ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከሞት አደጋ ሲያተርፋቸው፤ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከሞት አደጋ ሲያተርፋቸው፤ 

“ቤተሰባችን” ወረርሽኙ ያመጣው የጸጥታ ጊዜ የመለወጥ እንጂ የጭንቀት መሆን የለበትም!

ክቡራት እና ክቡራን የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ተከታታዮቻችን እንደምን ሰንብታችኋል። በዛሬው ሳምንታዊ የ“ቤተሰባችን” ዝግጅት ዓለማችንን በማስጨነቅ ላይ በሚገኝ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዙሪያ  የተሰጡ አንዳንድ አስተያየቶችን እናካፍላችኋለን።

በማኅበራዊ መገናኛዎች ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መወራት ከጀመረ ወራት አልፈዋል። ስለ ቫይረሱ እና  የመተላለፊያ መንገዶች በሚገባ አውቀን ራሳችንን እና ሌሎችን ከሞት ማትረፍ የእያንዳንዳችን ግዴታ ነው። ወረርሽኙ በቅርብ ወራት በመቶ ሽህዎች የሚቆጠር የሰው ሕይወት ለሞት መዳረጉ አደገኛነቱን እጅግ አጉልቶታል።

ስለ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ ተብሏል። በተለይ ፈዋሽ መድኃኒት እሳካሁን አለመገኘቱ መላውን ዓለም ጭንቀት ውስጥ ከቶታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ተቋም የቫይረሱን መዛመት ለመቆጣጠር የሚያግዙ ምክሮችን በየጊዜው ለአገራቱ እያዳረሰ ይገኛል። ይህ መረጃ በሁሉም የዓለማችን አካባቢዎች መልካም ውጤት እያስገኘ ነው ባይባልም ጥንቃቄዎችን በተግባር በሚያውሉ አካባቢዎች የቫይረሱ መዛመት ከመቀነሱ በላይ የሟቾች ቁጥርም ዝቅ ማለቱ የሚያስመሰግን ነው። የቫይረሱ መዛመት በመላው ዓለም በቁጥጥር ካልዋለ መልካም ውጤት ተገኘ ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ተመልሶ ማጥቃቱ አይቀርምና። ለዚህም ነው ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ ትብብርን እና ጥረትን ይጠይቃል የሚባለው።  

የቫይረሱን መዛመት ለመቀነስ ሲባል መንግሥታት የተለያዩ እርምጃዎች ወስደዋል። መሥሪያ ቤቶች እና የትምህርት ተቋማትእንዲዘጉ፣ የስፖርት ማዕከላት፣ የአምልኮ ሥፍራዎች፣ ባጠቃላይ ሰው በብዛት የሚገኙባቸው ቦታዎች ለጊዜው እንዲዘጉ ተደርገዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ተለያይተው የቆዩ የቤተሰብ አባላት ወደ ቤታቸው ተመልሰው በአንድነት የሚሆኑበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል። ይህን አጋጣሚ በመልካም ጎኑ ስንመለከተው ቤተሰባዊ ግንኙነት እና የእርስ በእርስ መረዳዳት ማደጉን እንገነዘባለን። ባሁኑ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የቤተሰብ አባላትን ብቻ ሳይሆን ጎረቤትን፣ ቀበሌዎችን፣ ወረዳዎችን፣ አውራጃዎችን፣ ክፍላተ ሃገራትን፣ ሃገራትን ወይም መንግሥታትን በማቀራረብ አንዱ ለሌላው እንዲጨነቅ እና በመካከላቸው መረዳዳት እንዲኖር አድርጓል። ዜጎች ስለ ሕዝባቸው በመጨነቅ ከወረርሽኙ የሚተርፉበትን የገንዘብ፣ የእውቀት እና የጉልበት እርዳታ በማስተባበር አለኝታነትን እና ፍቅርን በማሳየት ላይ ይገኛሉ። ወረርሽኙ በባሕሪው የመንግሥታትን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን እና የግለሰቦችን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑ ግልጽ ነው።

የሐይማኖት ተቋማት ተቀራርበው ይቅርታን በመደራረግ፣ ከዚህ አስከፊ ወረርሽኝ እግዚአብሔር እንዲታደጋቸው በማለት ምዕመናኖቻቸውን በማስተባበር ተንበርክከው ምሕረቱን በመለመን ላይ ይገኛሉ። ሁላችንም እንደምንረዳው አሁን የምንገኝበት ወቅት አንዴ ቆም ብለን ብዙ ነገሮችን እንድናስብ፣ ህሊናችንን እንድንመረምር ይጋብዘናል። የተጓዘንባቸው የሕይውት መንገዶቻችን ምን እንደሚመስሉ፣ ወደ ፊት ሕይወታችንን እንዴት መምራት እንዳለብን ለማሰብ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮልናል ማለት ይቻላል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሚያዝያ 13/2012 ዓ. ም. “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያመጣውን የጸጥታ ጊዜ በመጠቀም ከእግዚአብሔርን እና ከራሳችን ጋር መነጋገር የምንችልበትን አቅም ለማግኘት በርትተን መጸለይ ያስፈልጋል” ማለታቸው ይታወሳል። አሁን የምንገኝበት ጊዜ በሕይወታችን መሠረታዊ ለውጥን ለማምጣት ምቹ አጋጣሚ፣ የምሕረት እና የጸጥታም ጊዜ መሆኑን አንድ የፍራንችስካዊያን ካፑቺን ታናናሽ ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት አባ ኤሚሊያኖ አንተኑቺ አስረድተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰው ሕይወት ላይ እያስከተለ ያለውን የሞት አደጋ ብቻ ተመልክተን በፍርሃት እና በጭንቀት ከመኖር ይልቅ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በጸሎት የምንቀርብበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን መጠቀም እርስ በእርስ መጽናናትን፣ ከወረርሽኙ አስቀድሞ ይሁን በኋላ፣ በተለያዩ ችግር ውስጥ ለሚገኙት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እርዳታችንን፣ በሕዝቦች፣ በመንግሥታት እና በሐይማኖት ተቋማት መካከል ያመጣውን ኅብረት መመልከት እና ማስታወሱ መልካም ይሆናል።

ከዮሐንስ መኰንን።

26 April 2020, 21:18