መርከቧ ወደ ኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነችው የላምፔዱሳ ወደብ መድረሷ፣ መርከቧ ወደ ኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነችው የላምፔዱሳ ወደብ መድረሷ፣ 

በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የቆየች መርከብ ወደ ላምፔዱሳ ወደብ መድረሷ ተገለጸ።

46 ስደተኞችን ከሞት አደጋ በማትረፍ የነፍስ አድን እርዳታን ስታቀርብ የቆየች መርከብ ወደ ኢጣሊያ ግዛት ወደ ሆነችው ላምፔዱሳ ወደብ መድረሷ ታውቋል።

በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ የነፍስ አድን እርዳታን የሚማጸኑ ስደተኞችን ከሞት አደጋ በማትረፍ የምትታወቅ አሌክስ የተሰኘች መርከብ ያለፈው ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ. ም. ከምሽቱ 12 ሰዓት ገደማ የኢጣሊያ የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ላምፔዱሳ መድረሷ ታውቋል። አሌክስ የሚል ስያሜ የተሰጣት ይህች መርከብ ባሁኑ ሰዓት በኢጣሊያ የባሕር ክልል ውስጥ ብትገኝም መርከቧ ያሳፈረቻቸውን ስደተኞች በላምፔዱሳ ወደብ ላይ ማሳረፍ የሚያስችላትን ፍቃድ ከኢጣሊያ መንግሥት አለማግኘቷ ታውቋል። ስደተኞቹ የሚገኙበትን የጤና ሁኔታ የሚያጣራ የሕኪሞች ቡድን ብቻ ወደ መርከቧ ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ አሌሳንድሮ ዲ ቡሶሎ የላከልን ዘገባ አመልክቷል። ዘገባው በማከልም መርከቧ ወደ ላምፔዱሳ ወደብ የገባችው ከዚህ በፊት በኢጣሊያ መንግሥት ስደተኞችን ያሳፈረ ማንኛውም መርከብ ወደ ወደቡ እንዳይገባ በማለት ያስቀመጠውን ደንብ በመጣስ መሆኑን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ስደተኞች ከመርከቧ እንዳይወርዱ ፖሊሶች ከልክለዋቸዋል።

የመርከቧ ቃለ አቃባይ ወይዘሮ አሌሳንድራ ሹርባ፣ በመርከቧ ውስጥ ለሚገኙት ስደተኞች አስፈላጊውን ዕርዳታ መንፈግ ትክክል አይደለም በማለት ክስ ያቀረብቡ ሲሆን ስደተኞች በመርከቧ ውስጥ ከሚሰጣቸው እርዳታዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰብዓዊ እገዛዎችንም በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የመርከቡ ዕርዳታ አቅርቦት አገልግሎት አስተባባሪ እና የኢጣሊያ ፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ሌው ኤራዝሞ ፓላሶቶ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የስደተኞችን የጤና ሁኔታ የሚመለከት አንድ ሐኪም ወደ መርከቧ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች ብቻ በወደቡ የሚገኘውን የመጸዳጃ አገልግሎትን ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።

መርከቧ ወደ ወደቡ የገባችው አስቸኳይ የዕርዳታ አቅርቦታ በማስፈለጉ ነው፣

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በቂ የመጸዳጃ ቦታ እና የሕይወት ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ላይ ለሚገኙት ስደተኞች አስቸኳይ እገዛን በመፈለግ ወደ ወደቡ መግባት የግድ እንደነበር በመርከቧ ውስጥ በእርዳታ አቅርቦት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰራተኞች ገልጸዋል። ይህ ባይደረግ ኖሮ በመርከቧ ውስጥ የነበሩትን ስደተኞች ወደ ማልታ ደሴት ለማጓጓዝ እንገደድ ነበር ብለዋል።

በሌላ ወገን 65 ስደተኞችን ያሳፈረች የጀርመን ነፍስ አድን መርከብ ወደ ኢጣሊያ የወደብ ከተማ ወደ ሆነችው ላምፔዱስ መቃረቧ ታውቋል። የጀርመን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሲሆፈር ከሁለቱ የነፍስ አድን መርከቦች የተወሰኑ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የጀርመን መንግሥት ፈቃደኛ መሆኑን ለኢጣሊያው አቻቸው ለአቶ ሳልቪኒ ገልጸው የኢጣሊያ መንግሥትም ተመሳሳይ ትብብር እንዲያሳይ ጠይቀዋል። የጀርመኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሲሆፈር ለኢጣሊያው አቻቸው ለአቶ ሳልቪኒ በላኩት መልዕክት ስደተኞችን ላለመቀበል ብለው ያደረጉትን ውሳኔ መልሰው እንዲያጤኑት በትሀና ጠይቀው ጀርመን እና ኢጣሊያ የአውሮጳ ሕብረት የመሠረቱት አገሮች እንደመሆናቸው መጠን የስደተኞችን ጉዳይ በጋራ በመመልከት፣ በሜዲቴራኒያን አካባቢ የሚታየውን የስደተኞች ችግር በጋራ ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።  የኢጣሊያው የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሳልቪኒ ለመርከል መንግሥት በላኩት ጥብቅ መልዕክታቸው መንግሥታቸው ለሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች የሚያደርገውን ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስበው፣ ለስደተኞች እርዳታን እንሰጣለን በማለት የኢጣሊያ መንግሥት ያወጣውን ደንቦችን በመተላለፍ ላይ የሚገኙ ዜጎቻቸውን ወደ አገራቸው እንዲመልሱ አሳስበዋል። 

አውሮጳ የስደተኞችን ጉዳይ በአግባቡ ማስፈጸም አልቻለም፣

ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ የተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ፣ የአውሮጳ ሕብረት የስደተኞችን ሁኔታ በዝርዝር ተመልክቶ ጉዳዩን በአግባቡ ማስፈጸም አልቻለም በማለት ኮንኖታል። የቅድስት መንበር ጋዜጣ ሎዘርቫቶሬ በእትሙ እንዳብራራው የድሕነት እና የሰዎች ኑሮ አለመመጣጠን በሚታይበት ባሁኑ ወቅት የባሕር እና የብስ ድንበሮችን መዝጋት የችግሩ መፍትሄ ሊሆን አይችልም ብሏል። 

08 July 2019, 16:38