በቻይና የሚገኝ የሻንጋይ ከተማ፣             በቻይና የሚገኝ የሻንጋይ ከተማ፣  

“የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀነስ ከተሞችን በአረንጓዴ ተክሎች ማልማት ያስፈልጋል”።

“ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ የሚወያይ ሦስተኛ ዙር ዐውደ ጥናት፣ ሰኞ ጥር 4/2012 ዓ. ም. ሮም ከተማ በሚገኝ ቅዱስ ዮሐንስ ዘ ላቴራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መካሄዱ ታውቋል። በአውደ ጥናቱ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙት፣ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ እና አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ መሆናቸው ታውቋል። ክቡር አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ በአውደ ጥናቱ ላይ “ለስነ ምሕዳር ቀውስ የስው ልጅ አስተዋጾ” በሚል ርዕሥ ተመርኩዘው ጥናታዊ ጽሑፍ ማቅረባቸው ታውቋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጎርጎሮሳዊያኑ አዲስ ዓመት፣ 2020 ዓ. ም. ከገባ ወዲህ የመጀመሪያ በሆነው ዐውደ-ጥናት ላይ፣ ሥነ ምሕዳርን በማስመልከት ጥናታዊ ጽሁፋቸውን ያቀረቡት፣ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ደ ዶናቲስ እና አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ በመመርኮዝ፣ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከጥፋት እና ከውድመት መከላከል በምንችልባቸው መንገዶች ላይ ያስተነተኑበትን ጥናታዊ ጽሑፍ በዐውደ-ጥናቱ ላይ ማቅረባቸው ታውቋል። በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ዐውደ-ጥናቱ በየወሩ እየተካሄደ እስከ መጭው ሰኔ ወር የሚቆይ መሆኑ ታውቋል።

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አቶ ዳቪድ ሳሶሊ እና የአየር ትንበያ ተመራማሪ ክቡር አቶ ሉካ ሜርካሊ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደረጉት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ በመመርኮዝ ባለፉት ወራት ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ማቅረባቸው ይታወሳል። “ለስነ ምሕዳር ቀውስ የስው ልጅ አስተዋጾ” በሚል ርዕስ ላይ፣ ሰኞ ጥር 4/2012 ዓ. ም. በተካሄደው ዐውደ-ጥናት፣ ከክቡር አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ በተጨማሪ፣ በጣሊያን፣ ሚላኖ ዩኒቨርሲቲ፣ የከተማ ልማት መምህር እና በሻንጋይ የፊውቸር ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር ተገኝተው ልምዳቸውን ማካፈላቸው ታውቋል።

የከተማ ውስጥ ተክሎችን መንከባከብ እና ማሳደግ፣

አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ፣ በጥናታዊ ጽሑፋቸው በኩል እንዳስገነዘቡት፣ የከተማ ውስጥ ተክሎችን እና ዛፎችን የመንከባከብ እና የማሳደግ ዕቅድ በስፋት መለመድ እና ማደግ እንዳለበት አሳስበው፣ የሰው ልጅ በከተማም ሆነ በዱር ከሚበቅሉ እጽዋዕት ጋር ያለው ግንኙነት ማደግ እዳለበት አሳስበዋል። የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ዛፎች የሚገኙት በዱር ወይም በጫካ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በተለይም በከተማ ውስጥ ቢያድጉ የከባቢ አየር ለውጥ ቀውስን በመቀነስ ለኑሮ የተመቻቸ አካባቢን በመፍጠር ትልቅ እገዛን የሚያበረክቱ መሆኑን አስረድተዋል።

የታዳሽ ኃይል አስፈላጊነት፣

አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ፣ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፣ ለአካባቢ ጥበቃ እንዲሆን በማለት  የምናደርጋቸው ጥንቃቄዎች፣ ከተሞቻችን በየዕለቱ የሚያመነጩት፣ 75 ከመቶ የሚሆን የተቃጠለ አየር ወደ ሕዋ የሚያሰራጭ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት ብለዋል። አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ የአካባቢን ደህንነት እና እንክብካቤን የሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት አሳስበው፣ በተለይም በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ላይ የሚገኙትን ወጣት ማሕበረሰብን የሚያሳትፍ መሆን ይኖርበታል ብለዋል። አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ ከዚህም ጋር በማያያዝ እንዳስረዱት፣ ከፀሐይ፣ ከነፋስ፣ እና ከውሃ የሚመነጩ የታዳሽ ኃይል አስፈላጊነትን እና በአካባቢያችን ከሚበቅሉ ተክሎች ጋር ያላቸውን ተፈጥሮአዊ ግንኙነት አስረድተው፣ የታዳሽ ኃይል ጥቅም ተፈጥሮን ለመንከባከብ እና የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን ከጉዳት ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የፍጥረት እንክብካቤ እና የር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስተምህሮ ሚና፣

ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮዎች ትኩረታቸውን የሰጡት አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ፣ ቅዱስነታቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በኩል የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችን አስመልክተው ጥልቀት ያላቸውን አስተምህሮዎችን ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ በሥነ ምሕዳር ጥናት ላይ ለሚሳተፉ ባለሞያዎችን ከፍተኛ እገዛ ማበርከታቸውን አስታውሰው፣ በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ ወጣት የስነ ምሕዳር አጥኚዎችም በምድራችን የተከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥ ከልብ በመረዳት፣ የሚከሰተውን አደጋ ለመቀንስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ በማለት አርክቴክት አቶ ስቴፋኖ ቦዬሪ አሳስበዋል። “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን፣ በርካታ የፖለቲካ መሪዎች፣ ሳይንትስቶች፣ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ከሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች አስቀድሞ የነበሩ ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዘ በመሆኑ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
15 January 2020, 16:34