እግዚአብሔር ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ  ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እግዚአብሔር ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?  

“የእግዚ/ር አባት መሆኑን የሚያምኑ ሁሉ ‘ፈቃድህ ይሁን’ ብለው መጸለይ ይኖርባቸዋል”!

“አባት ሆይ! ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ ውሰድ! ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን”

“አባታችን ሆይ”

ክፍል ዐስር

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ከዚህ ቀደም “አባታችን ሆይ!” በሚለው ጸሎት ዙሪያ ላይ የጀመርነውን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በመቀጠል ዛሬ ደግሞ በዚሁ ጸሎት ውስጥ በሚገኘው “ፈቃድህ ይሁን” በሚለው ሦስተኛው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ላይ ትኩረታችንን እናደርጋለን። ይህ የመማጸኛ የጸሎት ሐረግ የሚደገመው ከዚህ በፊት ከነበሩት ከሁለቱ ማለትም “ስምህ ይቀደስ” እና “መንግሥትህ ትምጣ” ከሚሉት የመማጸኛ ጸሎቶች በመቀጠል የሚደገም የጸሎት ሐረግ ሲሆን በዚህ መልኩ "ስምህ ይቀደስ"፣ "መንግሥትህ ይምጣ"፣ "ፍቃድህም ይሁን" የሚሉትን ሦስት መማጸኛዎችን በቅደም ተከተል በአንድነት በመጠቀም የሚደገም ጸሎት ነው። ዛሬ በሦስተኛው የመማጸኛ ጸሎት ሐረግ ላይ እናተኩራለን።

የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና

የሰው ልጅ ዓለምን መንከባከብ ከመጀመሩ በፊት አምላክ ለሰውና ለዓለም የሚጠቅም የማያቋርጥ እንክብካቤ አድርጉዋል። አጠቃላይ የቅዱስ ወንጌል ምልከታ ይህ ሐሳብ መቀልበሱን ያንጸባርቃል። ኃጢአተኛው ሰው የነበረው ዘኬዎስ ኢየሱስን ለማየት ስለ ፈለገ አንድ ዛፍ ላይ ወጣ፣ ነገር ግን ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ እግዚአብሔር እርሱን እየፈለገ እንደ ነበረ ግን አላወቀም። “ኢየሱስም ወደ እዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው”። በመጨረሻም ኢየሱስ “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና” (ሉቃስ 19፡5,10) በማለት ጨምሮ በአጽኖት ይናገራል። በእኛ ሕይወት ውስጥ ይፈጸም ዘንድ በመማጸን የምናቀርበው ጸሎት ይህ ነው! በኢየሱስ ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር ፍቃድ ምን ነበር? የጠፋውን መፈለግ እና ማዳን ነው። እናም እኛ ይህንን የመማጸኛ ጸሎት በምናቀርብበት ወቅት የእግዚአብሔር ፍለጋ የታለመለትን ግብ ይመታ ዘንድ፣ የእርሱ አጠቃላይ የደህንነት እቅድ በቅድሚያ በእኛ ውስጥ፣ ከእዚያም ቀጥሎ ደግሞ በመላው ዓለም ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን በመመኘት የምናቀርበው የመማጸኛ ጸሎት ነው። እግዚአብሔር እኔን እየፈለገኝ ነው፣ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስባችሁ ታውቃላችሁ ወይ? እያንዳንዳችንን የሚፈልገን እግዚአብሔር ነው ወይ? ብለን ጥያቄ ልናነሳ እንችል ይሆናል። አዎን አንተን ይፈልጋል፣ እኔንም ይፈልጋል፣ እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ይፈልገናል። እግዚኣብሔር ታላቅ ነው! ከዚህ ሁሉ ፍለጋ በስተጀርባ ያለው ፍቅር ምን ያህል ትልቅ ፍቅር ይሆን! 

እግዚአብሔር ሁሉም ሰዎች እንዲድኑ ይፈልጋል

እግዚአብሔር አሻሚ አይደለም፣ ከኋላም አይሸሸግም፣ የዓለምን የወደፊት ዕቅድ አሻሚ እና በሚለዋወጥ መልኩ አላዘጋጀም። በፍጹም እንዲህ አላደረገም። እርሱ በጣም ግልጽ ነው። ይህንን የማንረዳ ከሆንን “አባታችን ሆይ” በሚለው ጸሎት ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠውን የመማጸኛ ጸሎት ጭብጥ ለመረዳት ያዳግተናል። በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱሳችን እግዚአብሔር ለዓለም ስላለው አዎንታዊ የሆነ ፈቃድ የሚናገሩ መግለጫዎችን ይዞ ይገኛል። በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ውስጥ ይህንን ታማኝና ታጋሽ መለኮታዊ የሆነ የእግዚኣብሔርን ፈቃድ በተመለከተ መለኮታዊ የሆነ ምስክርነት የሚሰጡ ጥቅሶችን እናገኛለን (ቁ. 2821-2827)። ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመርያ መልእክቱ ላይ “እግዚአብሔር ሁሉም ሰዎች እንዲድኑ እና ወደ እውነት እውቀት እንዲደርሱ ይፈልጋል” (1ጢሞ 2፡4) ይላል። የእያንዳንዱ የሰው ልጅ ድህንነት  በእርግጠኝነት የእግዚአብሄር ፍቃድ ነው። እግዚአብሔር በፍቅሩ የልባችንን በር ያንኳኳል። ለምንድነው የሚያንኳኳው? እኛን ለመሳብ፣ ወደ እርሱ ሊስበን እና በደህንነት መንገድ ላይ እንድንጓዝ ሊያደርገን። እግዚአብሔር በደህንነት መንገድ ላይ እንጓዝ ዘንድ በፍቅሩ አማካይነት እጃችንን ይዞ ለመጓዝ ለእያንዳዳችን ቅርብ ነው። ከዚህ በስተጀርባ ያለው ፍቅር ምን ያህል ትልቅ ይሆን?

እግዚኣብሔር ነጻ ሊያወጣን ይፈልጋል

ስለዚህ "ፈቃድህ ይሁን” እያልን የተማጽዕኖ ጸሎት በምናደርግበት ወቅት ልክ እንደ ባርያ ራሳችንን ባዶ አድርገን በማሰብ ራሳችንን በመነቀነቅ መጸለይ አይኖርብንም። በፍጹም! እግዚኣብሔር ነጻ ሊያወጣን ይፈልጋል፣ ነጻ የሚያወጣን ደግሞ የእርሱ ፍቅር ነው። በእርግጥ "አባታችን ሆይ!" የሚለው ጸሎት የልጆች ጸሎት እንጂ የባሪያዎች ጸሎት አይደለም፣ የአባትን ልብ የሚያውቁና የእርሱን የፍቅር እቅድ የሚገነዘቡት ልጆች ብቻ ናቸው። ይህንን ጸሎት በምንጸልይበት ወቅት አስቀያሚ የሆነ እጣ ፈንታ ከፊት ለፊታችን እንደ ሚጠብቀን በማሰብ በትከሻችን ላይ እጃችንን አድርገን እኛ በፍጹም እንደ ማንለወጥ አስበን በዚህ መንፈስ ይህንን ጸሎት የምናደርግ ከሆነ ወየውልን! በተቃራኒው ለእኛ እና ለሕይወታችን መልካም የሆኑ ነገሮችን፣ ደህንነትን እና ሕይወትን በመስጠት እኛን ለመዳን በሚፈልገው በእግዚአብሔር ላይ ጠንካራ የሆነ እመንት በማስደር በዚህም መንፈስ ተሞልተን የምንጸልየው ጸሎት ሊሆን ይገባል። በብርታት መንፈስ ተሞልተን ልናደርገው የሚገባው ጸሎት ነው፣ በአለም ውስጥ በእግዚአብሄር እቅድ መሰረት የማይጓዙ በጣም ብዙ ነገሮች እና ብዙ እውነታዎች ስላሉ እንዲያውም ይህንን ጸሎት በተጋድሎ መንፈስ ልንጸልየው ይገባል። ሁላችንም እናውቃቸዋለን። ይህንን ሐሳብ በሚገባ ለመግለጽ ነቢዩ ኢሳያስ ጠቅለል አድርጎ ያስቀመጠውን በመግለጽ እንዲህ ማለት እንችላለን “አባት ሆይ እዚህ ጦርነት አለ፣ ስልጣንን ያላግባብ መጠቀም እና ብዝበዛ አለ። ነገር ግን አንተ የእኛን መልካምነት እንደ ምትፈልግ እናውቃለን፣ ስለዚህ የአንተ ፈቃድ ይፈጸም ዘንድ እንማጸንሃለን! ሰይፋችንንም ወደ ማረሻ፣ ጦሮቻችንንም ወደ ማጭድ፣ እንዲቀየር አድርግልን፣ ማንም ሰው ሰይፉን በሌላው ላይ አያንሳ!” እግዚኣብሔር የሚፈልገው ሰላም ነውና።

እግዚአብሔር ክፉን በመልካም ይቀይራል

“አባታችን ሆይ!" የሚለው ጸሎት ኢየሱስ ለአብ ያለውን ዓይነት መላክም ፈቃድ በእኛም ልብ ውስጥ የሚለኩስ ጸሎት ነው፣ ዓለምን በፍቅር እንድንለወጥ የሚያነሳሳን የእሳት ነበልባል ነው። ይህንን ጸሎት የምንጸልየው እግዚአብሔር ክፉን በመልካም በማሸነፍ እውነታን መለወጥ እንደሚችል እናምናለን ብለን በማሰባችን የተነሳ ነው። በጣም ከባድ በሆነው የፈተና ሰዓት እንኳን ሳይቀር ራሳችንን ለእርሱ ታዛዥ ለማድረግ እና የእርሱ ፈቃድ የፈጸም ዘንድ ራሳችንን ለእርሱ በአደራ በመስጠት የምንጸልየው ጸሎት ነው። በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ኢየሱስ መከራ ውስጥ በነበረበት ወቅት ያደርገው ጸሎት በዚህ ሁኔታ የተከናወነ ጸሎት ነበር፡ “አባት ሆይ! ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ ውሰድ! ይሁን እንጂ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” (ሉቃስ 22፡42) በማለት የአባቱን ፈቃድ ፈጽሙዋል። “እግዚአብሔር ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን?  እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል። ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን? እግዚኣብሔር የሚወደን በዚሁ መልኩ ነው።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በመጋቢት 11/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደርጉት የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 July 2019, 14:16