2022.05.13 ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሮም በሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ 2022.05.13 ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሮም በሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ 

በቅድስት መንበር እና በቻይና መካከል የተጀመረው ውይይት እንደማያቋርጥ ተስፋ ተጣለ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ሮም በሚገኝ ግሬጎሪያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ሐዋርያዊ ተግባራትን በማስመልከት ግንቦት 5/2014 ዓ. ም. በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተግኝተው፣ በሆንግ ኮንግ ብሔራዊ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ነጻ በተቀቁት በብጹዕ ካርዲናል ዜን ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት አጋርተዋል። ቀጥለውም በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነትንም በማውሳት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማውረድ ቅድስት መንበር የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች እና በጣሊያን መንግሥት በኩል የተጀመረውን የሰላም ድርድር ሂደት ቅድስት መንበር የምትደግፈው መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው በዕለቱ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሆንግ ኮንግ ጳጳስ በነበሩ ብጹዕ ካርዲ ዜን ዜ ኩን ጉዳይ፣ ከተለያዩ አገራት ለዩክሬን ስለሚደረግ የጦር መሣሪያ ድጋፍ፣ ስለ ቅድስት መንበር የሰላም ጥረት፣ ከዩክሬን ማሪዩፖል ከተማ ንጹሃን ዜጎችን ስለማስወጣት እና ከሞስኮ ፓትሪያር፣ ከብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ያለውን ግንኙነት በማስመልከት አስተያየታቸውን ከመስጠት በተጨማሪ፣ በዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፋውንዴሽን በተዘጋጀው በቀድሞ ር. ሊ. ጳ ዮሐንስ ጳውሎስ ቀዳማዊ አጭር ሐዋርያዊ ሕይወት የሚመለከት ስብሰባን ተካፍለዋል።

የካርዲናል ዜን በጸጥታ ኃይል መያዝ እና መለቀቅ

የሆንግ ኮንግ ከተማ ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ ካርዲል ዜን በጸጥታ ኃይል መያዝ ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ በጸጥታ ኃይሉ ቁጥጥር ከዋሉ ከአጭር ሰዓታት በኋላ በሰላም ነጻ መለቀቃቸውን እና ከካርዲናሉ ጋር ያላቸውን አንድነት ገልጸዋል። ክስተቱ እ. አ. አ በ2018 ዓ. ም. በሁለቱ አገራት ማለትም በቅድስት መንበር እና በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል በጳጳሳት ሹመት ላይ የተደነገገውን እና ለሁለት ዓመት የሚራዘመውን ስምምነት ሊያሰናክል እንደማይገባ ገልጸው፣ እንደነዚህ ያሉት እንቅፋቶች ቀድሞውንም ቀላል ያልነበረውን የውይይት ሂደት ሊያወሳስቡ እንደማይችሉ አስረድተዋል።

የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ጋላገር የኪዬቭ ተልዕኮ

በዩክሬን እየተካሄደ ከሚገኝ ጦርነት ጋር በተያያዘ፣ በቅርቡ ወደ ዩክሬን መዲና ኪዬቭ የተጓዙት በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ጋላገር ተልዕኮን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የሊቀ ጳጳሱ ተልዕኮ ቫቲካን ለሩሲያ እና ዩክሬን ሰላም የምታበረክታቸውን እና በማበርከት ላይ የምትገኘውን የሰላም ጥረቶች  ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ገልጸው፣ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምን ለማምጣት ከሁሉ አስቀድሞ ወደ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ መሠረታዊ መነሻ መሆኑን አስረድተዋል።

ለዩክሬን የሚሰጥ የጦር መሣሪያ ድጋፍ

ለዩክሬን የሚደረግ የጦር መሣሪያ ድጋፍ ጉዳይ አሳሳቢነት የተመለከቱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ካለፉት ወደ 80 ከሚጠጉ የጦርነት ቀናት አስቀድሞ የተገለፀው አቋም መኖሩን አስታውሰው፣ ወረራ በሚደርስበት ወቅት በጦር መሣሪያ ትጥቅ ራስን የመከላከያ መብት መኖሩን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ እንደሚናገር፣ ነገር ግን በተወሰኑ ሁኔታዎች አንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚያስቀምጥ ገልጸዋል።

በቅድሚያ መፍትሄዎችን ማግኘት

በቅርቡ የተሰሙ የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነት የሰላም ፍንጮችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ የሰላም መፍትሄን ማግኘት የማይቀር መሆኑን ገልጸው፣ ሁለቱ አገሮች በመልክዓ ምድር አቀማመጥ አኳያ አንድ ሳይሆን አብረው እንዲኖሩ የሚያስገድዳቸውን በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ በማስረዳት፣ እስካሁን የተከሰቱ የሰው ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ለመካላከል የሰላም መፍትሄዎችን አስቀድሞ ማግኘት ይቻል እንደ ነበር ገልጸው፣ ይህ እንዲሳካ ቅድስት መንበር ከመጀመሪያ አንስቶ ትመኘው እንደነበር ገልጸዋል። ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ የመንግሥታት ኅብረት እየተሸረሸረ በመምጣቱ ምክንያት ችግሮች መፍጠራቸውን ተናግረው፣ ዛሬ የሚታዩት ችግሮችም የዚህ ውጤት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከሞስኮ ፓትሪያርክ ጋር ያለው ግንኙነት

ቀደም ሲል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ኮሪዬረ ዴላ ሴራ” ከተባለ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከሞስኮ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተ የቅዱስነታቸው አቋም “ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ለጊዜው በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ላለመነጋገር ቢወስኑም፣ የምንገኝበትን አስቸጋሪ ወቅት በመገንዘብ እውቅና ልንሰጠው ይገባል” ብለዋል። አክለውም፣ ነገር ግን ይህ ማለት በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት ቅዝቅዟል ማለት እንዳልሆነ እና ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ በጎ የጋራ ውይይት መንገዶች መኖራቸውን እና ለመወያየትም ሙከራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ በቅርቡ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ነገሮች የበለጠ አስቸጋሪ መሆናቸውን አስረድተዋል።

16 May 2022, 15:10