የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤት በወረሩበት ወቅት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን የአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤት በወረሩበት ወቅት 

ቤተክርስቲያን በአሜሪካ ምክር ቤት ለተደረገው ወረራ አስተያየቷን ሰጠች

የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ታኅሳስ 28/2013 ዓ. ም. የአሜሪካ ምክር ቤትን ጥሰው በመግባታቸው ምክንያት በጸጥታ አስከባሪዎች በተሰነዘረ አጸፋ የጠፋው የሰው ሕይወት መጨመሩ ታውቋል። ተሰናባቹ ፕሬዚደትን ዶናልድ ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት የምርጫ ውጤት ሐሰት መሆኑን አሳውቀው፣ ደጋፊዎቻቸው ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ በሆነው የካፒቶል ሒል ግዙፉ ህንጻ ላይ ወረራን ባካሄዱበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት የጆ ባይደን የምርጫ አሸናፊነትን ለማጽደቅ ተሰብስበው እንደነበር ታውቋል። የምክር ቤቱ አባላት ከጸጥታ አስከባሪዎች በተሰጣቸው ማሳሰቢያ መሠረት ከምክር ቤቱ ሕንጻ ለጉዳት ሳይጋለጡ እንዲወጡ መደረጋቸው ታውቋል። ሰልፈኞቹ የምክር ቤቱን ሕንጻ ጥሰው በመግባታቸው ድርጊቱ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ታውቋል። በዚህ ወቅት ከአንድ የምክር ቤቱ ሕንጻ ደህንነት ጠባቂ በኩል በተሰነዘረው ጥቃት የአንዲት ሴት ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ የሌሎች ሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ 13 ሰዎች መቁሰላቸው እና 52 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል። በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ የከተማይቱ ከንቲባ ጆ ባይደን ቃለ መሐላ እስከሚፈጽሙበት ዕለት የሚቆይ የሁለት ሳምንት የሰዓት እላፊ አዋጅ ማወጃቸው ታውቋል። የተወካዮች ምክር ቤት የአሪዞና ግዛት የምርጫ ውጤት ውድቅ ካደረገ በኋላ ምክር ቢርቱ በማይክ ፔንስ መሪነት ከእያንዳንዱ መንግሥታዊ ክልሎች የቀረቡ የምርጫ ውጤቶችን ለማረጋገጥ ስብሰባ መጥራቱ ታውቋል። ከማላኒያ ዋይት ሃውስ ቃል አቃባይ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱ በርካታ የቀድሞ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን እየለቀቁ መሰናበታቸው ታውቋል። በሌላ ወገን በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኝ የአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ የተካሄደውን ወረራ የአውሮፓ ሕብረት አገራት መሪዎች የተቃወሙት ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት አማኑኤል ማክሮን፣ የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዚደንት ቮን ዴን ሊን እና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ይገኙባቸዋል። የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚደንት ክቡር ዳቪድ ሶሳሊ በበኩላቸው “በአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤት የተካሄደውን ወረራ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ የማይፋቅ ጥቁር አሻራ ያረፈበት ነው” ብለዋል።

ከሎሳንጀልስም እንደዚሁ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎሜዝ ክስተቱን የተቃወሙ መላው የጉባኤው አባላትን በመወከል ባስተላለፉት መልዕክት “ይህ ድርግት ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ የማስረከብ ባሕላችንን የሚቃረን፣ ማንነታችንንም የማይገልጽ ተግባር ነው” ብለው፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሕዝቡን በጥበብ ወደ እውነተኛ አገር ወዳድነት መንፈስ እንድትመራ ጠይቀዋል። የዋሽንግተን ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ዊልተን ግሬጎሪ በበኩላቸው አገሪቱ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ወደ መረጋጋት እንድትደርስ መጸለይ ያስፈልጋል ብለው፣ በአሜሪካ መንግሥት ዋና መቀመጫ የተካሄደውን ወረራ ተቃውመውታል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአገራቸው የመለያየት መንፈስ መታየቱን ገልጸው፣ በአገሪቱ አመጽን እና ጥላቻን የሚቀሰቅሱት በሙሉ ሃላፊነትን መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል። አክለውም ለአገራቸው ታላቅ ክብርን በመስጠት ባቀረቡት መልዕክታቸው በአገራቸው ፖለቲካ ሂደት በሰላማዊ መንገድ ውይይቶችን በማካሄድ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል ብለዋል። ለአገራቸው ጸጥታ እና የመንግሥት ባለስልጣናትን ባስታወሱበት ጸሎታቸው፣ ለመንግሥት ሰራተኞች፣ ለሰልፈኞች እና ጸጥታ አስከባሪዎች በጸሎታቸው አስታውሰዋል። በግርግሩ የቆሰሉት መኖራቸውን እና የንብረት መውደም መኖሩን ገልጸው፣ የጋራ ጥቅምን በሚያስከብር በአገራቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመተባበር በኅብረት መቆም ያስፈልጋል ብለዋል። የቺካጎ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ብሌዝ ዮሴፍ ኩፒች፣ በቲዊተር መገናኛ በኩል ባስተላለፉት መልዕክታቸው “ድርጊቱ አሳፋሪ ነው” ብለው፣ እግዚአብሔር አሜሪካዊያንን በፍቅሩ እንዲያስታውሳቸው፣ ለፖለቲካ መቃቃር ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ ተመኝተው፣ የአሜሪካን የዴሞክራሲ ሥርዓት ባሕል በመከተል፣ ተመራጭ የፖለቲካ መሪዎችም መልካም የሆኑ ምክረ ሃሳቦችን በመቀበል፣ ቃል የገቡለትን የአገራቸውን ሕገ መንግሥት ከአደጋ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የሰላም ኮሚሺን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ጆኒ ዞኮቪች በአሜሪካ መንግሥት የምርጫ ቦርድ ያካሄደው የቆጠራ ሂደት ለፖለቲከኞች፣ ለመገናኛ ተቋማት፣ ለቤተሰብ እና ለሌሎችም ተቋማትም የውድቀት ምልክት መሆኑን አስታውቀው፣ በብዙ ሰዎች መካከል የጠላትነትን እና የልዩነት ስሜትን በመፍጠር ለብዙዎችም ከሥራ ለመወገድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። የሰላም ኮሚሺን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ጆኒ ዞኮቪች በማከልም “ተሰናባቹን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን ላለፉት አራት ዓመታት በሥልጣን ያቆዩቱት፣ በአገሪቱ ውስጥ መጥፎ ትዝታዎች እንዲመዘገቡ ያደረጉት፣ በአሜሪካ መንግሥት መቀመጫ በሆነው በካፒቶል ሒል ህንጻ ላይ ወረራ እንዲካሄድ ያደረጉት ኃላፊነትን ካለመወጣት የተደረገ አሳዛኝ ክስተት ነው” ብለዋል።

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ስጋት

በመጨረሻዎቹ ወራት ውስጥ በሰሜን አሜሪካ በታዩት ክስተቶች የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ደስተኛ አለመሆኑን ጽ/ቤቱ ገልጿል። በአገሪቱ በመጨረሽዎቹ ዓመታት የታዩት ፋፋይ የፖለቲካ አካሄዶች በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ልዩነቶች እንዲስፋፉ ዕድል ማመቻቸቱን የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ ክቡር ያን ሳውካ ገልጸው፣ የግጭት ቀስቃሾች ለውይይት እንዲቀርቡ እና ሁሉም ወገን ሃላፊነት እንዲሰማው ጠይቀዋል። በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አገሪቱ የምትመራበትን ምክር እና ኃይል በመጨመር እንዲተባበሩ በጸሎት እንጠይቃለን ብለው፣ አገሪቱ ከገባበት የፖለቲካ ችግር ወጥታ ወደ ሰላም እና እርቅ ጎዳና እንድትመለስ ያላቸውን ፍላጎት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ ክቡር ያን ሳውካ አስታውቀዋል።                                                      

08 January 2021, 16:21