ከዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች አንዱ፤ ከዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች አንዱ፤  

"ቤተሰባችን"፥ በልጆች መልካም አስተዳደግ የወላጆች ሃላፊነት።

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን፣ በዚህ ዝግጅት “ወላጆች በልጆቻቸው መልካም አስተዳደግ ላይ ያላቸውን ሃላፊነት” የሚመለከት አጭር ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን።

ወላጆች የልጆቻቸውን ሕይወት ወደ መልካም ደረጃ ላይ ለማድረስ ትልቅ ድርሻ እንዳለባቸው ይታወቃል። ሃላፊነታቸው ለልጆቻቸው ከሚያሟሉት ቁሳዊ ፍላጎት እስከ ስነ ልቦናዊ ዕድገት ድረስ የሚደረገውን ዕርዳታ ያጠቃልላል። በተለይም የአዳጊ ልጆች የስነ ምግባር እድገትን ተከታትሎ አስፈላጊውን አቅጣጫን እንዲይዝ ማድረግ ቀላል ሃላፊነት አይደለም። ልጆች ያለ ወላጅ ቤተሰብ፣ ያለ አሳዳጊ ወይም ያለ አስተማሪ የሚያድጉ ከሆነ ሕይታቸው ጥሩ መሠረት ሊኖረው አይችልም። ምክንያቱም ስነ ምግባርን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚችሉ በርካታ ገጠመኞች እና ልማዶች በመኖራቸው ነው። የዘመናችን ልጆች ስነ ምግባር ፈተና ውስጥ ከጣሉት አንዱ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። የመገናኛ ቴክኖሎጂ ውጤቶች ማህበራዊ ግንኙነቶችን እንድናሳድግ እና የተለያዩ ዕውቀቶችን እንድንቀስም በማድረግ ከፍተኛ ጥቅም አስገኝቶልናል። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ፈጣን የሃሳብ፣ የእምነት፣ የእውቀት እና የባሕል ልውውጦችን ማድረግ ችለናል።  

ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች የተለያየ ዓላማ ወይም አቋም፣ ምኞት፣ እምነት፣ ባሕል እና ቋንቋ ካላቸው በርካታ ሰዎች ጋር እንድንገናኝ ሰፊ መድረክ መፍጠራቸውን መዘንጋት የለብንም። ከሁሉም በላይ ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶችን የሚጠቀሙት ወይም የሚገለገሉት በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ዘመናዊ የመገናኛ መንገዶች ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ ከሚሰጡት ከፍተኛ ጥቅም በተጨማሪ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። ስለዚህ ወላጆች የመገናኛ መሣሪያዎች አጠቃቀም ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ድጋፍ ካልሰጧቸው ልጆች ለተለያዩ የስነ ምግባር መቃወስ ሊጋለጡ ይችላሉ። የመገናኛ ብዙሃን ከተጠቃሚዎች መካከል አንዳንዶቹን ንቁ ተጠቃሚዎች ከማድረግ ይልቅ የሚሰሙትን እና የሚያዩትን በዝምታ እንዲቀበሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2496)

ልጆችን በነጻነት ማሳደግ መልካም እና አስፈላጊ ቢሆንም በትክክለኛው መንገድ ካልሆነ ጉዳትን ሊያስከትል ይችላል። “የግብረ ገብ ትምህርት በሐሳብ፣ በማበረታቻ፣ በተግባራዊ ልምድ፣ በቅስቀሳ፣ በሽልማት፣ በምሳሌ፣ በምክር፣ በውይይት እና ነገሮችን የምናከናውናቸውን መንገዶች ያለመታከት በማጤን ነጻነትን ከማዳበር ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህ ሁሉ በቀጥታ መልካም ነገርን ወደ ማድረግ የሚመሩንን የተረጋጉ ውስጣዊ መርሆች ለማዳበር የሚረዱ ናቸው። ጥሩነት ጽኑ ውስጣዊ የአሰራር መርሆ እና እምነት ነው። ስለዚህ ጥሩ ሕይወት ነጻነትን ይገነባል፣ ያጠነክራል፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ የጸረ ኅብረተሰብ ዝንባሌ ተገዥዎች እንዳንሆን ያደርገናል። ምክንያቱም ሰብዓዊ ክብር ራሱ እያንዳንዳችን ከውስጥ በመነጨ እና በተቀሰቀሰ ግላዊ መንገድ በማስተዋል ነጻ ምርጫን ይጠይቃል” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክራቸውን አካፍለዋል። (“ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” ምዕ. 7፣ ቁ. 267)     

ወላጆች ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው ሲባል ኃላፊነታቸውንም የሚመሰክሩት ከሁሉ በፊት ገርነትን፣ ይቅርታን፣ አክብሮትን፣ አመኔታን እና ከራስ ወዳድነት የነጻ አገልግሎትን መመሪያ አድርጎ የሚኖር ቤተሰብ ሲመሰረት ነው። ቤት፣ ምግባራትን ለማስተማር የተመቸ ሥፍራ ነው። ይህ ትምህርት የእውነተኛ ነጻነት ቅድመ ሁኔታዎች የሆኑትን ራስን የመካድ፣ ቅን የሆነ ፍርድን የመስጠት እና የመቆጣጠር ብቃትን ይጠይቃል። ወላጆች ልጆቻቸው ሰብዓዊ ሕብረተሰብን ከሚያውኩ አስጊ እና አዋራጅ ነገሮች የሚርቁበትን መንገድ ማስተማር አለባቸው። (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2221 – 2224)  

ሕብረተሰብን ከሚያውኩ፣ ለማሕበራዊ ጸጥታ አስጊ ከሚባሉ ማሕበራዊ ቀውሶች መካከል አንዱ የሰላም መደፍረስ ነው። ሰላም ለሰብዓዊ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ፍጥረት የሚሻው የሕይወት መሠረት እና ዋስትና ነው። የሰው ልጆች ሰላም ካልተከበረ፣ በነጻነት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ እና የመሥራት ነጻነት ካልተከበረ፣ ለዚህም ብርቱ ጥረት ካልተደረገልት ሰላምን በምድራችን ማንገሥ አዳጋች ይሆናል። ሰላም ሊገኝ የሚችለው እያንዳንዱ ሰው በአስተሳሰቡ፣ በንግግሩ እና በሥራው ትክክለኛነቱ የተረጋገጠለትን ተግባር ሲያከናውን ነው። ንግግራችን እና ሥራችን ሰላምን የተላበሰ፣ ፍቅርን እና አንድነትን መሠረት ያደረገ እንጂ ጥላቻን የሚቀሰቅስ፣ ልባችንም ምህረትን እና እርቅን የሚያደርግ እንጂ በቀልን የሚመኝ መሆን የለበትም። “በሰዎች መካከል እርቅ እና ሰላምን የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ ደስ ይበላቸው” (ማቴ. 5:9)። 

በልጆች መልካም አስተዳደግ ስለ ወላጆችን ሃላፊነት ስንናገር፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ስለ ሰላም አስፈላጊነት የማስተማር፣ በመልካም ሥነ ምግባር የማነጽ፣ የመምከር፣ የመገሰጽ፣ በመልካም ሥነ ምግባር እንዲያድጉ የማድረግ ግዴታ አለባቸው። ይህን የሚያደርጉት ከሁሉ አስቀድሞ ራስን የሰላም መሣሪያ እና ምሳሌ በመሆን ነው።

ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

04 July 2020, 20:24