታቸው ይታወሳል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1935 ዓ. ም. ወደ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት የገቡት ብጹዕ አቡነ ጆርጅ የአገራቸው መንግሥት የሚጠይቀውን ግዳጅ ለመፈጸም ወደ ጣሊያን በመሄድ በውትድርና አገልግሎት የቆዩ መሆናቸው ታውቋል። በጣሊያን ናፖሊ ከተማ ለሦስት ዓመት ያህል በግዞት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ጀርመን ተመልሰው ከወላጆቻቸው ጋር መቀላቀላቸው ይታወሳል። ወደ ጀርመን ከተመለሱ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በ1947 ዓ. ም. በሙኒክ ከተማ በሚገኝ የግሬጎሪያን ከፍተኛ ዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት፣ ከታናሽ ወንድማቸው ዮሴፍ ጋር እንዲሁም ከሌሎች 40 ተማሪዎች ጋር ለክህነት ማዕረግ የሚያበቃቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ከተከታተሉ በኋላ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሰኔ ወር 1951 ዓ. ም. ከወንድማቸው ጋር በተመሳሳይ ቀን የክህነት ማዕረግ የተቀበሉ መሆናቸው ይታወሳል። ቀጥለውም በሬግኔስቡርግ ከተማ በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ የዜማ መሪ እና ደራሲ በመሆን ማገልገላቸው ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ 22/2008 ዓ. ም. በጣሊያን ውስጥ ከካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ከንቲባ የክብር ዜግነት መብት የተሰጣቸው መሆኑም ይታወሳል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ስለ ወንድማቸው የሕይወት ታሪክ ሲናገሩ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ታማኝ ረዳታቸው በመሆን ያገለገሏቸው፣ በአስቸጋሪ ወቅትም ትክክለኛውን አቅጣጫ በመጠቆም ከጎናቸው ሆነው ያገዟቸው መሆኑን አስታውሰዋል።  በልጅነት ጊዜያቸው ሁለቱ አብረው በመንበረ ታቦት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ያስታወሱት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ ሕይወታቸው ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንደሆነ በቅድሚያ እርሳቸው፣ ቀጥሎም ወንድማቸው የተገነዘቡ መሆኑን አስታውሰዋል።     

ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2011 ዓ. ም. ከአንድ የጀርመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ወንድማቸው ዮሴፍ ራዚንገር በጤና መታወክ ምክንያት ሐዋርያዊ የቤተክርስቲያን መሪነታቸውን በሚገባ ማከናወን የማይችሉ ከሆነው ስልጣናቸውን ለማስረክብ ወደ ኋላ ማለት የለባቸውም በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ይህን አስተያየታቸውን ወንድማቸው ለሆኑት ለቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በማቅረብ የመጀመሪያ መሆናቸው ታውቋል።

ብጹዕ አቡነ ጆርጅ ራዚንገር፣ በጀርመን ውስጥ ከምትገኝ የሬግኔስቡርግ ከተማ ተነስተው ባሁኑ ጊዜ በቫቲካን ውስጥ “ማቴር ኤክሌሲያ” ገዳም ውስጥ የሚገኙ ወንድማቸውን፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛን ለመጠየቅ በየጊዜው ወደ ሮም ሲመላለሱ መቆየታቸው ይታወሳል።             

02 July 2020, 10:47