የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ዓለምን እንደ አንድ የጋራ መኖሪያችን መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ።

በስፔን ዋና ከተማ ማድሪድ፣ ከመስከረም 4-6/2012 ዓ. ም. በተካሄደው “ጸሎት ለሰላም” ስብሰባ የተካፈሉት የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች ዓለምን እንደ አንድ የጋራ ቤታችን መመልከት እንደሚያስፈልግ ጥሪያቸውን አቀረቡ። ዘንድሮ ለ33ኛ ጊዜ የተካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ “ሰላም በድንበር ሳይከለል በሐይማኖት ተቋማት እና በባሕሎች መካከል በሚደርግ ውይይት በመታገዝ በሁሉም አካካባቢ ሊገለጽ ይገባል በማለት ስብሰባውን ያዘጋጀው እና ዋና መቀመጫውን በሮም ከተማ ያደረገ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማሕበር አስታውቋል። በሚቀጥለው ዓመት ሊካሄድ የታቀደው እና የሐይማኖት ተቋማትን የሚያሳትፍ ዓለም አቀፍ በሮም ከተማ እንደሚደረገ ማሕበሩ አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በማድሪድ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አልሙዴና አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ያሰሙት የጉባኤው ተካፋዮች፣ እንደ ሰው ሊኖራቸው የሚገባውን መልካም ሕይወት የተነፈጉ፣ ሰው መሆናቸውም የተረሳ በርካታ ሰዎች በዙሪያችን አሉ ብለዋል። በማድሪድ ከተማ ስብሰባቸውን ያካሄዱት፣ ከዓለም ዙሪያ የመጡ የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ሌሎችም የስብሰባው ተካፋዮች በሙሉ፣ በዓለማችን ውስጥ በድህነት ሕይወት የሚሰቃዩ፣ በዘር፣ በቋንቋ እና በሐይማኖት ልዩነት ብቻ ግፍ የሚፈጸምባቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። የጋራ መኖሪያ የሆነች ዓለማችንን መጠበቅን እና መንከባከብ ያስፈልጋል በማለት ጥሪያቸውን ያስተላለፉት የሰብሰባው ተካፋዮች በማከልም የመጭው ትውልድ ዕጣ ፈንታ እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረው ምክንያቱንም ሲገልጹ የምንኖርባት ዓለማችን ባሁኑ ጊዜ የሁላችን መኖሪያ ቤታችን መሆኗ ቀርቶ፣ ርህራሄ በጎደለ መልኩ እያወደሟት እና እየበዘበዟት የሚገኙ የጥቂቶች ብቻ ትመስላለች ብለው አንዳንድ አገሮች ጫናን በመፍጠር እና ሃይልንም በመጠቀም በዓለማችን ላይ በታሪክ ያልታየ ውድመት እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል። የስብሰባው ተካፋዮች በማከልም በዓለማችን ከፍተኛ የሰው፣ የንብረት እና የተፈጥሮ ጥፋትን እያስከተለ ያለው የሽብር ተግባርም አልተገታም ብለው ይህ የሆነበትም ሰላም በመዘንጋቱ ነው ብለዋል። እነዚህ እና ሌሎች ትላልቅ ችግሮችም ሊፈቱ የሚችሉት በጋራ ውይይት ነው ብለዋል። ለሃይማኖት አክራሪነት ዕድል መስጠት የለብንም ያሉት የሕይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በእግዚ አብሔር የሚያምን ሁሉ፣ የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችን፣ ሕዝቦች ተሳስበው በቤተሰባዊ ፍቅር አብረው የሚኖሩባት እንጂ፣ በቂ ሕክምናን ሳያገኙ ቀርተው በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕጻናት የሚሞቱባት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የትምህርት ዕድልን ሳያገኙ የሚያድጉባት መሆን የለባትም ብለዋል። በጋራ በምንኖርባት ምድራችን የሕዝቦች አንድነት ያስፈልጋል ያሉት የቅዱስ ኤጂዲዮ ማህበር መስራች ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ በተለይም በአማዞን ግዛት ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ አስረድተው፣ ዛሬ ሥነ ምህዳራዊ ጥያቄ በሁሉም ዘንድ ተደማጭነትን አግኝቶ ተገቢ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።     

ስነ ምሕዳርን መጠበቅ እና መንከባከብ የተወሰኑ ሰዎች ወይም አገሮች ሃላፊነት እንደሆነ ይቆጠር እንደነበር ያስታወሱት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ ሐቁ ግን በእያንዳንዳችን አገር የታየው የአየር ለውጥ፣ የዝናብ እጥረትን በማስከተል የምንኖርበትን አካባቢ ወደ በረሃማነት እየቀየርው ይገኛል ብለዋል። በአንዳንድ አገሮች በሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ሰዎች የሚኖሩበትን አካባቢ ለቀው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰደዱ ተገደዋል ብለው ይህን ችግር ለመቀነስ የስነ ምሕዳር እንክብካቤን በማስመልከት ለዓለማችን ሕዝቦች በሙሉ ግንዛቤን መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ግንዛቤን ለመስጠትም በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ ውይይት አንደኛው መንገድ መሆኑን ያስረዱት አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ ምክንያቱም ሐይማኖቶች በሙሉ ምድር የሰው ልጆች እንዲኖሩባት የተፈጠረች የጋራ መኖሪያ መሆኗን ስለሚያምኑበት ነው ብለዋል። አቶ አንድሬያ በማከልም በማድሪድ የተካሄደው ስብሰባ ስነ ምሕዳርን በመንፈሳዊ አቅጣጭ የተመለከተው ቢሆንም፣ ይህን መንፈሳዊ አቅጣጫን ከፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ አቅጣጫ ለይቶ መመልከት አይቻልም ብለዋል። 

ስለ ግሎባላይዜሽን ብዙ የሚነገር መሆኑን ያስታወሱት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ፣ ግሎባላይዜሽን አገራትን በዋነኛነት በንግድ እና በምጣኔ ሃብት ለማገናኘት ያለመ ከመሆኑ ባሻገር የፖለቲካ እና የሐይማኖት አንድነትን ለማምጣት የቆመ ባለመሆኑ ሰላምን ከማስፈን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ብለዋል። ይባስ ብሎ ግሎባላይዜሽን በአግሮች እና በሕዝቦች መካከል ስጋትን በመፍጠር ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ አድርጓቸዋል ያሉት አቶ አንድሬያ ሪካርዲ አገርን እና ሕዝብን ከመከፋፈል ይልቅ አንድ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። የአማዞን ደኖች ቃጠሎ ሁላችንንም ይመለከታል ያሉት አቶ አንድሬያ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይም ቢሆን ትክክለኛ ምላሽን የሚያገኘው አገሮች ድንበሮቻቸውን ሳይዘጉ በጋራ ሆነው በሚያገኙት የመፍትሄ ሃሳብ እንጂ አንድ አገር ብቻውን የሚፈታው ችግር አለመሆኑን አስረድተዋል። በአንድ አገር የሚነሳ ጦርነት ለጎረቤት አገራትም ይተርፋል ያሉት አቶ አንድሬያ ሪካርዲ የሶርያን ጦርነት እንደ ምሳሌ ጠቅሰው፣ በጦርነቱ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው የሚሰደዱት ስደተኞች ለጎረቤት አገሮች፣ ለአውሮጳ፣ ለቱርኪያ እና ለዮርዳኖስ የተለያዩ ችግሮችን ፈጥረዋል ብለዋል።        

19 September 2019, 18:19