"በሰዎች መካከል እርቅ እና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ" (ማቴ. 5፡9) "በሰዎች መካከል እርቅ እና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉ" (ማቴ. 5፡9) 

“ቤተሰባችን”፣ ቤተሰብ ሰላም እና ጸጥታን በማስከበር የሚጫወተው ሚና።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት አንባቢዎቻችን በዛሬው ጽሑፋችን “ቤተሰብ ሰላም እና ጸጥታን በማስከበር የሚጫወተው ሚና” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን፥

የቤተሰብ አባላት ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወትን ወደ መልካም አቅጣጫ በመምራት፣ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው። ቤተሰብ ይህን ሃላፊነት ለመወጣት፣ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወትን ወደ መልካም አቅጣጫ ለመምራት የሚያግዙ የተለያዩ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶች አሉት። ሰላማዊ እና የተሟላ ማኅበራዊ ሕይወት መኖር ማለት እያንዳንዱ የማኅበረሰብ አባል የዘር ወይም የቆዳ ቀለም፣ የጾታ እና የሐይማኖት ልዩነት ሳይደረግበት፣ ሰብዓዊ መብቱ ተከብሮለት ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እኩል የመጠቀም መብትንም ያካትታል።   

ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ለውጦች የሚታዩበት፣ ድህነት እና የኑሮ አለመመጣጠን የሚታይበት፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ሕዝቦች ለአደጋ የተጋለጡበት፣ በድህነት እና በበሽታ ምክንያት ሰዎች ከማኅበራዊ ሕይወት እየተገለሉ የመጡበት ዘመን ነው። ይህ በሆነበት ዘመን የቤተሰብ ሚና ምን መሆነ አለበት የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አስፈላጊ ነው።

ከዓመታት በፊት በዓለማችን ውስጥ በመንግሥታት መካከል የሚደረጉ ግጭቶች እና ጦርነቶች እየቀነሱ መጥተዋል። ይህ ማለት ግጭቶች እና አመጾች ጠፍተዋል ማለት አይደለም። በአገሮች ወይም በመንግሥታት መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች እና አመጾች ይቀንሱ እንጂ በሌላ ወገን በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ ወንድም እና እህት ሕዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች እና አመጾች፣ በዚህም ምክንያት የበርካታ ንጹሃን ሰዎች ሕይወት መጥፋት እንዲሁም የንብረት መውደም ሲከሰት እንመለከታለን። በአንድ መንደር ውስጥ ሰላም ሲደፈርስ፣ ማሕበራዊ ሕይወት እንቅፋት ሲገጥመው የቤተሰብ ሚና ምን ሊሆን ይገባል የሚለውን መመልከት መልካም ይሆናል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀንን በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የካቲት ወር 1994 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በጻፉት መልዕክታቸው በመበልጸግ ላይ ለሚገኝ ዓለማችን ቤተሰብ ሊያበረክት የሚችለው ቀጥታ ተሳታፊ በመሆን ሳይሆን ለውጡ ትክክለኛ መንገድን የተከተል እንዲሆን ማድረግ ነው ብለው፣ ይህን እገዛ ማድረግ የሚችሉት    

በፍቅር እየኖሩ የፍቅር ስልጣኔን በማበረታታት ነው ብለዋል። በዚህ ሂደት የቤተሰብ ተግባር ማኅበረሰብን ፍቅር በማስተማር እንደሆነ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በሕዝቦች መካከል በተግባር የሚገለጽ ፍቅር ለማኅበራዊ እድገት እና ብልጽግና የሚያበረክተው እገዛ ከፍተኛ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል።

ከሁሉም በላይ ራስን በፍቅር እና በመልካም ስነ ምግባር ማነጽ ለትክክለኛ እና እውነተኛ ብልጽግና መሠረት እንደሆነ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አስገንዝበዋል። ቤተሰብ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን በማሳደግ እና በማስተማር በማኅበረሰብ መካከል የሚፈጠሩ ችግሮችን፣ አለመግባባቶችን እና አመጾችን ማስወገድ ይችላል። ቤተሰብ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን የማሳደግ እና የማስተማር ኃላፊነት አለበት ሲባል ኃላፊነቱም ከሁሉ በላይ እርስ በእርስ በመደማመጥ፣ ይቅርታን እና እርቅን እንዲሁም ሰላምን መመሪያው ሲያደርግ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል። “ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ፍቅር ያቀረበውን ዝርዝር “ሁሉን” በሚሉ አራት ስንኞች ያጠቃልላል። ፍቅር ሁሉን ይታገሳል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። እዚህ ላይ፣ የሚያሰጋውን ነገር ሁሉ መቋቋም የሚችለውን የፍቅር ጸረ ባሕላዊ ኃይል እናያለን።

አንደኛው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው፣ ፍቅር ሁሉን ነገር ይታገሳል። ይህም ክፋትን መቋቋም ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ አንደበትን ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው። ግሡ ከሌላው ሰው በደል ጋር በተያያዘ “የራስን ሰላም መጠበቅ” ነው ሊባል ይችላል። ፍርድ ከመስጠት መቆጠብን፣ ብርቱ እና ጨካኝ የውግዘት ስሜት መቆጣጠርን ያመለክታል። አትፍረዱ፣ አይፈረድባችሁም (ሉቃ. 6:37) በተለምዶ አንደበታችንን ከምንጠቀምበት ሁኔታ በተቃራኒ፣ የእግዚአብሔር ቃል “ወንድሞች እና እህቶች ሆይ፣ እርስ በእርሳችሁ አትወነጃጅሉ ይለናል። (ያዕ. 4:11) ሌላውን ሰው መወንጀል፣ ራሳችንን ንጹሕ የማድረጊያ እና ስለምናደርሰው ጉዳት ግድ ሳይኖረን ቅሬታን እና ቅናትን መተንፈሻ መንገድ ይሆናል። ሐሜት ኃጢአት መሆኑን ብዙውን ጊዜ እንዘንጋለን። የሌላውን ሰው መልካም ስም የሚጎዳ እና ያንን ስም ማደስ የማያስችል ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመ ከባድ በደል ይሆናል። (ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ ቁ. 110 እና 111)

እያንዳንዱ ቤተሰብ የሚገኝበትን አካባቢ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች በመከተል፣ ከልዩ ልዩ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት ጋር በመተባበር በሕዝቦች መካከል ሰላም እና ጸጥታ እንዲሰፍን በማድረግ ከፍተኛ ሚናን ሊጫወት ይችላል።

ዮሐንስ መኰንን።      

25 July 2020, 16:49