ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን  

ካርዲናል ታርክሰን፣ “ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ለድሆች ስቃይ መልስ መስጠት ያስፈልጋል”።

በስዊዘርላንድ-ዳቮስ፣ ከጥር 12-15/2012 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ በሚገኝ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ የተገኙት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን “ለምድራችን እና ለድሆች ስቃይ መልስ መስጠት ያስፈልጋል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል። በስዊዘርላንድ ዳቮስ፣ እየተካሄደ በሚገኘውን የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ ከተገኙት የውህደት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት የቁስጥንጥንያ ፓትሪያርክ ባርቶሎሜዎስ ቀዳማዊ እና በሞስኮ የአይሁድ እምነት መምህር ከሆኑት ጎልድስሚድ ጋር ሆነው ባቀረቡት ጥሪ የዓለም መንግሥታት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በጋራ የምንኖርባትን ዓለም ከጥፋት መታደግ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የምንኖርባት ምድራችን እንዲሁም በእርሷ የሚኖሩ ድሃ ሕዝብ የስቃይ ድምጹን በማሰማት ላይ ይገኛሉ በማለት በስዊዘርላንድ-ዳቮስ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ መልዕክት ያስተላለፉት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በዳቮስ በመካሄድ ላይ በሚገኝ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ላይ እንዲገኙ፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን ያነሳሳቸው ቀዳሚ ዓላማ፣ የዓለም መንግሥታት መሪዎች የገንዘብ አቅማቸውን ሆነ ጉልበታቸውን በማስተባበር፣ በምድራችን ላይ ለተከሰተው አስፈሪ የሥነ ምሕዳር ለውጥ መልስ እንዲሰጡ ለማሳሰብ ነው ብለዋል።

የሥነ ምሕዳር ለውጥን ለመላው ዓለም ማስገንዘብ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐርዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ የምድራችንን ስቃይ እና የድሆችን ጩሄት ሰምቶ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል በማለት ያቀረቡትን መልዕክት ያስታወሱት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ሁላችንም በጋራ ሃይላችንን በማስተባበር የምድራችንን ስቃይ ማስታገስ ይኖርብናል ብለዋል። ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ከማድረግ ሊያግዱን አይገባም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቅም የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት፣ ነዋሪዎቿንም ከጉዳት መታደግ ያስፈልጋል ብለው፣ ይህችን የምንኖርባትን ምድር ከጉዳት ጠብቀን፣ የሚገባትን እንክብካቤ ካላደረግንላት ሌላ መኖሪያ ምድር የለንም በማለት፣ በስዊዘርላንድ ዳቮስ፣ ከጥር 12-15/2012 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ በሚገኝ የዓለም የኤኮኖሚ መድረክ ንግግራቸውን አሰምተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
23 January 2020, 16:07