ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለወጣቶች የብጹዕ ካርሎ አኩቲስን ሕይወት አስታወሱ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከተለያዩ የኢጣሊያ ከተሞች ወደ አሲዚ ከተማ መጥተው መንፈሳዊ ጉብኝታቸውን በማድረግ ላይ ለሚገኙት ወጣቶች በላኩት ቃለ ምዕዳናቸው ወጣቶቹ የብጹዕ ካርሎ አኩቲስን አብነት መከተል እንዳለባቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  አሳሰቡ።

የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው ካርሎ አኩቲስ፣ ወላጆቹ ለሥራ ፍለጋ ወደ ሎንደን ከተማ በሄዱበት በሚያዝያ 25 ቀን 1983 ዓ. ም. የተወለደ ሲሆን ቀጥሎም ወደ ሰሜን ኢጣሊያ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሚላን በመምጣት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ለክርስትና እምነቱ ባሳየዉ ጥልቅ ፍቅር የሚታወቅ አዳጊ ሕጻን ነው። በ15 ዓመት ዕድሜ ያረፈው ካርሎ አኩቲስ በዚህ ዕድሜው በኢንተር ኔት ድረ ገጽ አማካይ ለምዕመናን የወንጌል አገልግሎትን ያዳርስ እንደነበር እና የቅዱስ ቁርባንን ተዓምራት ይመሠክር እንደነበር ታውቋል። በሕይወት በኖረባቸው ዓመታት ወደ ሰማያዊው ክብር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ ቅዱስ ቁርባን እንደሆነ የገለጸ፣ እንዲሁም በሰዎች ስም የሚቀርብ የመቁጠሪያ ጸሎትን ያዘወትር እንደነበር ታውቋል። ሕጻን ካርሎ አኩቲስ በአጥንት ሕመም ምክንያት፣ ጥቅምት 2 ቀን 1999 ዓ. ም. ማረፉ ታውቋል።

ራስን ሆኖ መገኘት፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለወጣቶቹ በላኩት መልዕክት እንዳስረዱት ባሁኑ ጊዜ በወጣቶች ዘንድ በብዛት የሚዘወተረው የማሕበራዊ መገናኛ ጥቅም አሉታዊ ገጽታ ወጣቶች ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር በአካል እንዳይገናኙ ነጥሎአቸው እንደሚያስቀር ካስረዱ በኋላ የካርሎ አኩቲስን ከዚህ የተለየ እንደሆነ፣ የማሕበራዊ መገናኛ መሣሪያን ጥቅም በመረዳት ለወንጌል አገልግሎት ወይም ስርጭት ይገለገልበት እንደነበር ገልጸዋል። “ሕያው ክርስቶስ” በተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ “ብዙዎች ሲወለዱ የነበራቸውን ማንነት አጥተው ሌላ ሰው ሆነው ይሞታሉ” በማለት ብጹዕ ካርሎ አኩቲስ የተናገረው መጠቀሱን የካርሎ አኩትስ እናት ወይዘሮ አንቶኒያ ሳልዛኖ አስታውሰዋል። ልጃቸው ብጹዕ ካርሎ አኩቲስ በማሕበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች በመገዛት፣ የሙይጠቅሙ እና የማያንጹ ርዕሦችን በመከታተል ጊዜውን ማጥፋት አልፈለገም ብለዋል።

ቅዱስ ቁርባን እና ዘመናዊ ቲክኖሎጂ፣

የካርሎ አኩቲስ እናት ወይዘሮ አንቶኒያ ሳልዛኖ በማከልም ልጃቸው የዘመናዊ ማሕበራዊ መገናኛ መሣሪያዎች አጠቃቀምን በደንብ ያወቀ እና በማሕበራዊ መገናኛዎች አማካይነት ለቅዱስ ቁርባ ያለውን ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ ጥረት አድርጓል ብለዋል። ከሕይወት ታሪኩ ለመረዳት እንደሚቻለው ዘወትር መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ እንደሚገኝ፣ ቅዱስ ቁርባንን ከቆረበ በኋላ በመንበረ ታቦት ፊት ተንበርክኮ ጸሎት ያቀርብ እንደነበር ያስታወሱት እናቱ አሮጌ ኮምፒውተሩን በመጠቀም በአምስቱ አህጉራት ለሚገኙት፣ በብዙ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የቅዱስ ቁርባንን አውደ ትዕይንት ሊያቀርብ ችሏል ብለው ይህን መንገድ በመከተል የሕይወቱ ማዕከል የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች መመስከር ችሏል ብለዋል።  

የአጽም ዝውውር፣

በአሲዚ በሚገኝ የንግደት ሥፍራ የተቀመጠው የብጹዕ ካርሎ አጽም መጋቢት 27 እና 28 2011 ዓ. ም. ለምዕመናን የሚገለጥ መሆኑ ታውቋል። የብጹዕ ካርሎ አኩቲስ እናት ወይዘሮ አንቶኒያ ሳልሳኖ እንደገለጹት፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ መሠረት፣ የልጃቸው የብጹዕ ካርሎ አብነት በሌሎች ወጣቶች ልብ ውስጥ ገብቶ ሊያነሳሳ ይችላል ብለዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ስጋው እና ወ ደሙ በኩል ለመንፈሳዊ ሕይወቱ እድገት ብርታት እንደሆነለት ብጹዕ ካርሎ መናገሩን ወይዘሮ አንቶኒያ ሳልሳኖ ገልጸዋል።

የሕትመት ስራዎች፣

የብጹዕ ካርሎ አኩትስ ሕይወት ብዙዎችን የማሕበራዊ መገናኛ ተቋማትን ያነሳሳ መሆኑ ሲታወቅ ከእነዚህም መካከል በቫቲካን መገናኛ መምሪያ ስር የሚገኝ የፊልም ሥራ ክፍል መሆኑ ታውቋል። ይህ ክፍል ከዚህ በካርሎ አኩቲስ ሕይወት ዙሪያ ጥናታዊ ፊልሞችን የሠራ ሲሆን በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የቅዱስ ቁርባን ተዓምራቶችን የሚያሳይ ጥናታዊ ፊልምም ተዘጋጅት ለእይታ መቅረቡን የቫቲካን የፊልም ዝግጅትና መዝገብ ቤት አስታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
03 April 2019, 15:09