በአፍሪካ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረግ የጤና አገልግሎት በአፍሪካ ውስጥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረግ የጤና አገልግሎት 

ለሰብዓዊ ክብር ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ተገለጸ

የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት አስፈላጊነትን በማስመልከት በቫቲካን ከጥቅምት 25-26/2014 ዓ. ም. ጉባኤ ማካሄዱ ይታወሳል። ጳጳሳዊ አካዳሚው በጉባኤው ላይ እንዳስታወቀው፣ የመከላከያ ክትባቶቹ ፍትሃዊ መንገድን ተከትለው ለሁሉም እንዲደረሱ ማድረግ በሀብታም እና በድሃ ማኅበረሰብ መካከል ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ይዳረዳል ብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በድሃው ማኅበረሰብ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ መኖሩን የገለጸው የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው፣ በአገሮች እና በትውልዶች መካከል ያለውን ልዩነትም የበለጠ እንዲጨምር ማድረጉንም ገልጿል። በቫቲካን በሚገኝ ፒዮስ 4ኛ አዳራሽ ውስጥ በበይነ መረብ አማካይነት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከተነሱት ሀሳቦች መካከል አንዱ "በወረርሽኙ መንስኤዎች ላይ በሚቀርቡ አዳዲስ አመለካከቶች፣ ድርጊቶች እና ውጤቶች ላይ የሳይንስ እና የጤና ፖሊሲዎች አንድምታ" የሚል እንደነበር ታውቋል።

ከሥነ ምግባር አኳያ የማይታለፍ ግፍ

ከሁሉም አስቀድሞ፣ የወረርሽኙን መንስኤዎች እና የሕክምና ዘዴዎችን በመረዳት ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ቀጣይነት ያለው ዝግጅት መደረግ እንደሚያስፈልግ ጉባኤው በድጋሚ ገልጿል። ከዚህም አንፃር በመከላከያ ክትባት ልማትና የሕክምና ዘርፍ አዳዲስ ሳይንሳዊ ግንዛቤዎች መታየታቸው አስደናቂ እና ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ መገኘቱ ታውቋል። ይሁን እንጂ በጤና ፖሊሲ ውስጥ የሚታዩ አዳዲስ ተሞክሮዎች እና አቀራረቦች በነፃነት ለውጥ ተደረጎባቸው፣ ክትባቱ ለሁሉም በእኩልነት መድረሱ ሊረጋገጥ እንደሚገባ፣ ይህ ካልሆነ ግን በድሃ አገሮች ውስጥ የሚታይ የመከላከያ ክትባቶች እጥረት ከሥነ ምግባር አኳያ ኢ-ፍትሃዊነትን ሊያስከትል እንደሚችል ተገልጿል። በበለጸጉ አገሮች በኩል ያለው የክትባት በእኩል እንዳይዳረስ የማድረጉ አዝማሚያ እና ወገንተኝነት ማብቃት እንደሚገባ ጉባኤው አሳስቦ፣ ወረርሽኙ እንዳይዛመት ለማድረግ የተወጠነው አስፈላጊው ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት ተጨማሪ ድጋፍ ማግኘት እንዳለበት ጉባኤው አሳስቦ፣ ዝቅተኛ የመከላከያ ክትባት ሽፋን አዳዲስ ልዩነቶችን በመፍጠር አደጋን ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

የሕዝብ ጤና ሥርዓቶች ቅድሚያ ይሰጥ

በምርመር እና ሕክምናው ዘርፍ የሚታዩ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የገለጸው ጉባኤው፣ አዳዲስ ግኝቶቹ በሕዝብ የጤና ሥርዓቶች ውስጥ ገብተው ወረርሽኞችን በመልካም መንገድ መቆጣጠር በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ እና ይህን ለማከናወን የዓለም ጤና ድርጅት ያለው ቁልፍ ሚና ተጠናክሮ መቀጠሉ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።

በሕጻናት እና ወጣቶች በሚያስከትለው ተጽእኖ ላይ ምርምር ማድረግ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የእንክብካቤ ሥርዓቶች አስፈላጊ መሆናቸን የገለጸው ጉባኤው፣ በሌሎችም እንደ ምግብ፣ ትምህርት እና የሕዝብ ጤናን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስቧል።   የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሕጻናት እና በወጣቶች መካከል መገለልን በመፍጠር፣ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ሥነ-ልቦናዊ ለውጦችም እንዳሉት ግንዛቤ የሚያሳድጉ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ምርምሮች እንዲደረጉ ያሳሰበው ጉባኤው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሊያስከት የሚችለው የረዥም ጊዜ ተፅእኖ አሳሳቢ መሆኑን አስታውቋል።

የተሳሳተ መረጃ እና የሴራ ጽንሰ-ሀሳቦችን መጋፈጥ

ከዚህ በፊት የተደረጉ ሳይንስ ምርምሮች የብዙ ሰዎች ሕይወት መታደጉን ጉባኤው ገልጾ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅትም ጥራቱን ጠብቆ በሕዝቦች መካከል የሚታየውን ጭንቀት ማስወገድ እንደሚገባ አሳስቧል። በሳይንስም ሆነ በትምህርት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሃይማኖታዊ ተቋማት ዘንድ የሚመላለሱ የተሳሳቱ መረጃዎች እና የሴራ ፅንሰ-ሀሳቦች መታረም እንዳለባቸው ያሳሰበው ጉባኤው፣ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሰው ልጅ ክብር፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮችን እና የሚወሰዱ እርምጃዎችን ለመምራት ዋና ነጥብ መሆን እንዳለበት አስታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድሞች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት መሠረት፣ ሁሉን አቀፍ የጤና ፖሊሲዎች በእውነት፣ በፍትህ፣ በአንድነት እና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረቱ መሆን እንዳለባቸው ፣ በቫቲካን የተካሄደው የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ጉባኤ አሳስቧል። 

29 November 2021, 14:30