በላምፔዱሳ ወደብ በስደተኞች ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል፣ በላምፔዱሳ ወደብ በስደተኞች ላይ ከሚደርሱ አደጋዎች መካከል፣  

ሕይወትን መታደግ ሕጋዊ ግዴታ መሆኑ ተነገረ።

በሮም ከተማ የሚገኝ አስታሊ የተባለ የስደተኞች መርጃ ማዕከል መዲቴራኒያን ባሕር ላይ የሚያጋጥም የሞት አደጋ እንዲቆም አሳሰበ። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኢየሱሳዊያን ማሕበር የስደተኞች መርጃ ማዕከል በማሳሰቢያው በአመጽ እና በጦርነት ውስጥ ከሚገኙ አገሮች ለሚሰደዱት ስደተኞች ሰብዓዊ ዕርዳታን ማዳረስ የሚቻልበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቆ በሊቢያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች ወደ ሚፈልጉበት አገር እንዲደሩስ የሚፈቅድ ሕጋዊ የጉዞ መስመር እንዲመቻች ጠይቋል። የማዕከሉ ፕሬዚደንት የሆኑት ክቡር አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዓለማችን ለሚታየው ግድ የልሽነት ዓለም አቀፍ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።  

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሜዲቴራኒያንን ባሕር በሚያቁርጡት ስደተኞች ላይ የሚደርስ የሞት አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ በዓለም አቀፍ ሚዲያ አይገለጽም በማለት የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ቅሬታውን አሰምቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በመስከረም ወር 2016 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር የበርካታ ስደተኞች ሕይወት በሜዲቴራኒያን ባሕር ውስጥ እንደሚቀጠፍ መግለጻቸውን ማዕከሉ አስታውሶ አደጋው እንዲገታ አሳስቧል።

በላምፔዱሳ የ5 ሰው ሕይወት መጥፋቱ እና የ15 ስዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገልጿል፣

ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 13/2012 ዓ. ም. ከደቡብ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ከሆነችው ላምፔዱሳ በትንሽ ርቀት ላይ በደረሰ የመርከብ አደጋ ከሊቢያ ተሳፍረው ወደ ኢጣሊያ ይጓዙ በነበሩ 169 ስደተኞች ላይ አደጋ መድረሱ ይታወሳል። በአደጋ የ5 ሰው ሕይወት መጥፋቱ፣ 15 ስዎች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል። የደቡብ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ከንቲባ ሳልምቫቶሬ ማርቴሎ የአደጋውን አስከፊነት ጠቅሰው ባደርጉት ንግግር በአደጋው ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን በሐዘን እያስታወሱ ከአደጋው ለተረፉትም አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ መሞት ይብቃ፣

በሮም ከተማ የሚገኝ የኢየሱሳዊያን ማህበር የእርዳታ መስጫ ማዕከል በበኩሉ በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ የሚከሰት የሰው ሕይወት መጥፋት ለማስቆም ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ፣ የተቀናጀ መፍትሄ እንዲገኝለት አሳስቦ ግድ የለሽነትን በማስቀረት የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ መታደግ እና ተቀብሎ ማስተናገድ ለአውሮፓ ሕብረት አገሮች መንግሥታት የፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታ ነው በማለት በጋዜጣዊ መግለጫው አስታውቋል። አውሮፓ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን እና ውሎችን በተደጋጋሚ እየጣሰ ይገኛል ያለው የአስታሊ የስደተኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ይህ የለዘብተኝነት አቋም ባስቸኳይ እንዲቀየር ጠይቀዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመላዋ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልጋይ ሆነው በተመረጡ በአንድ ዓመት ውስጥ በሲሲሊ ክፍለ ሀገር፣ የወደብ ከተማ የሆነችውን ላምፔዱሳ በጎበኙበት ወቅት ያደረጉትን ንግግር የጠቀሰው የማዕከሉ ጋዜጣዊ መግለጫ ቅዱስነታቸው በንግግራቸው “ከእንግዲህ ወዲይ የሰው ሕይወት በሜዲቴራኒያን ባህር ላይ መሞት የለበትም” ማለታቸውን አስታውሷል። ማዕከሉ በመግለጫው ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰቢያ በአውሮፓ ሕብረት አገሮች መንግስታዊ ተቋማት መካከል በተግባር ሊተረጎም ይገባል በማለት ዋና ጽሕፈት ቤቱን በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ላይ ያደረገው የኢየሱሳዊያን ማሕበር የስደተኞች መርጃ ማዕከል አሳስቧል።

በዓለማችን የሚታየውን ግድ የለሽነት መዋጋት ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ “የግድ የለሽነት ስሜት በልባችን ውስጥ ሥፍራን እያገኘ መጥቷል እና አጥብቀን መዋጋት ይኖርብናል” ያሉትን በመጥቀስ አስተያየታቸውን ለቫቲካን ሬዲዩ የገለጹት በሮም የአስታሊ የስደተኞች አገልሎት መስጫ ማዕከል ፕሬዚደትን ክቡር አባ ካሚሎ ሪፓሞንቲ፣ ግድ የለሽነትን በማስቀረት የሰውን ሕይወት ከሞት አደጋ መታደግ እና ተቀብሎ ማስተናገድ ለአውሮፓ ሕብረት አገሮች መንግሥታት የፖለቲካ ምርጫ ሳይሆን ሕጋዊ ግዴታ ነው ብለው፣ ስደተኞች ወደሚፈልጉበት አገር መግባት እንዲችሉ የሚያደርግ ሕጋዊ የጉዞ መስመር እንዲከፈትላቸው ጠይቀዋል። ስለሆነም ህጋዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሲደርሱ በሕጋዊ መንገድ ሥራን የማግኘት እና ሰብዓዊ ክብራቸውንም የሚያስጠብቁበት መንገድ ይሆናል ብለዋል።

በሊባኖስ ለሚገኙት ስደተኞች አዲስ የመተላለፊያ መንገድ ተፈጠረ፣

በሊባኖስ ውስጥ ለተቀመጡት ስደተኞች በተፈጠረው አዲስ የመተላለፊያ መንገድ ትናንት ህዳር 17/2012 ዓ. ም. 113 የሶርያ ስደተኞች ወደ ሮም መድረስ መቻላቸው ታውቋል። የጉዞ መስመርን ያመቻቹላቸው በሮም ከተማ የሚገኙ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በኩል የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር፣ በጣሊያን የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ፌደሬሽን እና የቫልደሰ ቤተክርስቲያን ሕብረት በጋራ ሆነው ከጣሊያን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት ስምምነት መሆኑ ታውቋል። ከሊባኖስ ተነስተው ወደ ሮም መድረስ የቻሉት 1,800 የሶርያ ስደተኞች በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ የእርዳታ አቅራቢ ማሕበራት፣ በቁምስናዎች እና በቤተስቦች በኩል እገዛ የሚደረግላቸው መሆኑ ታውቋል። ጎልማሶች ወደ የቋንቋ ትምህርት እንዲገቡ፣ ሕጻናት ወደ ሕጻናት መንከባከቢያ እንዲገቡ፣ ሕጋዊ የስደተኞች መታወቂያ ሲዘጋጅ የሥራ ዕድል የሚመቻችላቸው መሆኑ ታውቋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 November 2019, 15:36