በኢራቅ የደረሰው የቦንብ አደጋ በኢራቅ የደረሰው የቦንብ አደጋ  

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ በጠፋው የሰው ሕይወት ማዘናቸውን ገለጹ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ በቫቲካን ዋና ጸሕፈት ቤት አማካይነት ማክሰኞ ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ በላኩት የቴሌግራም መልእክት በባግዳድ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ለሞቱት ወገኖች ሀዘናቸውን በመግለጽ ኢራቅ ውስጥ እርቅ እንዲደረግ ያቀረቡትን አቤቱታ በድጋሚ ማደሳቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በባግዳድ አል-ውሃይት ገበያ ላይ በደረሰው ፍንዳታ የሰው ሕይወት መጥፋቱ የተገለጸ ሲሆን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በድርጊቱ እጅግ በጣም ማዘናቸውን በመልእክታቸው ያፋ አድርገዋል።

የቫቲካን ዋና ጸሐፊ በሆኑት በካርዲናል ፒኤትሮ ፓሮሊን በኩል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ይፋ ባደረጉት መልእክት በኢራቅ በሚገኘው የቫቲካን ኤንባሲ አባሳደር በሆኑት ሊቀ ጳጳስ ምትጃ ሌስኮቫር በኩል የተላከው የቴሌግራም መልእክት የቅዱስነታቸውን የሐዘን መግለጫ መልእክት ያካተተ ሲሆን በጥቃቱ “ለሞቱት ቤተሰቦች እና ወዳጆች ነፍሳቸውን ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ምህረት በአደራ እንሰጣለን” በማለት የመጽናናት መልእክት መላካቸው ተገልጿል።

በመጨረሻም የቴሌግራም መልዕክቱ ላይ እንደ ተገለጸው “ብፁዕነታቸው ኢራቅ ውስጥ ሰላምን እና እርቅ ለማጎልበት ይቻል ዘንድ እየተከናወነ የሚገኘውን ጥረት በማንኛውም የኃይል እርምጃ እንዳይቀለበስ ምንም ዓይነት የኃይል እርምጃ እንዳይወስድ የሚያደርግ ልባዊ ጸሎታቸውን ያድሳሉ” የሚል መልእክት ማሰተላለፋቸው ተገልጿል።

ሐምሌ 13/2013 ዓ.ም ማክሰኞ ዕለት በኢራቅ ኢል አል አድሃ በዓል በሚከበርበት ወቅት ሰሜናዊ የኢራቅ ዋና ከተማ ባግዳድ ውስጥ ባለው የገበያ ስፍራ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመው። ከአከባቢው የሚወጣው ዜና እንደ ሚያመልክተው ከሆነ በጥቃቱ ምክንያት 30 ሰዎች እንደሞቱ እና በደርዘን የሚቆጠሩ ደግሞ መቁሰላቸውን የሚያመልክት ሲሆን ከባለፉት ስድስት ወራት ወዲህ በባግዳድ ውስጥ የተፈጸመ እጅግ የከፋ ጥቃት እንደ ሆነም ተገልጿል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኢራቅ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ከየካቲት 26-29/2013 ዓ.ም 33ኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማደረግ ወደ ኢራቅ ተጉዘው እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን ይህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮ በሰባት አመት የርዕሰ ሊቃነ ጵጵስና ዘመናቸው ከጣሊያን ውጭ በኢራቅ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ጨምሮ 33 ሐዋርያዊ ጉብኝቶችን ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በእነዚህም ሐዋርያዊ ጉብኝቶች በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሚገኙት ከኬኒያ፣ ከሁጋንዳ እና ከመካከለኛው የአፍሪካ ሪፖብሊክ አንስቶ በኩባ፣ በአሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ በምስራቅ አውሮፓ እና በኤሽያ አህጉር በመጓዝ የሰላም እና የአንድነት መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል።

ቅዱስነታቸው በኢራቅ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ. ም. የሦስቱ ሐይማኖቶች ማለትም የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነቶች መሠረት እና የከለዳውያን ምድር ወደ ሆነው የኡር ግዛት ተጉዘው እንደ ነበረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው ወደ ኡር ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በሚገኙ የእምነት ተቋማት መካከል እንዲያድግ ጥረት በማድረግ ላይ ላሉት የጋራ ውይይቶች እና ወንድማማችነት ዓላማ ትልቅ ስፍራ የተሰጠው እንደ ነበረ መዘገባችን ይታወሳል። “ይህ የተቀደሰ ስፍራ፣ የእግዚአብሔር ሥራ ወደ ሆነው የእምነታችን መሠረት ተመልሰን እንድንመጣ አድርጎናል” በማለት ቅዱስነታቸው ለሦስቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።

ጉዞ ወደ ቤታችን

“የአብርሃም የትውልድ ስፍራ ወደ ሆነው ኡር ግዛት ተመልሰን መምጣታችን ወደ ቤታችን እንደመጣን ይቆጠራል” በማለት በወቅቱ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ሦስቱ ሐይማኖቶች የተገናኙበት ኡር በአገሩ ባሕል መሠረት የአብርሃም ቤት የሚገኝበት ስፍራ መሆኑ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ኡር አብርሃም ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥሪ የተቀበለው፣ ለጉዞ የተነነሳው እና ታሪክ የተቀየረበት ቦታ መሆኑን በወቅቱ የገለጹት ቅዱስነታቸው “እኛም የዚህ ጥሪ እና ጉዞ ፍሬዎች ነን” ማለታቸው ይታወሳል። እግዚአብሔር አብርሃምን ከዋከብትን እንዲቆጥር ማዘዙን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የእርሱ ተከታዮች እንደ ሰማዩ ከዋከብት ቁጥራቸው የበዛ እንደሚሆን ቃል መግባቱን አስታውሰው፣ ይህን በማድረጉ “እኛን ልጆቹን ተመልክቶናል” በአብርሃም ምድር የተሰበሰቡት የሦስቱ ሐይማኖቶች ተወካዮች በምድር ላይ ስንጓዝ ቀና ብለን ሰማይን መመልከት ይኖርብናል ማለታቸው ይታወሳል።

የሽብርተኝነት እና የጥላቻ ደመናዎች

“እግዚአብሔር መሐሪ ነው” በማለት በወቅቱ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በእግዚአብሔር ላይ የምንፈጽመው ትልቁ በደል “ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመጥላት ስሙን ማጥፋት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን ቅዱስነታቸው በሐይማኖት ምክንያት የሽብር ጥቃት ሲደርስ ምዕመናን በዝምታ መመልከት እንደሌለባቸው ገልጸው፣ አመጽ እና አክራሪነት የሐይማኖት ፍሬዎች አይደሉም በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ጥቁር ደመና እና አሸባሪነት፣ ጦርነት እና አመጽ የኢራቅ ሕዝብን ማስጨነቁ፣ ሁሉም ጎሳ እና የሐይማኖት ማኅበረሰቦች በስቃይ ላይ መሆናቸውን ያመለክታል በማለት በወቅቱ ተናግረው የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በማከልም በኢራቅ ውስጥ ከያዚዲ ጎሳ አባላት መካከል ብዙዎቹ መገደላቸውን፣ በባርነት መሸጣቸውን እና እምነታቸውን እንዲለውጡ መገደዳቸውን አስታውሰዋል።

በኢራቅ ውስጥ ለስደት እና ለምርኮ የተዳረጉት በሙሉ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው በሰላም እንዲመለሱ በማሰብ በወቅቱ ጸሎት ያደረጉት ቅዱስነታቸው በሁሉም አካባቢዎች የሕሊና እና የሐይማኖት ነጻነት እንዲከበር መጸለይ ያስፈልጋል በማለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ቅዱስነታቸው፣ እነዚህ መሠረታዊ መብቶች በመሆናቸው የተፈጠረልን ሰማይ ይህንን እንድናሰላስለው ነጻነትን ይሰጡናል ብለዋል።

በጨለማ ውስጥ የሚያበሩ ኮከቦች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎች በሰሜናዊው ኢራቅ ከፍተኛ ውድመት መፈጸማቸውን በወቅቱ መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ውድመት ቢደርስባቸውም አንዳንድ ከዋከብት ብርሃን መስጠትን ያላቋረጡ መሆኑን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በጦርነት የወደሙ የአምልኮ ሥፍራዎችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጊዶችን መልሶ ለመገንባት የተወሰደው የጋራ ጥረት መልካም ምሳሌ ነው ማለታቸው ይታወሳል። የአምልኮ ሥፍራዎች ተመልሰው አገልግሎት ሲጀምሩ ወደ ቅዱሳት ሥፍራዎች መንፈሳዊ ጉዞን ወይም ንግደት ማድረግ እንደሚያስፈልግ በወቅቱ በአደራ ጭምር የተናገሩት ቅዱስነታቸው የእምነታችን አባት የሆነው አብርሃም በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ለእግዚአብሔር መንበረ ታቦቶችን ሰርቶ ለጸሎት በማዘጋጀት የአምልኮ ሥፍራን ማዘጋጀቱን አስታውሰው፣ ይህ የጸሎት ሥፍራ ሰዎች የሚገናኙበት የሰላም ሥፍራ መሆኑን በወቅቱ አስረድተዋል።

21 July 2021, 11:48