ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ ከሶርያ ወጣቶች ጋርም ተገናኝተዋል ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ ከሶርያ ወጣቶች ጋርም ተገናኝተዋል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሶርያ ቤተክርስቲያን የ $170,000 የገንዘብ ዕርዳታ አደረጉ

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በሶርያ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማካሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በጉብኝታቸው ወቅት ከሶርያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው፣ በጦርነቱ የተጎዱትን ለመርዳት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ቃል መግባታቸውን ገልጸውላቸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ የዘጠኝ ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በጀመሩባት ደማስቆ ከተማ ከአንጾኪያ ግሪክ ካቶሊካዊ ፓትሪያርክ ከብጹዕ አቡነ ዩሱፍ አብሲ ጋር በመሆን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አሳርገዋል። ብጹዕነታቸው ቀጥለውም ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ አንድ መቶ ወጣቶች ጋርም ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአገሪቱ ውስጥ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው ጦርነት ይበልጥ የተጎዱትን ለመርዳት የተቋቋሙ የዕርዳታ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን $170,000 ለመደገፍ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ለሶርያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ ባሰሙት ንግግር፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ በሶርያ ውስጥ ለሚገኙ አሥራ ሰባት የቤተክርስቲያኒቱ ጽሕፈት ቤቶች የሚዳረስ መሆኑን ገልጸው፣ በየሀገረ ስብከቱ ብጹዓን ጳጳሳት በኩል ለተረጂዎች የሚደርስ መሆኑን አስረድተዋል።   

በመጋቢት ወር 2022 ልዩ ጉባኤ ይካሄዳል

የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ በንግግራቸው፣ በሶርያ ውስጥ ብጹዓን ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ ገዳማዊያንን እና ገዳማዊያትን፣ ምዕመናንን፣ ካቶሊካዊ የዕርዳታ ድርጅቶችን የሚያሳትፍ ልዩ ጉባኤ እ. አ. አ. በመጋቢት ወር 2020 ዓ. ም. የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ የቫቲካን ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ተወካዮች እና የምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት የእርዳታ ኤጀንሲዎችም የሚገኙበት መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ አክለውም “ጉባኤው በሶርያ ውስጥ የሚገኙትን የዕርዳታ ፕሮጄክቶችን እና ውጥኖችን በመዘርዘር፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት ‘የበጎ አድራጎት ሲኖዶሳዊነትን’ ለማሳደግ ያለመ ነው” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሶርያ ሕዝብ ጋር ያላቸው አጋርነት

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ለሶርያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ባሰሙት ንግግር፣ ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች፣ ጳጳሳት እንዲሁም የቅድስት መንበር እንደራሴ የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ ለሶርያ ሕዝብ ላደረጉት ድጋፍ እና የደረሰባቸውን ስቃይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቀው ለማድረግ ስላደረጉት ከፍተኛ ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከዚህም ጋር አያይዘው ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሶርያ ሕዝብና ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ቅርበት ገልጸው፣ በተደጋጋሚ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪያቸውን በማስታወስ፣ በጦርነት በምትሰቃይ ሶርያ የፍትህ እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቀውስን ለመቋቋም ከቅድስት መንበር በኩል የተደረገውን አስቸኳይ ዕርዳታ አስታውሰዋል። በማከልም ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ. ሚያዝያ 12 ቀን 2020 ዓ. ም. ያስተላለፉትን የብርሃነ ትንሳኤ መልእክት እና በተመሳሳይ ዓመት መስከረም 25 ቀን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያስተላለፉትን የቪዲዮ መልዕክት አስታውሰዋል።

ሲኖዶሳዊ ሂደት በሶርያ

ሌላው የሶርያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ልዩ ትኩረት፣ የአገሩ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማካሄድ ላይ የምትገኘው ሲኖዶሳዊ ሂደት እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን በበላይነት የሚከታተሉት የሶርያ የፖለቲካ ሁኔታ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ፣ በር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የታሰበው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስተዳድሩት ሲኖዶሳዊ መዋቅሮችንም የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

 

 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “መላዋ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የማስተዋል፣ ራስን የማንጻት እና የመታደስ ጎዳናን እንድትጓዝ” መፈለጋቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ፣ በአገሪቱ የሚገኙ የላቲንም ሆነ ምሥራቃዊ የአምልኮ ሥርዓት የሚከተሉ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ምዕመናኖቻቸውን በቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ ላይ በማሳተፍ እ. አ. አ በ2023 ዓ. ም. በሮም ለሚካሄድ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ  መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

 

ካቶሊካዊ ወጣቶች "የፍቅር አብዮት" እንዲመሩ

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ከሶርያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ካካሄዱት ጉባኤ ቀጥለው፣ በደማስቆ ከአንጾኪያ ግሪክ ካቶሊካዊ ፓትሪያርክ ከብጹዕ አቡነ ዩሱፍ አብሲ ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን አሳርገዋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ቀጥለውም ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ አንድ መቶ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወጣቶች ጋር ተገናኝተዋል። በዚህ ወቅት ወጣቶቹ የደረሰባቸውን ስቃይ፣ በሶርያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና በሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ያላቸውን ስጋት ለብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ አካፍለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሳንድሪ በበኩላቸው ለወጣቶቹ ባሰሙት የማበረታቻ መልዕክት፣ በቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ሂደት በብቃት በመሳተፍ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል መሠረት በማድረግ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮ “በተለይም ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመታገዝ "ለሰብዓዊ ክብር የፍቅር አብዮት" እንዲመሩ አሳስበዋል።

 

በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ የዘጠኝ ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ዕሮብ ጥቅምት 24/2014 ዓ. ም. ወደ ሮም ከመመለሳቸው አስቀድመው በሶርያ ውስጥ ታርቱስ፣ ሆምስ፣ አሌፖ፣ ያብሮድ እና ማሎኡላ የተባሉ አካባቢዎችን እንደሚጎበኟቸው ታውቋል። 

28 October 2021, 17:01