በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ለሕጻናት ምግብ ሲታደል፤ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ለሕጻናት ምግብ ሲታደል፤ 

“ቤተሰባችን” በስቃይ መካከል ፍቅር ጎልቶ ሲታይ!

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደ ምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን አስጨናቂ ጊዜን እንዴት ተቋቁመን ልናልፈው እንችላለን? በግል ሆነ በጋራ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል የሚሉ ጥያቄዎችን ተመልክተን ጠቃሚ ከሆኑ የመፍትሄ ሃሳቦች መካከል ጥቂቶችን አብረን እንመለከታቸዋለን፤ አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉ እንጋብዛችኋለን።  

እንደሚታወቀው ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለማችን ሕዝብ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመቱ፣ መከላከያም ሆነ መፈወሻ መድኃኒት እስካሁን አለመገኘቱ፣ በዚህ ምክንያት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ለሞት መዳረጉ፣ የሰዎች ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሕይወት ከነበረበት ደረጃ ውጥቶ ሕይወትን የበለጠ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ያስከተለው አደጋ ዓለማችንን ሲያስጨንቁ ከቆዩ አደጋዎች መካከል አንዱ ነው። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ስቃይ እና የሞት አደጋ ከቅርብ ወራት ወዲህ የጀመረ እንጂ ዓለማችን በተለያዩ መኅበራዊ እና የተፈጥሮ ችግሮች ውስጥ ከገባ ብዙ ጊዜ ሆኖታል ማለት ይቻላል። ጦርነት፣ አመጽ፣ ረሐብ፣ በሽታ እና ስደት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል በማድረግም ላይ ይገኛል። በሰው ልጆች መካከል ሊኖር የሚገባው ፍቅር፣ መተሳሰብ እና መረዳዳት እየቀነሰ ሲመጣ በዚያው መጠን ችግሮች እያደጉ፣ እየጨመሩ ይመጣሉ።   

በማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ላይ ሊደርሱ ከሚችሉት ቀውሶች በተጨማሪ ተፈጥሮም ቢሆን የሚገባውን እንክብካቤ እና ጥበቃ ካልተደረገለት በሕይወት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ቀላል አይደለም። በተፈጥሮ ላይ የምናደርሰው ጥፋት በጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን ላይ ያስከተለው አደጋ ጥቂት የሚባል አይደለም። ለተፈጥሮ ሊሰጥ የሚገባው እንክብካቤ እና ጥበቃ ሲጓደል የአየር ንብረት ለውጥ፣ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፣ የምድራች በረሃማነት ፣ የባሕር መናወጥ፣ የጎርፍ አደጋን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አደጋዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ለምን ወይም እንዴት ተከሰተ ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ፣ ለእያንዳንዱ ክስተት የራሱ መነሻ እና ምክንያት አለው። በሰዎች ማኅበራዊ ሕይወት እና በተፈጥሮ ላይ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ በመካከላቸው ሊኖር የሚገባ መልካም ግንኙነት አደጋ ላይ መውደቁን እንገነዘባለን። ይህን ካወቅን ቶሎ ብሎ ወደ መፍትሄ ከመሄድ ሌላ አማራጭ አይኖርም።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወዳስከተለው ማሕበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ስንመለስ፣ በቅርቡ አንድ ካህን ያደረጉትን አስተንትኖን እንመለከታለን። እንደሚታወቀው በዓለማችን ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ሰዎች የገንዘብ፣ የጉልበት እና የእውቀት ድጋፋቸውን በማበርከት ላይ ይገኛሉ። በተለይም የጤና ባለሞያዎች የሕክምና ድጋፍ እና የምክር አገልግሎትን በመስጠት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ ስቃይ በሚታይበት ባሁኑ ወቅት በሕክምና አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙት የጤና ባለሞያዎች ፣ የተጠሩበት የአገልግሎት ዘርፍ የሞት መስዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑን ይገነዘባሉ። በሕይወታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከባድ አደጋን ሳይፈሩ ነፍስ አድን የሕክምና አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙትም ለሕይወታቸው ግድ የለሽ ስለሆኑ ሳይሆን የተጠሩበት የፍቅር አገልግሎት ፍርሃትን የሚያሸንፍ መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ነው በማለት ካህኑ አስረድተዋል።

ሕይወታችንን እስከማጣት ደርሰን ሌሎች ለመርዳት እና ለማገልገል የምንነሳው በልባችን ውስጥ ፍቅር ሲኖር ነው። ፍቅር፣ ደግነት፣ ቸርነት እና ርህራሄ በውስጣችን የምንይዛቸው ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል የተሰጡን የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። የተሰጡንም ራስን ብቻ ለመጥቀም ሳይሆን ሌሎችን ማገልገል እንድንችል ነው። ወደ ሌሎች ዘንድ ደርሰው በተግባር የማይገለጹ ከሆነ እነዚህ ስጦታዎች ፍሬን ሳያፈሩ ይቀራሉ። በውስጣችን ይዘን የምንቆይ ከሆነ ወይም ራሳችንን ብቻ የምንጠቅም ከሆነ የስጦታውን ትክክለኛ ትርጉም እንዘነጋለን ማለት ነው።      

ልባችንም በፍቅር እሳት በሚቃጠልበት ጊዜ ብዙ አስደናቂ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ካለው የሞት አደጋ በተጨማሪ በመካከላችን በድህነት፣ በስደት፣ በፍትህ መጓደል፣ ከሕብረተሰቡ መካከል በመገለል፣ በመበዝበዝ፣ በመጨቆን፣ ፍትህን በማጣት የተለያዩ በደሎች የሚደርስባቸው ሰዎች መኖራቸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን በጭንቀት፣ በሕመም እና በሞት ውስጥ ባስገባበት በዚህ አስፍሪ ጊዜ የጤና ባለሞያዎች እና ሌሎችም የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል የተነሱበት ዋና ምስጢር የፍቅርን ታላቅነት ለመግለጽ፣ የስቃይ ታሪክን በሙሉ ወደ ፍቅር መለወጥ የሚቻል መሆኑን እንገነዘባለብ በማለት የዛሬውን ሳምንታዊ የቤተሰባችን ዝግጅት በዚህ እናጠቃልላለን። በሚቀጥለው ሳምንት እስከምንገናኝ ሰላም፣ ፍቅርን እና ጤናን የምመኝላችሁ የፕሮግራሙ አዘጋጅ እና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን ነኝ።

ይህን ዝግጅት በድምጽ መከታተል ከፈለጉ “ተጫወት” ምልክትን ይጫኑ፣
09 May 2020, 21:35