የታይላንድ ክርስቲያን ቤተሰብ፤ የታይላንድ ክርስቲያን ቤተሰብ፤ 

“ቤተሰባችን” የቤተሰብ ተስፋ እና ተግዳሮት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን (1)

ለቤተስብ የሚሰጥ ትርጉም በመልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ፣ በእምነት እና በባሕል አወቃቀር ምክንያት ሊለያይ ቢችልም መሠረታዊ ትርጉሙ ተመሳሳይነት አለው። “ቤተሰብ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል በሚደረግ ስምምነት በአንድ ቤት ውስጥ እየኖረ ከጊዜ ወደ ጊዜ በቁጥር የሚያድግ ማሕበራዊ ተቋም ነው” የሚለው ትርጉም ብዙ የኅብረተሰብ ጠበብት የሚስማሙበት ነው።  

የማኅበረሰብ ጠበብት ለቤተሰብ የሚሰጡት ትርጉም ባሕልን እና የሰዎችን የእድገት ደረጃ መሠረት ያደረገ ነው። አንዳንድ አገሮች ለቤተሰብ የሚሰጡን መሠረታዊ ትርጉም ሳይለውጡ ነገር ግን ቤተሰብ ማለት በአንድ ቤት ውስጥ አብረው ከሚኖሩ የቤተሰብ አባላት በተጨማሪ በጋብቻ፣ በሥራ እና በሌሎች ምክንያቶች ከወላጆቻቸው ቤት ወጥተው በሌላ አካባቢ የሚኖሩትንም ያካትታል። እንደዚሁም የደም ግንኙነት ባይኖርም እንኳን በአስተሳሰብ፣ በእምነት እና በመልካም ማኅበራዊ ግንኙነት ምክንያት ራሳቸውን እንደ አንድ ቤተሰብ የሚቆጥሩ አሉ።

የተለያዩ ባሕሎች እና እምነቶች ለቤተሰብ ያላቸው ግንዛቤ የሚለካው ቤተሰብ ለማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚያበረክቱኑን አስተዋጽዖ መሠረት በማድረግ ነው። ቤተሰብ፣ አምስቱ ታላላቅ ማሕበራዊ ተቋማት ከሚባሉ፥ ትምህርትዊ ፣ ሐይማኖታዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና መንግሥታዊ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። የእነዚህ ማሕበራዊ ተቋማት ቀዳሚ ዓላማ፣ የሰዎችን ሕይወት በእውቀት፣ በእምነት ፣ በሃብት እና በኑሮ ደንብ በማገዝ እድገታቸው፣ ፍቅራቸው፣ ብልጽግናቸው እና የኑሮ ሥርዓታቸው ትክክለኛ መንገድ እንዲረጋግጥላቸው ለማድረግ ነው። ከእነዚህ ማኅበራዊ ተቋማት መካከል የቤተሰብን ተቋም ልዩ የሚያደርገው፣ በሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ በመግባት እውቀቱን እና ጉልበቱን በማበርከት፣ ለማኅበራዊ እድገት አስተዋጽዖ የሚያደርግ የሰው ኃይል የሚያቀርብ መሆኑ ነው።

ቤተሰብ ለሚለው ቃል በተቻለ መጠን ሙሉ ማብራሪያን መስጠት እንዲቻል፣ በአንድ ቤት ውስጥ አብረው በሚኖሩ የቤተሰብ አባላት እነርሱም እናት፣ አባት እና ልጆቻቸው ላይ የምናተኩር ይሆናል። በአንድ ቤት ውስጥ በሚኖሩ የቤተሰብ አባላት መካከል የሚታይ የዕድሜ፣ የጾታ እና የትምህርት ደረጃ ልዩነቶችን መዘንጋት የለብንም። ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሚሳተፍበት የሥራ ዘርፍ እና የሚኖረው ሃላፊነት እንደዚሁ ይለያያል። አባት እና እናት ልጆች ከተወለዱ በኋላ የመቀለብ፣ የማሳደግ እና የማስተማር ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው። በመልካም ስነ-ምግባር ከታነጸ ወላጅ የሚወለድ ልጅ ከራሱ አልፎ ሌሎችን የማሕበረሰብ ክፍሎችን በማገዝ የበኩሉን ሃላፊነት ይወጣል። ልጆች ከወላጆቻቸው በሚደረግላቸው ድጋፍ በመታገዝ ራሳቸውን፣ ወላጆቻቸውን እና የሚኖሩበትን ማኅበረሰብ መልሰው የማገዝ እና የመንከባከብ አደራ እና ሃላፊነት አለባቸው። ቤተሰብ ለማኅበራዊ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽዖ ዘላቂ ለማድረግ ከሁሉ አስቀድሞ የቤተሰብ ህልውና እንዲረጋገጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው።  

ቤተሰብን የተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላል። ረሃብ፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ ስደት እና መፈናቀል፣ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ መገለል፣ የተፈጥሮ አደጋ እና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች አደጋ ውስጥ ሊጥሉት ይችላል። በኅብረተስብ መካከል የሚገኙ ማኅበራዊ ተቋማት ኅብረት ያስፈለበት ዋናው ምክንያት በቤተሰብ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በጋራ በመወጣት ወደ ተሻለ የሕይወት ደረጃ እንዲደርሱ ለማድረግ ነው። ቤተሰብ በሁሉም ማኅበራዊ ዘርፎች አስፈላጊው ድጋፍ ካልተደረገለት ለልዩ ልዩ ማኅበራዊ ተቋማት የሚያቀርቡት፣ በእውቀት እና በጉልበት ያደገ የሰው ሃይል እጥረት ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም መንግሥታዊ እና ሐይማኖታዊ ተቋማት የቤተሰብን ሕይወት እና ደህንነት የመንከባከብ እና የማጠናከር ሃላፊነት አለበት። ለኤኮኖሚ እድገት የጥቂት ቤተሰብ እገዛ ብቻውን በቂ አይደለም። የተቀናጀ የቤተሰቦች ትብብር ሊኖር ይገባል። ቤተሰብን የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ልማት ፕሮግራም ማዕከል ለማድረግ የኑሮአቸው ሁኔታ ተጠንቶ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት ያስፈልጋል። 

በአገሮች መካከል ሰፊ የኤኮኖሚ ልዩነቶች መኖራቸውን እንመለከታለን። አንዳንድ አገሮች በቴክኖሎጂ አድገው፣ በኤኮኖሚ በልጽገዋል፣ የሕዝቦቻቸው ማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ደርሶ እናያለን። አገሮች እኩል የኤኮኖሚ እድገት ሊኖር አይችልም። የአንድ አገር እድገት የሚለካው በዜጎቹ ማኅበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ ጥራት እና መጠን ነው። በመሆኑም የቤተሰብ አባላት በማኅበራዊ አገልግሎት ለማሳተፍ ጥራት ያለው የትምህርት እና የስልጠና ዕድል ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን።   

06 June 2020, 19:28