ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በዋሽንግተን ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ሲደርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ አድረገው ታይተዋል። ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በዋሽንግተን ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ሲደርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ አድረገው ታይተዋል። 

የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአገራቸው ፍትህ እና ጸጥታ እንዲሰፍን ጠየቁ።

ባለፈው ሳምንት በሰሜን አሜሪካ፣ ሚኒያፖሊስ ግዛት ውስጥ፣ ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ አፍሮ-አሜሪካዊ ግለሰብ ግድያን በማስመልከት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በአገራቸው ፍትህ እንዲሰፍን ተማጸኑ። ብጹዓን ጳጳሳቱ በሚኒያፖሊስ ለተፈጸመው ግድያ  ፍትህን ተማጽነው ብጥብጥ እና አመጽ እንዲቆም ጠይቀዋል። አክለውም ከርጅም ዓመታት ወዲህ በሕዝቡ ዘንድ የሚታየው ጥላቻ እና ዘረኛነት እንዲወገድ ጠይቀዋል። በአገሪቱ ውስጥ ቢያንስ በ14 ግዛቶች ውስጥ የተቀሰቀሰውን የሕዝብ አመጽ ለማስቆም የአገሪቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የጸጥታ አስከባሪዎቻቸውን ማሰማራታቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚታዩትን አሳዛኝ ክስተቶች የሚገልጹ ዜናዎች ሲሰራጩ መቆየታቸው ይታወሳል። ጆርጅ ፍሎይድ በተባለ አፍሮ-አሜሪካዊ ግለሰብ ግድያ ምክንያት በሚኒያፖሊስ ግዛት በተቀሰቀሰው አመጽ አንድ ሌላ ሰው መገደሉን እና ሁለት ሰዎች በጽኑ መቁሰላቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ ከጸጥታ አስከባሪዎች መካከል አራቱ ከሰልፈኞቹ በተሰነዘረባቸው ጥቃት  መቁሰላቸው ታውቋል። የዋሽንግተን እና አካባቢዋን ጸጥታ ለማስከበር መንግሥት ጸረ አደንዛዥ ዕጽ ተቆጣጣሪ ፖሊሶችን እና የፌደርራል መከላከያ ሠራዊትን ማሰማራቱ ታውቋል። እስካሁን ድረስ በመላው አገሪቱ ከ4,400 በላይ ሰዎች ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸው እና በ20 ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ 40 ከተሞች ውስጥ የሰዓት እላፊ ገደብ መደንገጉ ታውቋል። ግድያውን ፈጽሟል የተባለውን ፖሊስ መንግሥት መጭው ሰኔ 1/2012 ዓ. ም. በመጀመሪያ ችሎት ለፍርድ የሚያቀርበው መሆኑ ታውቋል። የሚኒያፖሊስ ግዛት ነዋሪ የሆነው ጆርጅ ፍሎይድ ጥፋተኛ ተብሎ በፖሊስ የተያዘው እና ለሞትም የበቃው ከአንድ ሱቅ ለገዛው ዕቃ ሐሰተኛ ባለ 20 ዶላር ኖት ሲከፍል በመያዙ ነው ተብሏል።

ዘረኝነት ተስፋፍቶ ኖሯል፣

“ለፍትህ የሚጮህ እና በኃጢአት የተሞላ የግድያ ተግባር ነበር” በማለት ድምጻቸውን ያሰሙት የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የሎሳንጀለስ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ እሑድ ግንቦት 23/2012 ዓ. ም. እንደተናገሩት፣ በመላው የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ስም ለጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምህረትን፣ በሐዘን ውስጥ ለወደቁት ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ እና ለሚኒያፖሊስ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች በሙሉ መጽናናትን በጸሎታቸው ተመኝተውላቸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ በብጹዓን ጳጳሳቱ ስም በላኩት መልዕክታቸው፣ የአካባቢው ባለ ስልጣናት ፍትህን ለማረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሠሩ፣ የቆዳ ቀለምን በመለየት በአፍሮ-አሜሪካዊያን ላይ የሚደርሰውን በደል፣ አድልዎ እና ዘረኝነት ለማስቀረት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ በአፍሮ-አሜሪካዊያን መካከል የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ ቁጣ ተመልክተው ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።  ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ በማከልም በአገሪቱ እጅግ ሥር የሰደደ ዘረኝነት ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ያለ መሆኑን አስረድተው፣ ለፍትህ መጓደል ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን መለየት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ በማከልም በእነዚህ ቀናት በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱ የሕዝብ አመጾች ለተፈጸመው ድርጊት መልስ እንደማያስገኙ አስረድተው፣ በአገሪቱ ጸጥታ እና መረጋጋት እንዲሰፍን ጠይቀዋል። “የጆርጅ ፍሎይድ ሞት በዋዛ የሚታለፍ አይደለም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሆሴ ሆራሲዮ ጎመዝ፣ ዘረኝነትን እና ጥላቻን ከልባችን በማስወገድ ለጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ ክብር መስጠት ያስፈልጋል ብለው፣ በመላው አገሪቱ የሕይወት ዋስትና፣ ነጻነት እና እኩልነት እንዲረጋገጥ በማለት በመልዕክታቸው ጠይቀዋል።           

የዶናልድ ትራምፕ መግለጫ እና የቤተክርስቲያኗ ምላሽ፣

ሰሞኑን የተቀሰቀሰውን የሕዝብ አመጽ በማስመልከት የአገሪቱ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ በሰጡት መግለጫ፣ አመጹ ሕገ ወጥ እና የአሸባሪነት ተግባር ነው ብለው፣ የህን ሕገ ወጥ ተግባር ለማስቆም የመንግሥታቸው ሕግ በአንቀጽ 1807 ላይ ጸጥታን የሚያስከብር ሃይል የማሰማራት ስልጣን የሚሰጣቸው መሆኑን አስረድተዋል። በመግለጫቸው “በአገሪቱ የተነሳውን አመጽ እና ብጥብጥ ለማስቆም፣ የአገሪቱን ጸጥታ ለማስከበር አደራ እና ስልጣን የተጣለብኝ የአገሪቱ ፕሬዚደንት ነኝ” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሰላማዊ ሰልፎች ወደ አመጽ እና ብጥብጥ እንዲቀየሩ አንፈቅድም ብለው በዋሽንግተን ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ሲደርሱ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍ አድረገው ሲያሳዩ ታይተዋል ተብሏል።

ከፍሎይድ ታናሽ ወንድም የቀረበ ይግባኝ፣

ፍትህን ለመጠየቅ ከወጡት ሰልፈኞች መካከል የሟቹ ጆርጅ ፍሎይድ ታናሽ ወንድም በበኩሉ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሱትን አመጾች ተገን በማድረግ የሚካሄዱ የዘረፋ እና ንብረት የማውደም ተግባራት እንዲቆሙ አሳስቦ፣ ሰላማዊ መንገድን በመጠቀም ፍትህን መጠየቅ እንደሚያፈልግ ጠይቋል። ለወደ ፊት ሕይወታቸው ወሳኝ ወደ ሆነው የመጭው ዓመት ህዳር ወር ምርጫ መዘጋጅት እንደሚያስፈልግ ያሳሰበው ቴረንስ በቺካጎ እና በሚኒያፖሊስ ጎዳናዎች ለሰልፍ ለወጡት ታዳሚዎቹ እንደተናገረው፣ በቁጣ እና በአመጽ በመነሳት በማህበረሰባችን፣ በመኖሪያ ቤቶቻችን፣ በሱቆቻችን እና በንብረቶቻችን ላይ ከፍተኛ ጥፋት የምናደርስ ከሆነ ራስን ከመጉዳት በተረፈ ምንም ውጤት ማምጣት አንችልም ብሏል።

03 June 2020, 15:37