በሱዳን ከሚገኙ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን መካከል ጥቂቶቹ፤ በሱዳን ከሚገኙ የትምህርተ ክርስቶስ መምህራን መካከል ጥቂቶቹ፤  

በሱዳን ሕገ መንግሥት፣ የክርስትና ትምህርቶችን ማስተማር የሚፈቅድ ሕግ እንዲጸድቅ ጥያቄ ቀረበ።

ባሁኑ ጊዜ የሱዳን ሽግግር መንግሥት እያደረገ ያለውን በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥን ተከትሎ፣ በሱዳን የሚገኙ ክርስቲያኖች በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የክርስትና እምነት ለማስተማር የሚፈቅድ ሕግ እንዲጸድቅ መጠየቃቸው ታውቋል። የሱዳን ሽግግር መንግሥት የሞት ቅጣት ፍርድን ጨምሮ በርካታ ከበድ ያሉ ቅጣቶችን የሚያስቀር አዳዲስ ሕጎችን በማጽደቅ ላይ መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

የሱዳን ሽግግር መንግሥት ከዚህ በፊት በነበረው ሕገ መንግሥት ላይ የሚያደርጋቸው ማሻሻያዎች በአገሪቱ ተስፋፍቶ የሚገኘውን የእስልምና እምነት የበላይነት የሚያስቀር ነው ተብሏል። በአገሪቱ እየተደረገ ያለው ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ፣ ለሰላሳ ዓመታት ሱዳንን በአምባ ገነንነት የመሩት የቀድሞ ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ መሆኑ ታውቋል። በሱዳን የሽግግር መንግሥ ፍትህ ሚኒስቴር በኩል ቅዳሜ ሐምሌ 4/2012 ዓ. ም. ይፋ የሆነው ሕገ መንግሥታዊ ተሻሽሎ፣ በሱዳን ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ከእስልምና እምነት ትምህርት ጎን ለጎን የክርስትና እምነትንም ለማስተማር የሚያስችል ሕግ አለመካከቱ በርካታ ክርስቲያንችን ያስቆጣቸው መሆኑ ታውቋል።

የሱዳን ሽግግር መንግሥት ከአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ ከሰረዟቸው ከባድ ቅጣቶች መካከል አንዱ የእስልምና እምነትን በሚተው ሰዎች ላይ የሚጣል የሞት ቅጣት ፍርድ መሆኑ ታውቋል። የሕግ ማሻሻያው በተጨማሪም የሰዎች ግርፋትን ያስቀረ ሲሆን፣ የሕዝቡን ሰላም በሚያውክ፣ የሙስሊም እምነት ተከታዮች ባልሆኑት ላይ የተጣለ የአልኮል መጠጦች እገዳንም ያነሳ መሆኑ ታውቋል። በሱዳን የሽግግር መንግሥት የፍትህ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ናስርዲን አብዱልባሪ፣ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ የሽግግር መንግሥታቸው አሁንም በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን አስታውቀው፣ የሐይማኖት ነጻነትን፣ የዜግነት እኩልነትን እና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር በሚያስችሉ ሕጎች ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የሴቶችን መብት በተመለከተ አዲስ የተሻሻለው ሕገ መንግሥት የሴቶች ግርዛት የሚከለክል፣ ረጅም ጉዞን ለማድረግ ሲፈልጉ ከባል ፈቃድ ሳያሻቸው ከልጆቻቸው ጋር መጓዝን የሚፈቅድ መሆኑን አቶ ናስርዲን አብዱልባሪ በመግለጫቸው ገልጸዋል። በማከልም የዜጎችን እኩልነት የሚጻረር፣ በዜጎች መካከል ልዩነትን የሚያንጸባርቅ ማንኛውም ዓላማ የሱዳናዊያንን ሰብዓዊ መብት የሚጻረር በመሆኑ በሽግግር መንግሥታቸው ውስጥ ተቀባይነት የለውም መሆኑን ገልጸዋል።     

የክርስትና እምነትን ለማስተማር የሚያስችል ሕግ አለመካከቱ በርካታ የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን ያስቆጣችው ቢሆንም፣ የሽግግር መንግሥቱ ባለፈው የሰኔ ወር በምሑራን በኩል የቀረቡትን አስተያየቶች ተቀብሎ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። በሱዳን የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ውስጥ ብቸኛዋ ክርስቲያን ተወካይ፣ ራጃ ኒኮላ ኤይሳ አብደል ማሲ፣ ከሌሎች የሥራ ተባባሪዎቻቸው ጋር ሆነው በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ መሆኑ ታውቋል። የሕግ ባለ ሞያ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑት አብደል ማሲ፣ አስራ አንድ አባላት በሚገኙበት የሱዳን ሽግግር መንግሥት፣ በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ እንዲሠሩ ተብለው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ወስጥ መመረጣቸው ይታወሳል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 2019 ዓ. ም. በኦማር አልበሽር መንግሥት ላይ በተነሳው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በርካታ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄዎቻቸውን ይዘው ወደ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል። የደቡብ ሱዳን መገንጠልን ተከትሎ፣ የቀድሞ የሱዳን ፕሬዚደንት አቶ ኦማር አልበሽር በሰሜን ሱዳን እስላማዊ መንግሥ ለማቋቋም፣ እስላማዊ ባሕልን እና የአረብኛ ቋንቋን ብሔራዊ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። በሰሜን ሱዳን የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች በአገሪቱ የሚገኙ በርካታ ቤተክርስቲያኖች መውደማቸውን ወይም መወረሳቸውን እና ጥቂት መንፈሳዊ መጽሐፍት ብቻ ቀርተው ሌሎች መውደማቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

በሰሜን ሱዳን ከሚገኝ አርባ ሚሊዮን ነዋሪ ሕዝብ መካከል ሦስት በመቶ የሚሆነው የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኑን መረጃዎች ቢያመለክቱም በአገሪቱ የሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ግን የክርስቲያን ቁጥር ከዚህ እጅግ እንደሚበልጥ መግለጻቸው ታውቋል።       

14 July 2020, 18:16