ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኢጣሊያ የአካል ጉዳተኞች ማህበር አባል ጋር ሰላምታን ሲለዋወጡ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከኢጣሊያ የአካል ጉዳተኞች ማህበር አባል ጋር ሰላምታን ሲለዋወጡ፣  

በዓለማችን በዓመት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በሥራ ዘርፍ በሚደርስ ድንገተኛ አደጋ እንደሚሞቱ ተገለጸ።

ትናንት እሑድ ሚያዝያ 20/2011 ዓ. ም. የሥራ ቦታ የደህንነት ዋስትናን የሚያስከብር ዓለም አቀፍ ቀን ታስቦ መዋሉ ታውቋል። ዕለቱ በየዓመቱ ያስቦ እንዲውል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተደነገገ መሆኑ ታውቋል። ዕለቱን ምክንያት በማድርግ በኢጣሊያ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ፍራንኮ ቤቶኒ በሥራ ገበታ ላይ የሚደርሰውን የአካል እና የሕይወት አደጋ የመከላከል ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማችን ዙሪያ በየዓመቱ ወደ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ እንደሚሞቱ፣ ከ374 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ አደጋ ድንገተኛ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት አስታውቆ በሠራተኞች ላይ ከሚደርሱ ድንገተኛ አደጋዎች መካከል አብዛኛዎችን መከላከል የሚቻል መሆኑንም አስታውቋል።

በማደግ ላይ ያለ ጉዳት ነው፣

ጉዳቱ በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ በበለጸጉ በምዕራቡ ዓለምም ያለ መሆኑ ታውቋል። ባለፈው ዓመት በኢጣሊያ ውስጥ 641 ሺህ ሠራተኞችን በሥራ ገበታ ላይ እያሉ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ሲነገር ይህም ካለፈው የጎርጎሮሳዊው 2017 ዓ. ም. ጋር ሲነጻጸር በ0.9 የጨመረ መሆኑ ተስተውሏል። የበለጠ የሚያሳስበው በሥራ ገበታ በሚያጋጥም ድንገተኛ አደጋ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 10 ከመቶ ማደጉ ነው ተብሏል። ባለፈው የጎርጎሮሳዊው 2018 ዓ. ም. ብቻ በኢጣሊያ ውስጥ በሥራ ገበታ ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1, 133 መሆኑን የአገሩ የሠራተኞች የሕይወት ዋስትና ማሕበር አስታውቋል።

በግብርናው ዘርፍ አደጋው የበለጠ ነው፣

በኢጣሊያ ውስጥ በሚገኙ ምርት አቅራቢ ድርጅቶች ውስጥ በሠራተኛ ላይ ከፍተኛ የሞት አደጋን በማድረስ ከሚታወቁ የሥራ ዘርፎች መካከል የግብርናው መስክ በቅድሚያ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በመቀጠልም የሕንጻ ሥራዎች፣ የማዕድን ኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት እና የምርት ማከማቻ ዘርፎች መሆናቸው ታውቋል። በኢጣሊያ ውስጥ በሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካል እና የሕይወት አደጋ ከሚደርስባቸው ክፍላተ ሀገር መካከል የኮርቶኔ ክፍለ ሃገር በቅድሚያ የሚጠቀስ መሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሠራተኞች ተገቢ ጥበቃ ሊደረግ ይገባል፣ ሰራተኞች ማሕበር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመስከረም 10 ቀን 2011 ዓ. ም. የኢጣሊያ የአካል ጉዳተኞች ሕብረት ሥራ ማሕበር አባላትን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ማሕበሩ በሥራ ላይ በሚያጋጥም አደጋ ይሁን በሕመም ምክንያት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸው ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸው በተጨማሪም የአካል ጉዳተኞቹ በደረሰባቸው የአካል መጓደል ምክንያት  የሚሰማቸውን ሐዘን አስታውሰው ይህም በቤተሰቦቻቸው ላይ ሊያስከትል የሚችለው የኑሮ ቀውስ እንዳለ ማስረዳታቸው የሚታወስ ነው።

የጋራ ትብብር እና ድጎማ ሊኖር ይገባል፣

ቅዱስነታቸው ከመንግሥት በኩል የአካል ጉዳተኞችን ለመደጎም የሚደረግ ጥረት መልካም ተግባር እንጂ አካል ጉዳተኞችን የሕብረተሰብ ሸክም ለማድረግ የሚወሰድ ውሳኔ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ማለታቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማሕበራዊ አስተምህሮን በማስታወስ በጋራ ትብብርና በመስግሥት ድጎማ መካከል ሚዛናዊ እኩልነት ሊኖር ይገባል ብለው ለአካል ጉዳተኞች የሚደረግ ድጎማ ተረጂዎች ማከናወን በሚችሉት የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ለዓለማችን እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ እንጂ የሚያሰንፍ መሆን የለበትም ማለታቸው ይታወሳል።

የአካል ጉዳተኞችን ማሕበራዊ ሕይወት ለማሻሻል የጋራ ትብብር ሊኖር ይገባል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አላስፈላጊ ወጭን ለመቀነስ በማለት የሥራ ዕድሎችን ማጥበብ ወጣቱን ትውልድ የበለጠ እንደሚያሳስብ ገልጸው ቢሆንም ለሥራ አጥ ሰዎች የሚደረግ ማሕበራዊ ድጋፍ መቀነስ የለበትም ብለዋል። በኢጣሊያ የአካል ጉዳተኞች ማሕበር ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ፍራንኮ ቤቶኒ በሥራ ገበታ ላይ የሚደርሰውን የአካል እና የሕይወት አደጋ ለመቀንስ ጥረት የሚያደርግ አዲስ ትውልድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።  

29 April 2019, 16:30