የእናቶች ቀን በዓል በፍሎሪዳ ጎዳናዎች ሲከበር፣ የእናቶች ቀን በዓል በፍሎሪዳ ጎዳናዎች ሲከበር፣ 

ግንቦት 2/2012 ዓ. ም. የእናቶች ቀን ተከብሮ ዋለ።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቤተሰቦች ዓመታዊውን የእናቶች ቀን እሑድ ግንቦት 2/2012 ዓ. ም. በዝግ አክብረው መዋላቸው ታውቋል። በእናቶች ቀን የቤተክርስቲያን እናት እና በስቃይ ላይ የሚገኙ ሴቶች እናት ወደ ሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት መቅረቡ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር የግንቦት ወር ሁለተኛው እሑድ በበርካታ አገሮች ዘንድ የእናቶች ቀን በመባል ተከብሮ የሚውል መሆኑ ይታወቃል። በየአገራቱ እና በየቤተሰብ መካከል እንደ አመቺነቱ በተለያየ ደረጃ ተከብሮ የሚውል ቢሆንም ዋና ዓላማው ለእናቶች ክብርን ለመስጠት፣ ለእኛ ሲሉ በየቀኑ የሚከፍሉትን መስዋዕትነት ለማሰብ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሰው ልጅ ስብዕና የተመሠረተው በእናቶች ጥረት ነው ብለው፣ በልዩነት እና በጥላቻ በተሞላው ዓለም ውስጥ እናቶች የፍቅር መድኃኒት ናቸው ማለታቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በማከልም እናቶች ታላቅነታቸውን የገለጹት ርህራሄ እና ትህትናን በማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓለማችን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት የእናቶች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ቢሆንም እናቶች ከልጆቻቸው ጋር ተሰብስበው በጋራ ለማክበር እድል ያገኙበት ዕለት መሆኑ ታውቋል። ከዚህ በፊት በርካታ ቤተሰቦች በሥራም ሆነ በሌሎች ምክንያት ተለያይተው የቆዩ መሆናቸው ታውቋል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተጠቁ እናቶች ብዙዎቹ ነፍሰ ጡሮች መሆናቸው ሲነገር፣ በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳረጋገጠው በዓለማችን ውስጥ ወደ 116 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የሚወለዱ መሆናቸው ታውቋል። የሕጻናት መርጃ ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ ሄንሬታ ፎር እንደገለጹት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እናቶች ትዳርን የመሠረቱት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት መሆኑን አስታውሰው፣ እነዚህ እናቶች የሚወልዷቸውን ሕጻናት ለማሳደግ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። ነፍሰ ጡር እናቶች ወደ ሕክምና አገልግሎት ለመሄድ ፍርሃት እንደሚይዛቸው ገልጸው ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለእናትነት ስሜት ከፍተኛ እንቅፋት የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “እናቶች ለልጆቻቸው ሙሉ ፍቅርን በማሳየት የሰላም ምሳሌ ናቸው” ብለው፣ የብቸኝነት እና የራስ ወዳድነት ስሜት የሚያስወግዱ፣ ከዚህም በተጨማሪ ጦርነትንም የሚቃወሙ መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሕይወቷ ብዙ የመከራ ጊዜዎችን አሳልፋለች ብለው፣ መልካም እናት በመሆኗም ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር በመሆን በሕይወታችን ውስጥ መከራ ሲያጋጥመን ብርታትን እና ድፍረትን ትሰጠናለች ብለዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የግንቦት ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተክርስቲያን እናት መሆኗ የሚታወስበት ወር ነው በማለት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ1964 ዓ. ም. በይፋ ማወጃቸው ይታወሳል። እግዚአብሔርም እመቤታችንን የሰላም ንግሥት እንድትሆን መርጧታል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ማርያም የጠላትን ሴራ በማክሸፍ፣ በሰዎች መካከል አንድነትን በመፍጠር ወደ መልካም መንገድ የምትመራ የሰላም ንግሥት መሆኗንም አስረድተዋል።

በግንቦት ወር ምዕመናን የመቁጠሪያ ጸሎትን በመድገም ወደ እመቤታችን ቅድስት ድስንግል ማርያም ጸሎት ማቅረብ እንደሚገባ አሳስበው፣ የኮሮና ቫይረስ ያደረሰብንን ስቃይ ለማስወገድ ቤተሰብ በጸሎት እንዲተባበር አደራ ብለዋል።

እሑድ ግንቦት ሁለት ቀን 2012 ዓ. ም. በመላው ዓለም የሚገኙ ቤተሰቦች በመተባበር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን ማቅረባቸው ታውቋል።            

11 May 2020, 15:41