ወጣትነትና፤ቅደመ ጋብቻ ግንዛቤ ወጣትነትና፤ቅደመ ጋብቻ ግንዛቤ 

ወጣትነትና፤ቅደመ ጋብቻ ግንዛቤ

በሰው ልጅ ዕድገት ውስጥ የሕፃንነት፣ ልጅነት፣ ወጣትነት፣ ጎልማሳነትና የእርጅና ደረጃዎች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ የዕድገት ደረጃዎች ውስጥ መደረግ የሚገባቸው (አንድ ሰው ሊያከናውናቸው የሚገባቸው ነገሮች አሉ)፡፡ እነዚህን ለዕድሜ የሚመጥኑ ተግባራትን በተገቢው ዕድሜ አለማከናወን በቀጣዮቹ ደረጃዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡

አዘጋጅ እና አቅራቢ አሸናፊ ደበል-ቫቲካን

በልጅነት ጊዜ በአብዛኛው ራሳችንን ስለማንችል በብዙ ነገር በወላጆቻችን ላይ ጥገኞች ሆነን እንኖራለን፡፡ ሆኖም በልጅነት ጊዜ ለወጣትነት ጊዜ መልካም መሠረት የሚጥሉ ሥራዎችን እንሠራለን (ለምሳሌ ትምህርት መማር፣ የተለያዩ ክህሎትን ማጎልበት፣ …)፡፡ በወጣትነትና በጎልማሳነት ጊዜም እንዲሁ የምንሰራቸው ስራዎች ይኖራሉ፡፡ከወላጆቻችን ጋር በጥገኝነት የምንኖረው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ እያደግን ስንሄድ፣ እነርሱን ትተን በራሳችን መኖር መጀመር አለብን፡፡

ሰውነታችንና አእምሮአችን ‹‹ለጋብቻ ደርሰሃል/ ደርሰሻል›› ብለው ሲደውሉ ማዳመጥ አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህን ማዳመጥ ካልቻልን ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች  ‹‹እንዴት ነው አልደረሰም›› የሚል ሃሳብ ሲያቀርቡ ከመደንገጥ ወይም ችላ ከማለት ቆም ብሎ በማሰላሰል አዎንታዊ እርምጃ መውሰድ መልካም ነው!

ከጋብቻ በፊት ከሚጠየቁ መሠረታዊና አስፈላጊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ‹‹መቼ ላግባ?” የሚለው ነው፡፡ ሆኖም ስለጋብቻ ለሚያስቡ ወጣቶች ለዚህ ቅድመ ጋብቻ ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠት ቀላል እንዳልሆነ ይታሰባል፡፡እንዲህም ሆኖ ለሁሉም ነገር ጊዜ ስላለው፣ ነገሮች በተገቢ ጊዜያቸው ሲከናወኑ ውበት ይኖራቸዋል፡፡ በሰው ልጅ ውስጥ ጊዜን የማወቅ እምቅ ጥበብ አለ፡፡ በውስጣችን የተቀመጡ ሆርሞኖችም ጊዜያቸውን ጠብቀው ስራቸውን ሲሰሩ የተለያዩ እርምጃዎችን እንድንወስድ ያነሳሱናል፡፡ይህም ተፈጥሮ ራሷ ሰዓት አላት እንደ ማለት ነው፡፡

በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ወጣቶች መቼ ማግባት እንዳለባቸው ከመጠየቃቸው በፊት ወላጆች ይወስኑላቸዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ጋብቻ የሚወሰንላቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ ለአንዳንዶች ደግሞ የጉርምስና ዕድሜያቸውን እንደ ጀመሩ ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው በሁለንተናዊ ሕይወታቸው ሙሉ ሰው ከመሆናቸው በፊት ወደ ጋብቻ እንዲገቡ ማድረጋቸው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ነው፡፡ የልጅነት ወቅት የሚባለው በአጠቃላይ መልኩ ሲታይ እስከ 18 ዓመት ያለው ዕድሜ መሆኑ ነው፡፡

በልጅነት የሚደረግ ጋብቻ በልጆቹ ሕይወት በተለይ በሴት ልጆች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያመጣል፡፡ ከዚህም በላይ  በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶችን ያስከትላል፡፡

መቼ ነው የማገባውን በተመለከተ ለበለጠ ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ በአንድ ሠርግ ላይ የሆነውን አንድ ታሪክ ላስከትል፡፡የአራት ዓመት ልጅ ከቤተሰቡ ጋር በአማረ ሠርግ ላይ ተገኝቶ በጣም ደስ ስላለው “እኔም ማግባት አለብኝ” ብሎ ወድያው ለእናቱ ይነግራል:: እናቱም ልጅዋን ላለማስከፋት ብላ “ ማንን ነው የምታገባው ማሙሽ?” ትለዋለች:: ሕፃኑም በጠረጴዛው ዙርያ ከተቀመጡት መርጦ: “ እከሊትን ነው የማገባው እማዬ” ብሎ በደስታ ይፈነድቃል:: “እከሊትማ ባል አላት ማሙሽ” ይሉታል በጠረጴዛው ዙርያ የተቀመጡት እየተሳሳቁ:: “እሺ እንግድያስ እከሊትን ነው” ይላል ማሙሽ አንድዋን ወጣት መልከት አድርጎ:: “እርሱዋማ ገና ተማሪ ናት ማሙሽዬ” ትለዋለች እናቱ ማሙሽን አቅፋ እያሻሸችው:: ማሙሽ በነገሩና በሰዉ ሳቅ በመናደድ “እንግዲያውስ አንቺን አገባለሁ” በማለት በጠረጴዛው ዙርያ ያሉትን ሁሉ በጣም አሳቀ::

አንዳንዴ  አዋቂ ትዳር ፈላጊዎችም እንደ ማሙሽ የሚሆኑበትና የሚሰሩትን የማያውቁበት ጊዜ አለ:: ጋብቻ ላልበሰሉ ሕፃናት  አልተፈቀደም::ጋብቻ በመንፈስና በአካል ላደጉት ጎልማሶችና ከዋዥቀ ሃሳብ ለተላቀቁት ወጣቶች አልያም ለአዋቂዎች ነው:: ሞቅ ሲለን ወይም የሰው ሠርግና ትዳር አይተን ወይም በቀን  ቅዠትና በሌሊት ሕልም የምንገባበትም መሆን የለበትም:: አንድ ሰው ለትዳር በቂ በሆነ አካላዊና መንፈሳዊ አስተሳሰብ አደገ የምንለው በጥልቅ ፍቅር መውደድ ሲችል ብቻ ነው:: ጋብቻ - የትምህርት፣የዕድሜ፣ የባህል፣የጊዜና የገንዘብ ዝግጅት የሚያስፈልገው ነው:: በርካታ በምዕራቡ ዓለም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአስር እስከ ሃያ ሁለት ዓመት ያለው ዕድሜ ክልል ለጋብቻ የሚያስፈልጉት መሠረታዊ የአስተሳሰብና አካላዊ ዝግጅቶች የሚሟሉበት ጊዜ ነው:: በአጠቃላዩ  እስከ ሃያ ሁለት ዓመት ያሉ ወጣቶች ለጋብቻ ሕፃናት መሆናቸውን እና ምርጫቸው ከላይ እንደተመለከትነው ማሙሽ የመሆን አዝማሚያ እንደሚኖረው ነው::

በስደት  ከአገር የሚወጣው ትውልድ ደግሞ እነዚህን መሰረታዊ ዝግጅቶች ለማሟላት ተጨማሪ አመታት ሊወስድበት ይችላል:: እንግዲህ ጋብቻን የሚያስብ ሰው እንደ ባለአዕምሮ ሰው ዕድሜዬ ለጋብቻ ደርሷል ወይ? በሎ መጠየቅ በመጀመርያ ይገባዋል:: ከዚያም በአካልና በአዕምሮ በስሜትና በመንፈሳዊ ሕይወቴ ጎልምሻለሁ ወይ? ትዳር ለሚያስፈልገው ዘለቄታዊ ቃልኪዳን የቆረጠ ውሳኔ አለኝ ወይ? ጤናማ ትዳር ምን እንደሚመስል ምሳሌ ሆኖ ያሳየኝ ወላጅ፣ አሳዳጊ ወይም ዘመድ አለ ወይ? የማገባትን ሚስት ወይም የማገባውን ባል የማስተዳድርበት ሥራና ንብረት አለኝ ወይ? ትምህርቴን ጨርሻለሁ  ወይ?  የሰከነና ቤተሰቤን ለመምራት የሚያስችል የጸባይ አቋም አለኝ ወይ? ስለትዳር ጥሩ አቋም ያለው ቤተ እምነትስ ተሳታፊ ነኝ ወይ? በማለት ራሱን መጠየቅ በመጀመርያ ይገባዋል::በዚህ ሃሳብ የተቃኘ ወጣት እነዚህን ዐበይት ሕይወት ነክ ጥያቄዎች በበቂ ይመልስልናል:: በዚህ ዓይነቱ ቅድመ ዝግጅትና ሂደት ውስጥ አልፎ የሚመሰረተውም ጋብቻ ጠንካራ መሰረት ይጥላል::የማያስማማ፣ነፋስ ሲነፍስና የግጭት ዝናብ ሲያካፋም በጣም የሚያሰጋው ነገር አይኖርም::

17 January 2020, 14:50