ለአፈር ሳይንስ 100ኛ ዓመት ጉባኤ የተዘጋጀ መድረክ  ለአፈር ሳይንስ 100ኛ ዓመት ጉባኤ የተዘጋጀ መድረክ  

የአፈር ሳይንስ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል በጣሊያኗ ከተማ ፍሎረንስ እየተካሄደ ይገኛል

የአፈር ሳይንቲስቶች በጣሊያኗ የፍሎረንስ ከተማ በመሰብሰብ አፈር በምግብ ምርት፣ የአየር ንብረት ለውጥን በመቀነስ እና በብዝሀ ህይወት ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና በማሳየት፥ የተፈጥሮ እፅዋትን መለወጥ የሚያስከትለው ጉዳት እንዲሁም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ጦርነት በአፈር ጤና ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ በማጉላት ተወያይተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የአፈር ሳይንቲስቶች ለአካባቢያችን፣ ለእርሻ እና ለሰው ልጅ ሕይወት እጅግ አስፈላጊ አካል የሆነውን የአፈርን አመጣጥ እና የወደፊት እንክብካቤን ተገናኝተው በየጊዜው ትምህርታዊ ውይይት ያደርጋሉ። በዚህም መሰረት ወደ 1,500 የሚጠጉ ባለሙያዎች በጣሊያን ሃገር፣ ፍሎረንስ ከተማ ከግንቦት 11 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ የአፈር ሳይንስ 100ኛ ዓመት በሚከበርበት ጉባኤ ላይ ስለ የአፈር ሳይንስ እድገት እና የወደፊት ምኞቶች ለመወያየት ተሰባስበዋል።

በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ሳይንቲስት እና የግብርና ፕሮፌሰር የሆኑት አሌክስ ማክብራትኒ፣ የአፈርን በምግብ ምርት ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና ገልጸው፣ የተፈጥሮ እፅዋትን ለእርሻ ዓላማ ተብሎ መቀየር ጎጂ ውጤቶችን እንደሚያመጣ አስጠንቅቀዋል።

አቶ አሌክስ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ውሃ ወይም ንፋስ አፈር ላይ በሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ፣ የአፈር መሸርሸር በመፍጠር አፈርን ልናጣው እንችላለን፥ ምክንያቱም ይህ እንዳይከሰት የአፈርን መሸርሸር ሊከላከሉ የሚችሉ ሁሉንም የእፅዋት ሽፋን ስላስወገድን ነው። ይህ ሂደት አፈሩን የእጽዋት እድገትን በእጅጉ ወደሚጎዳው ወደ አሲዳማ እና ጨዋማ አፈር ሊቀይርው ይችላል” ብለዋል።

ጨዋማነት

ፕሮፌሰሩ በጉባኤው ላይ ተደጋግሞ ሲዳሰስ በነበረው የጨው ክምችት ጉዳይ ላይ በማብራራት፣ የግብርና ስራዎች ወደ አፈርነት የተቀየረውን ባዮማስ መጠን በመቀነሱ አፈር ውስጥ ያለው ካርቦን እንዲቀንስ አድርጓል ካሉ በኋላ፥ ይህ የካርቦን መጥፋት የካርቦን ዳይ ኦክሳይድ (CO2) መጠን እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያደርጋል፣ ይህ ደግሞ የዓለም ሙቀት መጨመርን ያባብሳል በማለት አስረድተዋል።

በማከልም “በአሁኑ ወቅት በአፈር ሳይንስ ውስጥ ካሉት ትልቅ ፈተናዎች አንዱ ካርቦንን ወደ አፈር ውስጥ እንዴት መመለስ እንደሚቻል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቅረፍ መሞከር ነው” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የአፈር እና የአየር ንብረት ለውጥ

የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የአፈር ሚና ለሳይንቲስቶች ዋነኛ ትኩረት ነው። አቶ አሌክስ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጹ፥ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የአየር ንብረት ለውጥን ጉዳይ ክጳጳሳዊ ሥራዎቻቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል አንዱ እንዳደረጉት እና በዚህ ጉዳይ ላይም ሐዋርያዊ አስተምህሮአቸው የሆነውን ‘ሃዋሪያዊ ማሳሰቢያ’ አውጥተዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ከአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም እና ሥነ ምግባራዊ ተፅዕኖ ያላቸውን እይታ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አሌክስ በፍሎረንሱ ጉባኤ ባደረጉት ወሳኝ ንግግር፣ ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ድርብ ባህሪ አንስተዋል። ይህንንም የበለጠ ሲያብራሩ፥ “ሰፊ የቋንቋ ሞዴሎች” የሚባሉ መኖራቸውን ጠቁመው፥ እነዚህ ሞዴሎች ሁልጊዜ ትክክል ባይሆኑም በተለይ ዋና ዋና ሃሳቦችን ብቻ ለሚያስቀምጡ ለውጭ አገር ተማሪዎች ጠቃሚ ነው” ካሉ በኋላ “እነዚህ መሳሪያዎች የቋንቋውን ጥራት ወይም ይዘት ሊያሻሽሉ ይችላሉ” ብለዋል። “ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ከዚህ የተለየ ማሽን ተኮር ሰው ሰራሽ አስተውሎት አለ” ሲሉ የቀጠሉት ፕሮፌሰሩ፥ ይህ መረጃን ብቻ እንጂ እውቀትን እንደማይጠቀም ገልጸዋል።

መረጃን በማከማቸት ማሽኖች ስለወደፊቱ ትንበያ ለመስጠት ይሞክራሉ፥ ለምሳሌ በአፈር ውስጥ ምን ያህል ካርቦን እንደሚገኝ እና ሌሎች የወደፊት የአፈር ሁኔታዎችን ሊተነብዩ ይችላሉ። “ሞዴሎቹ እራሳቸው በጣም የተወሳሰቡ ናቸው፥ በመሆኑም እነዚህ ሞዴሎች ከሰው ልጅ መረዳት በላይ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ሞራላዊ ስጋቶች

“አንዳንድ ሰዎች ውሎ አድሮ ማሽኖቹ ምንም ቢሆኑም ራሳቸውን ማሻሻል ስለሚችሉ እና ምናልባትም ከእኛ የበለጠ የመረዳት ደረጃ ስለሚኖራቸው የበለጠ ያሳስባቸዋል” ሲሉ የአንዳንድ ሰዎችን ስጋት ተናግረዋል።

ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ፕሮፌሰሩ ከእንደዚህ አይነት አካላት ጋር በምንጋራው ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ ስላለው ቦታ ያላቸውን ጥያቄ አጋርተዋል። “የእነዚህ አካላት ሥነ ምግባር ምን ሊሆን እንደሚችል ምንም ዓይነት ፅንሰ-ሀሳብ የለንም” ሲሉም አስጠንቅቋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም ያመጣው የሞራል ስጋቶች ሌላ ተጨማሪ የሞራል ጉዳይ አምጥቷል፥ ይሄም ቅዱስ አባታችን ሁሌ ስለሚናገሩለት የጦርነት ጉዳይ ነው።

ጦርነት በአፈር ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ

ጦርነት በአፈር ላይ ያለው ተጽእኖ ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ነው። ጦርነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፈር እና በእርሻ ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት አቶ አሌክስ ማክብራትኒ ሲገልጹ አሁንም ድረስ የአንደኛ ዓለም ጦርነት አሻራ አፈሩን ወደ ነበረበት እንዳይመለስ ያገደውን በአውሮፓ የሚገኘውን የፍላንደርስ ግዛት ውስጥ እየሰሩ ያሉትን የስራ ባልደረቦቻቸውን ጠቅሰዋል።

“ይህ አከባቢ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት አፈሩ በጣም ተጎድቷል፥ በመሆኑም ለማገገም ብዙ ጊዜ ወስዶበታል” በዚህ ሁኔታ ለማገገም ከአንድ መቶ ዓመት በላይ እንደወሰደበት ተነግሯል።

ጦርነት አፈርን ላልተወሰነ ጊዜ ይጎዳል፥ አንዳንድ ጥናቶች በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሚያስከትለውን መዘዝ ከአሁኑ መመልከት ጀምረዋል፥ በዓለም ላይ ካሉት ውድ “ጥቁር አፈር” ውስጥ ወደ 10 በመቶ የሚጠጋው እና በንጥረ-ነገሮች እና ረቂቅ ህዋሳት የበለፀገው ይህ የዩክሬን አፈር በአንድ ወቅት ውድ ሀብት የነበረ ሲሆን፥ አሁን ግን አደገኛ የሆነ የፈንጂ አከባቢ ሆኗል።

ማስተማር እና ስለ አፈር ያለውን ግብዛቤ ማሳደግ

አፈር በሁሉም የዓለማችን ክፍል አለ፥ በየጊዜው የሚለዋወጥ እና ለሰው ልጅ ህይወት እና ለፕላኔታችን ጥበቃ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ፕሮፌሰር አሌክስ አፈር ምን ያህል ጠቃሚ ሀብት እንደሆነ ማስተማር ስላለው ጠቀሜታ ሲናገሩ፥ ከዓለም የብዝሀ ሕይወት ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአፈር ውስጥ እንደሚኖር እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የባክቴሪያ እና የፈንገስ ዝርያዎች እንደሚኖሩ አስገራሚ ጥናታዊ መረጃ አጋርተዋል።

“አፈር ሁሉም ዕፅዋት እና ከባቢ አየር ተጣምረው ከሚይዙት ካርቦን የበለጠ ይይዛል” በማለት የብዝሃ ህይወት እና የአየር ንብረት ተግዳሮቶችን ለመፍታት አፈር ያለውን ወሳኝ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ፕሮፌሰሩ “ወደ ሰባት የሚያህሉ ዓለም አቀፍ የህልውና ፈተናዎች አሉ” ካሉ በኋላ፥ “እነዚህም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ዋስትና፣ የውሃ ዋስትና፣ የኢነርጂ ደህንነት፣ የሰው ልጅ ጤና፣ የብዝሀ ህይወት እና የአፈር ደህንነት የሚባሉት ናቸው” ብለዋል።

ፕሮፌሰር አሌክስ ማክብራትኒ በመጨረሻም “የሰው ልጆች ከአፈር ጋር ልዩ የሆነ የተፈጥሮ ግንኙነት እና የተፈጥሮ ቅርርብ አላቸው" በማለት፥ "የከተማ መስፋፋት የሰው ልጅ ከመሬት ጋር ያለውን ግንኙነት አቋርጠዋል፥ አሁን ላይ ከ 50 በመቶ በላይ የሚሆን ህዝብ በከተማ ውስጥ ይኖራል፥ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ ከአፈር ጋር ያለውን ተፈጥሯዊ ቁርኝት አራርቋል፥ በመሆኑም ይህ ከአፈር ጋር ያለው ልዩ ግንኙነት እንደገና ቢፈጠር ጥሩ ነበር፥ ይሄንን በጊዜ ሂደት እንደገና ለመገንባት መሞከር አለብን” ብለዋል።
 

21 May 2024, 16:09