PAKISTAN BLASPHEMY ASIA BIBI CASE PAKISTAN BLASPHEMY ASIA BIBI CASE 

በፓክስታን እስላማዊ የፓለቲካ ግንባር የተቃውሞ ሰልፎችን እያካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡትም በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎች መንገዶችን መዝጋታቸው፣ በርካታ መኪኖችን በእሳት ማጋየታቸው ታውቋል። እስላማዊ ፓርቲው ሌሎችን መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ እያስተባበረ መሆኑ ታውቋል። የፓክስታን የጸጥታ አስከባሪዎችም በቁጥር ትንሽ የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከጥቃት ለመከላከል ተሰማርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የእስምናን ሕይማኖት አንቋሽሻለች፣ የነብዩ መሐመድን ስም አጥፍታለች በሚል የወንጀል ክስ፣ የሞት ፍርድ የተፈረዳባትን አሲያ ቢቢን፣ የፓክስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ. ም. ነጻ ማሰናበቱን ተከትሎ የአገሩ እስላማዊ የፓለቲካ ድርጅት የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄዱ ታውቋል። የክርስትና እምነት ተከታይ አሲያ ቢቢ ለስምንት ዓመታት በእስር መቆየቷ ታውቋል። ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡትም በራካታ የፓርቲው ደጋፊዎች መንገዶችን መዝጋታቸው፣ በርካታ መኪኖችን በእሳት ማጋየታቸው ታውቋል። እስላማዊ ፓርቲው ሌሎችን መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎችን ለማካሄድ እያስተባበረ መሆኑ ታውቋል። የፓክስታን ጸጥታ አስከባሪዎችም በቁጥር ትንሽ የሆኑ የክርስትና እምነት ተከታዮችን ከጥቃት ለመከላከል መሰማራታቸው ታውቋል።

በ2002 ዓ. ም. በአሲያ ቢቢ ላይ ክስ የመሰረቱት የእስላማዊ ፍርድ ቤት ጠበቃ፣ መሐመድ ሳሊም፣ ለአገሩ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ መለታቸው ታውቋል። የፓክስታን ጠውቅላይ ፍርድ ቤትም የመሐመድ ሳሊም ይግባኝን ተቀብሎ እየተመለከተው መሆኑን በኢጣሊያ የፓክስታን ክስቲያቲያኖች ሕብረት መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ በማከልም ይግባኝ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቅረብ እንጂ አሲያ ቢቢ ተመልሳ በቁጥጥር ስር እንድትውል የሚል ትዕዛዝ ኣስካሁን አለመተላለፉን ገልጸዋል።

መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ትክክል እንደሆነ አቋሙን ገልጿል፣

የእስላማዊ ፍርድ ቤት ጠበቃ፣ መሐመድ ሳሊም፣ ግለ ሰቧ ከአገር እንዳትወጣ የሚያግድ ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ መንገሥትን መጠየቃቸው ታውቋል። በኢጣሊያ የፓክስታን ክስቲያቲያኖች ሕብረት መስራች የሆኑት ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ፣ የፓክስታንን መንግሥት አቋም ጠቅሰው ባደረጉት ገለጻቸው የፓክስታን መንግሥት አሲያ ቢቢብን ከወንጀል ነጻ ለማድረግ በወሰደው እርምጃ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌለው፣ አሲያ ቢቢም ከአገር እንዳትወጣ የሚል ትዕዛዝ አለማስተላለፉን ገልጸዋል።

የተቃውሞ ሰልፎች ይቀጥላሉ፣ አሲያ ቢቢ የክርስትና እምነት ትልቅ ምልክት ሆናለች፣

አሲያ ቢቢ በእስላማዊ ፍርድ ቤት በኩል በደል የደረሳባት ብትሆንም ነገር ግን ቁጥራቸው ትንሽ በሆኑት የፓክስታን ክርስቲያኖች መልካከል ተጠቃሽ ምልክት ሆናለች። የአገሩ እስላማዊ የፖለቲካ ግንባር ዋና ዓላማ ቁጥራቸው ትንሽ በሆኑት የፓክስታን ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖን የሚፈጥር ሕገ መንግሥትን ለማርቀቅ፣ ቀጥሎም ቢቻላቸው ደግሞ ክርስቲያኖችን ከአገሩ ለማባረር የተደረገ ሴራ እንደሆነ ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ አስረድተዋል። የአገሩ እስላማዊ የፖለቲካ ድርጅት፣ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለውን ሕዝብ የሚያሳትፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ እያስተባበረ መሆኑ የታወቀ ሲሆን መንግሥትም በበኩሉ የክርስቲያን ማሕበረሰብ በብዛት በሚኖሩበት አካባቢዎች የጸጥታ አስከባሪ ሃይልን ማሰማራትቱ ታውቋል። እንደዚሁም በቤተክርስቲያን ሕንጻዎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በማለት ጥበቃን ማጠናከሩ ታውቋል። በአገሪቱ የሚገኙ ክርስቲያኖች ካደረባቸው ፍርሃት የተነሳ ከመኖሪያ ቤታቸው መውጣት እንደማይችሉ፣ በየቁምስናዎቻቸው የሚከናወኑ የጸሎትና የመስዋዕተ ቅዳሴ ዝግጅቶችን መካፈል አለመቻላቸውን ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ ገልጸዋል።

ጉዳዩን መንግሥት ሊያቃልለው የሚችለው ቢሆንም፣ የመብት ጥያቄን ይጨምራል፣

የፓክስታን መንግሥት ከአገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር በኋላ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚደግፍ የገለጸ ሲሆን ከዚህም ጋር የጸጥታ አስከባሪዎችን ቁጥር በማበራከት የአገሪቱን ድንበር ለማስከበር፣ የሕዝቡንም ሰላም ለማስጠበቅ መወሰኑን ብሔራዊ የጸጥታ ሃይል አስከባሪ ቃል አቃባይ ገልጸዋል።

የፓክስታን ክርስቲያን ማሕበረሰብ በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ ሆነው ለረጅም ጊዜ ያህል የአሲያ ቢቢን መፈታት በተስፋ ጠብቀው የቆዩ መሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ፣ በኢጣሊያ ውስጥ የሚገኙ የፓክስታን ክርስቲያኖች ሕብረት በጋራ ሆነው በትናንትናው ዕለት የምስጋና መስዋዕተ ቅዳሴን ማስቀደሳቸውን ተናግረዋል። መስዋዕተ ቅዳሴውን የመሩትም ካህን፣ የፓክስታን ሚኒስትር የነበሩትና፣ አሲያ ቢቢ እንድትፈታ ሲሟገቱ ቆይተው በታጣቂዎች የተገደሉ የሻባዝ ባቲ የአጎታቸው ልጅ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ በማከልም ለአሲያ ቢቢ ነጻነት ሲሟገቱ የነበሩ በታጣቂዎች የተገደሉ የእስልምና እምነት ተከታይና የፑንጃብ ከፍለ ሃገር አስተዳዳሪ የሆኑትን ሳልማን ታሲርን በጸሎታቸው ማስታወሳቸውን ገልጸዋል። ፕሮፌሰሩ በማከልም በአገሪቱ የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል እምነታቸውን በታማኝነት ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ፣ ልዩነትን ሳያደርጉ ለመላው የፓክስታን ሕዝብ የሚቆረቆሩ፣ በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የሚፈልጉ እንዳሉ አስረድተዋል።

ለፓክስታን ክርስቲያን ምሕበረሰብ አዲስ ምዕራፍ ነው፣

የአሲያ ቢቢ መፈታት ወይም ነጻ መለቀቅ ለፓክስታን የክርስቲያን ማሕበረሰብ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም ትልቅ ድል እንዳልሆነ ያስረዱት ፕሮፌሰር ሞቢን ሻዲድ፣ ነገር ግን የፓክስታን መንግሥታዊ ተቋማትን ትልቅ ዋጋ ያስከፈለ፣ ፓክስታንን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ ማሕበረ ሰብን ትኩረት የሳበ ምሳሌ ነው ብለዋል። ፕሮፌሰሩ በማከልም በፓክስታን መንግሥት የተወሰደው እርምጃ በፓክስታን ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የእምነት ተቋማት መካከል ውይይትና ጥናት እንዲደረግ መንገድን የከፈተ ተግባር ነው ብለዋል። ፕሮፌሰሩ በማከልም የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የፓክስታን መንግሥት የያዘውን አቋም በመደገፍ፣ ሰላማዊ ማሕበረሰብን ለመገንባት ማስተማር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

[ Audio Embed ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ]                

03 November 2018, 16:27