በስሪናጋር የረመዳን ጾም የመጀመሪያ ዓርብ በስሪናጋር የረመዳን ጾም የመጀመሪያ ዓርብ  (ANSA)

ለረመዳን ጾም የተላከው የቫቲካን መልእክት የጓደኝነት ባህልን ስለማዳበር ያሳስባል

በቅድስት መንበር የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፥ የእስልምናን የተቀደሰ የረመዳን ወር እና ኢድ አል ፈጥርን በማስመልከት መልዕክቱን ያስተላለፈ ሲሆን ፥ ክርስትያኖችም ሆኑ ሙስሊሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘የጥላቻ ባህልን’ በማስወገድ በተቃራኒው ‘ሠላማዊ ፣ ተስማምቶ አብሮ የመኖር እና አስደሳች የኑሮ ባህል’ ለመገንባት እንዲተባበሩ አሳስቧል።

የዘገባው አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ፤  አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ

ቅድስት መንበር ፥ ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች አሁን ባለው ግንኙነታቸው ላይ የፍቅር እና የጓደኝነት ባህልን በጋራ በማስፋፋት አሁንም ማህበረሰቦችን የሚያናጋውን የጥላቻ ባህልን እንዲቋቋሙ ጥሪዋን አቅርባለች።በቅድስት መንበር የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በዚህ ሳምንት ተጀምሮ ከአንድ ወር በኋላ በሚያልቀው የረመዳንን የጾም ወር በማስመልከት ነው ለሙስሊም ወንድሞች እና እህቶች በላከው መልእክት ጥሪውን ያቀረበው።

የጥላቻ ባህልን መከላከል

‘ነባር ጓደኝነት ተጠናክሮ ሌሎችም ይገነባሉ ፥ ይህም ለበለጠ ሰላም፣ ስምምነት እና አስደሳች አብሮ መኖር መንገድ ይከፍታል’ ሲል ‘ክርስቲያኖች እና ሙስሊሞች፡ የፍቅርና ጓደኝነት አራማጆች’ በሚል ርዕስ ፥ የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ከሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አንጄል አዩሶ የተፈረመበት እና የተላለፈው መልእክት። ፅንፈኝነትን ፣ አክራሪነትን ፣ አለመግባባቶችን እና ሃይማኖታዊ አመፅን ፊት ለፊት ለመጋፈጥ እና የጥላቻ ባህል የሚያቀጣጥላቸውን ድርጊቶች ለመቃወም እና ለማሸነፍ በጣም ተስማሚ መንገዶችን መፈለግ አስፈላጊ መሆኑን ጽሁፉ አጉልቶ ያሳያል።

በላቲን “Nostra Aetate” ወይም “የእኛ ዘመን” የተባለው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ፥ ‘ክርስቲያን ያልሆኑ ሃይማኖቶች’ በማለት እ.አ.አ. በ1965 የወጣውን ጽሁፍ በማስታወስ ፥ ህጋዊ የሆኑ ልዩነቶች ፥ ያሉንን የጋራ የሆኑ ነገሮቻችንን ችላ እንድንል ወይም እንድንረሳ ሊያደርገን እንደማይገባ በቅድስት መንበር የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ ገልጿል።

“ሁሉም የሚጀምረው ለእያንዳንዳችን ካለን አመለካከት ነው ፥ በተለይ በመካከላችን በሃይማኖት ፣ በጎሳ ፣ በባህል ፣ በቋንቋ ወይም በፖለቲካ ልዩነት ሲፈጠር ልዩነቶቹ እንደ ስጋት ሊታዩ ይችላሉ ፥ ሆኖም እያንዳንዱ ሰው ልዩ የሆነ ማንነቱን ከተለያዩ አካላት ጋር የማግኘት መብት አለው ፥ ነገር ግን የጋራ እሴቶቻችንን ችላ ሳይለው ወይም ሳይረሳው መሆን አለበት” ይላል መልዕክቱ።

የማህበራዊ ሚዲያ ሚና

መልዕክቱ በመቀጠል "ከእኛ ለየት ያለ ሃሳብ ባላቸው ላይ የምናሳየው አሉታዊ አመለካከቶች እና ባህሪያት" ማለትም "ጥርጣሬ ፣ ፍርሃት ፣ ፉክክር ፣ አድልዎ ፣ ማግለል ፣ ስደት ፣ ጭቅጭቅ ፣ ስድብ እና ሃሜት" ዛሬ ላይ በጣም ብዙ እና በማህበራዊ ድረ-ገጾችም ጭምር እየታገዙ ይራገባሉ። "የመግባቢያ እና የወዳጅነት ዘዴ ከመሆን ይልቅ ሚናቸውን በማጣመም የጠላትነት እና የትግል መሳሪያዎች ሆነዋል ይላል ማህበራዊ ድረ ገፆችን ሲገላጽ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘ኢንሳይክሊካል ሌተር ፍራቴሊ ቱቲ’ በተባለው ደብዳቤያቸው ላይ እንደገለጹት “ጠብ ማጫር እና ጥቃትን በኮምፒዩተር እና በተንቀሳቃሽ ስልኮች በኩል ለማስፋፋት ወደር ዬለሽ ቦታ አግኝቷል” ብለው እንደነበር እናስታውሳለን።

የፍቅር እና የጓደኝነት ባህልን በትምህርት ማሳደግ

የእነዚህ አሉታዊ ባህሪያት ተቃራኒ ደግሞ መከባበር ፣ በጎነት ፣ በጎ አድራጎት ፣ ወዳጅነት ፣ መተሳሰብ ፣ ይቅርባይነት ፣ ለጋራ ጥቅም መተባበር ፣ አካባቢያችንን መንከባከብ እና እንክብካቤ ለሚፈልጉ ሁሉ መርዳት ነው ፤ እነዚህን በመፈጸም በሠላም እና በደስታ የምንኖርበትን የጋራ የሆነ መኖሪያዎቻችን አስተማማኝ የተጠበቀ እና ሠላማዊ ቦታ ማድረግ እንችላለን።  እነዚህን እሴቶች በ ‘ድምፅ ትምህርቶች’ በኩል ለአዲሱ ትውልድ ማስተማር ይገባል ፥ በዚህም ዉስጥ ቤተሰብ ፣ ትምህርት ቤቶች እና የአምልኮ ስፍራዎች ወሳኙን ሚና ይጫወታሉ ይላል የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ።

"ፍትህ ፣ ሠላም ፣ ወንድማማችነት እና ብልጽግና የነገሰበት ዓለም ፥ ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ያስደስታል ፥ ለእኛም ሠላምን ያመጣል፣ ይህ እንዲሆንም የእኛን ቅን እና የጋራ ተሳትፎ ያስፈልጋል” በማለት መልዕክቱ ያበቃል።

28 March 2023, 17:19