ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ፣ ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ፣ 

የአፍሪቃ አገሮች በዓለም ግዙፉን የነጻ ገበያ ስምምነት ሊያጸድቁ መዘጋጀታቸው ተገለጸ።

ላለፉት አራት ዓመታት ውይይት ሲደረግበት የቆየው የመላው አፍሪቃ ነጻ ገበያ እቅድ ተግባራዊነት ወደ ስምምነት ላይ መቃረቡን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ሮቤርቶ አርቲጃኒ የላከልን ዘገባ ገልጿል። ስምምነቱን ይፈርማሉ ተብሎ ከሚጠበቁት የመጨረሻዎቹ አገሮች መካከል ናይጀሪያ እና ቤኒን ያላፈው እሁድ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ. ም. መፈረማቸው የታወቀ ሲሆን ስምምነቱን ለመቀበል ፈቃደኛነቷን እንድትገልጽ የምትጠበቅ የመጨረሻዋ አገር ኤርትራ ብቻ መሆኗ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ኮምቦኒ ዓለም አቀፍ የካህናት ማሕበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ እንደገለጹት እቅዱ የአፍሪቃ አገሮችን በኤኮኖሚ የሚያስተሳስር የገበያ ሥርዓትን የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት “ኮሜሳ” ወይም የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ አባል አገሮች በመባል የሚታወቅ ሕብረት መመስረቱን አስታውሰው የአሁኑ ግን መላውን የአፍሪቃ አገሮችን የሚያሳትፍ መሆኑን ገልጸው እርምጃው ጠቃሚ ይሆናል ብለዋል።

ችግሮችን መጋፈጥ ያስፈልጋል፣

የአፍሪቃ አገሮች ያጋጠማቸውን የተለያዩ ችግሮች፣ ከእነዚህ መካከል የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት መጨመር፣ እስካሁን ድረስ በመሠረታዊነት ከአገልግሎት አቅርቦት ጋር የተገናኙ ችግሮችን፣ የጥሬ እቃዎች፣ የማዕድን እና የኢነርጂ ሀብቶች፣ በቅድሚያም የነዳጅ ዘይት ምርት ማሳደግን የተመለከቱ ናቸው ብለዋል። አባ ጁሊዮ ቀጥለውም በሁሉም የአፍሪቃ አገሮች ዘንድ እያደገ የመጣው የውጭ ዕዳ አህጉሩን ያስጨነቀው ሌላው ችግር ነው ብለው፣ የአፍሪቃ አገሮች ችግር በመጠኑም ለመቅረፍ ተብሎ ከ15 ዓመት በፊት የዓለም ባንክ፣ የአፍሪቃ እድገት ባንክ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ የዕዳ ቅነሳ ማድረጋቸውን ወይም ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸውን አስታውስው ባሁኑ ጊዜ ግን ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ብቻ የዕዳ ጫና ወደ 700 ቢልዮን ዶላር አካባቢ ማደጉን ጠቁመዋል። ጉዳዩ ያሳስባል ያሉት አባ ጁሊዮ ዕዳው የወለድ ክፍያንም የሚያጠቃልል እና የአክሲዮን ገበያን ግምታዊ ዋጋን የተከተለ በመሆኑ የአፍሪቃ አገሮችን በታላቅ ችግር ላይ የሚጥል ሥርዓት በመሆኑ ያሳስባል ብለዋል።

ጉዳዩ አውሮጳንም ይመለከታል፣

ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መመልከት ያስፈልጋል ያሉት አባ ጁሊዮ በማከልም የአውሮጳ የኢኮኖሚ አጋርነት በሚል ዕቅድ ደቡባዊውን የዓለማችን ክፍል በልማት አጋርነት ለማሳተፍ ያደረገችው ስምምነት በተለይም የምርት አቅርቦትን በተመለከተ በኢንዱስትሪ ከበለጸጸጉ የአውሮጳ አገሮች ጋር በምንም መልኩ መወዳደር የማይችሉ በርካታ የአፍሪቃ አገሮችን ችግር ውስጥ መጣሉን አስረድተዋል።     

አፍሪቃ ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አህጉር፣

መላው የአፍሪቃ አገሮች የነጻ ገበያ ሥርዓትን ለማዋቀር መስማማታቸው ተስፋን የሚሰጥ ቀዳሚ እርምጃ ነው ያሉት አባ ጁሊዮ ነገር ግን አፍሪቃን ወደ ኢንዱስትሪ እድገት ለማድረስ የሚደረግ ጥረት በቂ መሠረተ ልማት ካለመኖሩ የተነሳ ብዙ ይቀረዋል ብለው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተሰርተዋል የሚባሉ መሠረተ ልማቶችም ቢሆኑ በቻይና ሕዝባዊት ሪፓብሊክ መንግሥት ድጋፍ የተቋቋሙ ናቸው ብለዋል። አፍሪቃ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብት ያላት አህጉር ቢትሆንም ይህን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ሕዝቦቿ ዘንድ ለማድረስ አሁንም ረጅም መጓዝ እንደሚያስፈልግ አባ ጁሊዮ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ስደት እና የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ፣

አባ ጁሊዮ በገለጻቸው እንዳስረዱት በዓለማችን ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች ያሳዩት የዕድገት ምልክቶች በስደተኞች እገዛ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ብለዋል። የስደተኞች ጉዳይ በኢጣሊያ ውስጥ በተሳሳተ እና በተጋነነ መልኩ ይገለጻል ያሉት አባ ጁሊዮ መረጃዎችን በመመልከት ብቻ በዓለማችን ከሚከሰቱ የሰዎች መሰደድ 75 ከመቶ የሚሆነው በአፍሪቃ አህጉር ውስጥ ነው ብለው ይህም ወደ 24 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ነው ብለዋል። የስደተኞች እንቅስቃሴ በእርግጥ ወደ ሰሜናዊው የዓለማችን ክፍል ያዘነብላል ያሉት አባ ጁሊዮ በቁጥር በርካታ የአውሮጳ ሕዝብ በዕድሜ እየገፋ መምጣቱን እና አዲስ ጉልበት እያስፈለገ መምጣቱን  የፖለቲካ ሥርዓታችን ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በመጪዎቹ አመታት ከአፍሪቃ ውስጥ የሚሰደድ የሕዝቦች ቁጥር በፍጥነት የሚጨምር መሆኑን የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ሪፖርት ያመለከተ መሆኑን አባ ጁሊዮ አስታውቀዋል። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት መሠረት በጎርጎሮሳዊያኑ 2050 ዓ. ም. የአፍሪቃ ሕዝብ ቁጥር ወደ 2.4 ቢሊዮን እንደሚደርስ፣ በ2100 ደግሞ ወደ 4 ቢሊዮን እንደሚደርስ የተገመተ ሲሆን ለኑሮ ተስማሚ የሆነ ሥፍራን ፍለጋ የሕዝቦች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ የማይቀር በመሆኑ ይልቅስ መንግሥታት ይህን ክስተት የሰዎችን የጋራ ጥቅምን እና ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ ማስተናገድ እንደሚያስፈልግ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ኮምቦኒ ዓለም አቀፍ የካህናት ማሕበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ጁሊዮ አልባኔዘ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 July 2019, 16:59