ቅዱስ አጎስጢኖስ “እውነትን በክርስቶስ ውስጥ ብቻ መፈለግ ይገባል!”

የአውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር በሚከተል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ዛሬ ነሐሴ 22/2010 ዓ.ም በላቲን ስረዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር ደንብ መሰረት የቅዱስ አጎስጢኖስ አመታዊ በዓል እየተከበረ ይገኛል። ቅዱስ አጎስጢኖስ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የኖረ ቅድሱ ቢሆንም፣ ነገር ግን እርሱ ጥሎ ያለፈው መልካም ምሳሌ በዛሬ ዘመን በሚገኙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እየተነጸባረቀ ይገኛል። የእርሱ ሕይወት በተፈጥሮ በረከቶች እና ከእግዚኣብሔር ጋር በግል በነበረው ግንኙነት ላይ መሰረቱን ያደረገ፣ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ከፍተኛ ደስታ እንዲኖረው የረዳው ተመክሮ ነው። በሕይወት ዘመኑ ከጻፋቸው በርካታ መጽሐፎች እንደ ምንረዳው ቅዱስ አጎስጢኖስ ‘እውነትን በክርስቶስ’ ውስጥ እንዴት መፈለግ እንደ ሚቻል አጽኖት በመስጠት አስተምሯል፣ በጹሑፎችም ውስጥ በሚገባ ገለጹዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቅዱስ አጎስጢኖስ ከልብ በመነጨ መልኩ እና በፍቅር በመሞላት እውነትን አጥብቆ ይፈለግ የነበረ ሰው በመሆኑ በዛሬው ዘመን እውነትን በመፈለግ ላይ የሚገኙ በጣም በርካታ ሰዎች በመኖራቸውም የተነሳ፣ የቅዱስ አጎስጢኖስ አስተምሕሮ እና አስተዋጾ በዛሬው ዘመናችን ውስጥ ሳይቀር በመነጸባረቅ ላይ የገኛል። ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላም እንኳን ሳይቀር “የቅድስ አጎስጢኖስ ኑዛዜ” በአሁኑ ዘመን ላሉ፣ ብዙ ጥያቄዎችን በሕይወታቸው ውስጥ በማንሳት ላይ የሚግኙ፣ በሕይወት ዘመናቸው ውስጥ በአእምሮዋቸው የሚመላለሱትን ጥያቄዎች መመለስ ላልቻሉ ሰዎች፣ በማመን እና ባለማመን አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው የሚገኙ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲፈትሹ፣ ጥያቄዎቻቸውንም በአግባቡ እንዲመልሱ ብርታት የሚሰጣቸው ወደ እውነት መንገድ የሚመራቸው ኑዛዜ በመሆኑ የተነሳ ወቅታዊ ያደርገዋል። ይህም የሚሆንበት ምክንያት “የቅዱስ አጎስጢኖስ ኑዛዜ” በሚል አርእስት ለንባብ የበቃው ቅዱስ አጎስጢኖስ ራሱ የጻፈው የሕይወት ተመክሮ “ከልብ ለልብ” የሚናገር መልእክቶችን ያዘለ በመሆኑ የተነሳ ነው።

ቅዱስ አጎስጢኖስ ለዛሬ ዘመን ወጣቶች ቅርብ ነው

በዛሬው እኛ በምንገኝበት ዘመን እየኖሩ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ዘመን አመጣሽ በሆኑ በተለያዩ ነገሮች በመነዳት እና በመወሰድ አጣብቂኝ ውስጥ እንደ ሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን እውነት የሆኑትን ነገሮች ለይተው ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት በማደርግ “እውነትን ፍለጋ” በመኳተን ላይ እንደ ሚገኙ የአደባባይ ምስጢር ነው። “ከቅዱስ አጎስጢኖስ ኑዛዜ” እንደ ምንረዳው እርሱ በሕይወቱ እውነትን ያለማቋረጥ፣ ተስፋ ሳይቆርጥ፣ በብርታት እና በክርስቶስ ብርሃን በመታገዝ እውነትን በሕየውቱ ውስጥ ፈልጎ እንዳገኘ ሁሉ፣ በአሁኑ ዘመን የሚኖሩ ወጣቶች እውነትን ያለምንም መታከት መፈለግ እንደ ሚገባቸው፣ እውነትን ፈልገው ካገኙ በኋላ ደግሞ ለእውነት ዘብ መቆም እንደ ሚኖርባቸው፣ እውነት ትቀጭጭ ይሆናል እንጂ ፈጽሞ እንደ ማትጠፋ በመረዳት በሕይወታቸው ውስጥ “እውነትን” ያለማቋረጥ እንዲፈልጉ ማበረታቻ ይሆናቸዋል።

ሁል ጊዜ ወደ ላይ መመልከት ያስፈልጋል

“ሁልጊዜም ቢሆን ተስፋ ሳትቆርጡ ወደ ላይ ተመልከቱ” በማለት ቅዱስ አጎስጢኖስ በሕይወቱ ዘመን ላገኛቸው ሰዎች ይመክር እንደ ነበረ የሚታወቅ ሲሆን ቅዱስ አጎስጢኖስ በሕይወቱ ‘እየዘመርክ ተራመድ’ የሚለው ሐረግ እርሱ በሕይወት ዘመን ጉዞ በመፈክርነት የሚጠቀምበት ሐረግ እንደ ሆነ ይታወሳል። በዚህም መሰረት ቅዱስ አጎስጢኖስ ይህንን ‘እየዘመርክ ተራመድ’ የሚለውን መፈክር እኛም እንድንጠቀም በመጋበዝ በፍጹም ወደ ኋላ እንዳንመለስ፣ ሁልጊዜ ራሳችንን በራሳችን በማዘጋጀት፣ ሁልጊዜም ለእግዚኣብሔር ድንቅ ሥራ ራሳችንን ክፍት በማደረግ፣ ልባችንን በላይ በሰማይ በሚገኘው በእግዚኣብሔር ዘንድ በማድረግ ወደ ፊት እንድንራመድ ይጋብዘናል፣ ያበረታታናል።

በመጨረሻም ቅዱስ አጎስጢኖስ በሕይወት ዘመኑ ያገኘው እና አሁን በዚህ ዘመን ለምንኖረው ለእኛ የሚመክረው ነገር ቢኖር “በሕይውት ዘመናችን ሁሉ ክርስቶስን ለመገናኘት መሞከር፣ ለሰው ልጆችን የልብ መሻት ሁሉ መልስ የሚሰጠው ክርስቶስ ብቻ መሆኑን” ተገንዝበን ሁልጊዜ ክርስቶስን እና ክርስቶስን ብቻ እንድንፈልግ ቅዱስ አጎስጢኖስ ከሕይወት ልምዱ በመነሳት የመክረናል።

28 August 2018, 09:51