የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል   የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል  

በደቡብ ሱዳን መንግሥት እና በተቃዋሚ ቡድን መካከል ጊዜያዊ የስላም ስምምነት መፈረሙ ተነገረ።

በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አሁን ደግሞ የተቃዋሚ ቡድን መሪ የሆኑት ሪክ ማሻር፣ በሽግግር መንግሥት ውስጥ የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ ተስማምተዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ ሱዳን ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጊዜያዊ የስላም ስምምነት መፈረሙ ታውቋል።  ይሁን እንጂ አንዳንድ የጎሳ ቡድኖች ስምምነቱን አልተቀበሉትም።

በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ከስልጣን የተወገዱት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አሁን ደግሞ የተቃዋሚ ቡድን መሪ የሆኑት ሪክ ማሻር፣ በሽግግር መንግሥት ውስጥ የስልጣን ክፍፍል ለማድረግ ተስማምተዋል። በዚህም መሠረት የሽግግር መንግሥቱን በፕሬዚደንትነት የሚመሩት  ሳልቫ ኪር ሲሆኑ ሪክ ማሻር የምክትል ፕሬዚደንትነትን ስልጣን ተረክበዋል። ስምምነቱን የተፈራረሙት በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም መሆኑ ታውቋል።

ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ጋር ለሃያ ዓመታት ከዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ፣ በ2003 ዓ. ም. ነጻነቷን ማግኘቷ ይታወሳል። ለልዩነታቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ የሰሜን ሱዳን የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን የደቡቡ ክፍል የክርስትና እና የባሕላዊ እምነት ተከታይ በመሆናቸው ነው ተብሏል። በደቡብ ሱዳን 64 ብሔረስቦች እንደሚገኙ፣ ጠቅላላ የሕዝቧ ብዛትም 11 ሚሊዮን እንደሆነ ይነገራል። ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ከተቀዳጀች ማግስት ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባች ሲሆን በዚህ ምክንያት በርካት ሰዎች ለሞት፣ ለስደት፣ ለረሃብ፣ ለበሽታ እና ለድህነት መዳረጋቸው ታውቋል። ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከ2005 ዓ. ም. ወዲህ 300 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ 2 ሚሊዮን ሰዎች መሰደዳቸው ታውቋል።            ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ስልጣን ላይ የወጡት በ2003 ዓ. ም. መሆኑ ሲታወስ፣ በ2005 ዓ. ም. ከምክትል ፕሬዚደንት ከሪክ ማቻር በኩል መፈንቅለ መንግሥት ተቃጥቶባቸው መክሸፉ ይታወሳል። በዚህ ምክንያት በሁለት ጎራ የተከፈለች ደቡብ ሱዳን ልዩነታቸው ወደ ብሔር ልዩነት በመዞር፣ የሪክ ማቻር ወገን የሆኑት የኑዌር ብሔረሰብ እና የሳልቫ ኪር ወገን የሆኑት የዲንቃ ብሔረሰብ አባላት መሆናቸው ታውቋል። እነዚህን ሁለት የጎሳ አንጃዎችን በማስታጠቅ የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት እያደገ በመምጣት ባሁኑ ጊዜ በርካታ ጎሳዎችንም ማሳተፉ ታውቋል። ቀስ በቀስ የጦርነቱ ምክንያት በእነዚህ በሁለት ብሔረሰቦች መካከል በተከሰተው ግጭት ብቻ ሳይሆን፣ ሃገሪቱ በያዘችው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ክፍፍል ምክንያትም እንደሆነ ታውቋል። የሱዳን ወደ ውጭ ከምትልካቸው የሃገር ውስጥ ምርቶች መካከል 95 ከመቶ ነዳጅ እንደሆነ ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥት እና በተቃዋሚው ቡድን በካከል፣ በ2008 ዓ. ም. የተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ በዋና ከተማዋ በጁባ በተነሳው ግጭት ምክንያት ፋይዳ ሳይኖረው መቅረቱ ይታወሳል። አሁንም ቢሆን በሃገሪቱ የሚገኙትን የተለያዩ የጎሳ መሪዎችን በማሳተፍ የተደረሰ የሰላም ስምምነት ባይሆንም ዘላቂ እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። በአሶሺየትድ ፕረስ ዘገባ መሠረት፣ በሪክ ማቻር የሚመራው ተቃዋሚ ቡድን በስምምነቱ ለመጽናት አቋሙን ቢገልጽም ከሁሉ በማስቀደም ጸጥታን ለማስከበት የተወሰዱት እርምጃዎች ተግባራዊ ካልሆኑ፣ የተደረሰው ስምምነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተገልጿል።

ከዚህ በፊት ከተገቡት ውሎች ባሻገር እነዚህ ሁለቱ ጎራዎች ስምምነታቸውን በመጣሳቸው ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል። አሁን በቅርቡ በሁለቱ የደቡብ ሱዳን መሪዎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና እንደሚያደርግ ታውቋል። የጦር መሣሪያ እቀባ እንደሚጥሱ የሚነገርላቸው ሳልቫ ኪር እና ሪክ ማቻር፣ በሁለታቸው መካከል የሚደረገው የሰላም ስምምነት ውይይት በሰኔ ወር ላይ ተገናኝተው በአዲስ መልክ ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል። አሁን በሳልቫ ኪር እና በሪክ ማቻር መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መልካም ፍሬን ሊያስገኝ ይችላል በማለት የአሜሪካ መንግሥት አድናቆቱን ያሳየ ቢሆንም፣ የሰላም ሂደቱ የሲቪል ማህበረሰብን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ሴቶችን እና እስካሁን ከሰላም ውይይት ተገልለው የቆዩ የማሕበረሰብ ክፍሎችን የማያካትት ከሆነ፣ ለደቡብ ሱዳን የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንደምታቋጥ፣ የአሜሪካ መንግሥት ማስጠንቀቋ ታውቋል። በደቡብ ሱዳን ሲታተም የቆየ፣ በኋላ ላይ እንዲዘጋ የተገደደው፣ ነገር ግን ከአገር ውጭ በመታተም ላይ ያለ የአንድ ጋዜጣ አዘጋጅ የሆኑት ዎል ከርግ ኣታክ እንደገለጹት፣ በሳልቫ ኪር እና በሪክ ማቻር መካከል ያለው ግንኙነት ባሁኑ ጊዜ እጅግ የቀነሰ በመሆኑ አሁን የደረሱበትን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ በመጣል ወደ ሌላ አመጽ ሊያመራ ይችላል ብለዋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ ባለፈው ዓመት፣ ሰኔ ወር ላይ እንደገለጹት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን መገኘት ባይችሉም፣ ደቡብ ሱዳን ለሰላም በምታደርገው ጥረት ላይ ቅድስት መንበር የጸና ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸው፣ በጦርነት ምክንያት በርካታ ችግሮች የደረሰበትን የደቡብ ሱዳን ሕዝብ መርጃ እንዲሆን በማለት፣ ከቫቲካን መንግሥት ጽሕፈት ቤት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና ከዓለም አቀፉ በጎ አድራጊ ካቶሊካዊ ድርጅት የተሰበሰበ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር መርዳታቸውን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፣ ለደቡብ ሱዳን የተደረገው እርዳታ በደቡብ ሱዳን የእርዳታ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ ባሉት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ ድርጅቶች በኩል፣ በደቡብ ሱዳን የተጀመረውን የዕድገት እና የሰላም ሂደት ለማገዝ ነው ብለዋል። በደቡብ ሱዳን የቶምቡራ ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ እና የደቡብ ሱዳን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ አቡነ ኩሳላ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጻፉት መልዕክት እንደገልጹት እርዳታው በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው በመጠልያ ጣቢያ ለሚገኝ በርካታ ሕዝብ ዕለታዊ ቀለብ ለማቅረብ፣ ሰላምን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ፣ ሰባዓዊ ክብራቸውንም ለማስጠበቅ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ነው ብለዋል።     

27 July 2018, 17:36