የስንዴ ሰብል የስንዴ ሰብል  

አቶ ሉቤትኪን፣ ረሃብን ለማስወገድ ዘላቂነት ያለው የግብርና ዘዴ እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

የምግብ ሥርዓትን ለማሻሻል በሮም ከሐምሌ 19 - 21/2013 ዓ. ም. ሲካሄድ የቆየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ በመስከረም ወር በኒውዮርክ በሚደረግ የድርጅቱ ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ሃሳቦችን በመሰብሰብ መጠናቀቁ ታውቋል። የስብሰባው ተካፋዮች ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል የእርሻ ምርቶች ንግድን ከማስፋፋት ይልቅ ባህላዊ የእርሻ ሥርዓትን እና ተፈጥሮን በመንከባከብ ላይ ማትኮር ያስፈልጋል የሚለው ሃሳብ በስፋት መቅረቡ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት አዘጋጅነት በሮም ሲካሄድ የቆየው ስብሰባ ዋና ዓላማ በዓለማችን ውስጥ አስተማማኝ እና በቂ ምግብ በዘላቂነት ለማቅረብ ምቹ መድረኮችን ማዘጋጃት በሚለው ሃሳብ ላይ በመወያየት በመስከረም ወር በኒውዮርክ ሊካሄድ በታቀደው ስብሰባ ላይ ተግባራዊ የድርጊት መርሃ ግብሮችን ለማስተዋወቅ መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ እስከ አውሮፓዊያኑ 2050 ዓ. ም ድረስ ከዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ለሚሆን የዓለማችን ሕዝብ ሃምሳ ከመቶ የምግብ መጠን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በምግብ ምርት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን ማስከተሉን ያስታወሰው የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ስብሰባ የአካባቢ ጥብቃ እና እንክብካቤ አስፈላጊነትንም አንስቶ ተወያይቷል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ማርዮ ሉቤትኪን ለስብሰባው ተካፋዮች እንደገለጹት ተጨባጭ እና ተግባራዊ የሚሆኑ እቅዶችን በአስቸኳይ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለማችን ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በረሃብ እንደሚሰቃይ፣ ሦስት ቢሊዮን የሚሆነው ምግብ የሚያገኝ ቢሆንም ለጤናው ተስማሚ የሚሆን የተመጣጠነ ምግብ የማያገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት “ረሃብ በዓለማችን ውስጥ በሰው ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ስቃይ ሰብዓዊ መብቱን የሚጻረር አሳፋሪ ወንጀል ነው” ማለታቸውን የጠቀሱት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ክቡር አቶ ማርዮ ሉቤትኪን፣ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ዓ. ም ድረስ ረሃብን ከዓለማችን ለማጥፋት የተያዘለትን ዓላማ እግብ ለማድረስ ዘጠኝ ዓመታት ብቻ መቅረታቸውን አስታውሰዋል። አክለውም እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በኤኮኖሚው እና በአካባቢያዊ ባህሎች መካከል ያሉት ግንኙነቶች ከመዳበር በተጨማሪ በህዝባዊ እና የግል ተዋናዮች መካከል የጋራ ግንኙነት ሊኖር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

አጠቃላይ እይታ

ክቡር አቶ ማርዮ ሉቤትኪን በንግግራቸው የቅድመ ዝግጅቱ ስብሰባ ዓላማ ተግባራዊ የሚሆኑ ተጨባጭ እቅዶችን ይዞ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል የሰውን ልጅ የጤና ጽንሰ-ሀሳብ ማለትም የሰው እና የእንስሳት በሽታ አምጪ ተህዋስያንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ገጽታዎችን መመልከት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ አካባቢን ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ፣ የንግድ ተለዋዋጭነት ፣ የምርት ዘዴዎችን ፣ የነባር ሕዝቦች ባህሎችን ፣ ሲቪል ማህበረሰብን ፣ የህዝብ እና የግል ኢንቨስትመንቶችን ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ሌሎች አስቸኳይ ሁኔታዎች መመልከት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። 

ካርዲናል ታርክሰን፥ ባሕላዊ እና ተፈጥሮአዊ የእርሻ ዘዴዎች አስፈላጊነት

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን “ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በተግባር ሲገለገሉባቸው የቆዩ ባሕላዊ እና ተፈጥሮአዊ የእርሻ ዘዴዎችን መልሶ ለመጠቀም ማኅበራዊ ተቋማትን እንደገና ማዋቀር ያስፈልጋል ማለታቸውን” ፣ “በገጠራማው የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች የተለያዩ የእርሻ ዘዴዎችን በመጠቀም የምግብ እጥረትን በማስወገድ ከረሃብ የሚወጡበትን መንገድ ጠንቅቀው ያውቃሉ” ማለታቸውን እና “ከዚህ በፊት በምግብ አቅርቦት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እና ምርምሮች፣ ባሕላዊ እና ማኅበራዊ የተፈጥሮ የእርሻ ዘዴዎች መልካም ውጤቶችን ሲያስመዘግቡ የቆዩ ናቸው” ማለታቸውንም ክቡር አቶ ማርዮ ሉቤትኪን አስታውሰዋል።

የፍትሕ መጓደል የመጀመሪያ ሰለባዎች ሴቶች ናቸው

ዓለም አቀፍ የግብር እና ልማት ፈንድን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት ሴት ተካፋዮች በበኩላቸው ሴቶች ከማኅበረሰቡ ተገልለው በፍትህ መጓደል ምክንያት የመጀመሪያ ሰለባዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህን ለማስቀረት ዓለም አቀፍ የግብር እና ልማት ፈንድ በሴራሊዮን ውስጥ በገጠራማው አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶችን ሊሳተፉ የሚችሉ የተለያዩ ፕሮጄክቶች መዘርጋታቸውን አስረድተዋል። በዓለማችን ውስጥ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ እና ግማሽ ከመቶ የሚሆነውን የዓለም የሠራተኛውን ኃይል የሚወክሉ፣ በቁጥር 1. 7 ቢሊዮን ሴቶች እና ልጃ ገረዶች በድህነት ሕይወት ውስጥ በረሃብ የሚሰቃዩ መሆናቸው ተገልጿል።

የሕፃናት እና የወጣቶች እንክብካቤ አስፈላጊነት     

ባሕላዊ የምግብ ሥርዓትን በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳሰበው ስብሰባው የሕጻናትን እና የወጣቶችን የአመጋገብ ስልት ለማሻሻል ተመጣጣኝ ምግቦችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ አሳስቦ፣ ይህ ካልተደረገ ሕጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት እድገታቸው በመቃወስ ለሞት የሚዳረጉ መሆናቸውን አመልክቷል።

ከአፍሪካ አህጉር የቀረበ አስተያየት

አህጉራቸው እ. አ. አ እስከ 2063 ዓ. ም ድረስ ተግባራዊ ለማድረግ የወጠኗቸው አምስት የተግባር መርሃ ግብሮች መኖራቸውን የገለጹት የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፖል ካጋሜ ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፣ በትምህርት ቤት የመመገቢያ ፕሮግራሞች ላይ ያተኮሩ የምግብ ፖሊሲዎችን መከተል፣  የአካባቢ ገበያን እና የምግብ አቅርቦት ሰንሰለቶችን መደገፍ፣ የግብርና ፋይናንስ ወጪን ወደ 20 በመቶ ማሳደግ፣ የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ማህበራትን ማበረታታት እና ለሴቶች የግብርና ምርቶች ተደራሽነት ማረጋገጥ እና በመጨረሻም የማህበራዊ ዋስትና ፕሮግራሞችን ማስፋፋት እና በአየር ንብረት ለውጥ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶች ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

29 July 2021, 16:40