የቤሰብን ውበት ለመግለጽ የታሰበ የአንድ ቀን ጥናታዊ የአስተንትኖ ቀን የቤሰብን ውበት ለመግለጽ የታሰበ የአንድ ቀን ጥናታዊ የአስተንትኖ ቀን  

የቤተሰብን የፍቅር ውበት እና ደስታን ለሌሎች መመስከር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

የቤሰብን ውበት ለመግለጽ የታሰበ የአንድ ቀን ጥናታዊ እና የአስተንትኖ ቀን ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ “ሳንታ ክሮቼ” በተባለ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። አርብ ጥቅምት 19/2014 ዓ. ም. የሚካሄደውን የአስተንትኖ ዝግጅት የሚያስጀምሩት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ በመከበር ላይ በሚገኝ የቤተሰብ ዓመት ውስጥ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ጥናታዊ የአስተንትኖ ዕለት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተመኙት እ. አ. አ በ2022 ዓ. ም. በሮም ለሚከበር ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ዝግጅት  መሆኑ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የአንድ ቀን ጥናታዊ የአስተንትኖ ቀኑ በ“ሳንታ ክሮቼ” ጳጳስዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማኅበራዊ መገናኛ ፋካልቲ የተመሰረተበት 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ጋር የተያያዘ መሆኑ ታውቋል።

ማኅበራዊ ሕይወትን ያጋጠሙት ቀውሶች እና ችግሮች በርካቶች ቢሆኑም ከሁሉም በላይ ዋና ግቡ የቤተሰብን ውበት ለሌሎች መመስከር እንደሆነ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ማሳሰቡ ይታወቃል። በሮም ከተማ በሚገኝ “ሳንታ ክሮቼ” ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ጥቅምት 19/2014 ዓ. ም. የሚካሄደውን ጥናታዊ የአስተንትኖ ዝግጅትን የሚያስጀምሩት፣ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የፔሩጃ-ፒዬቬ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ መሆናቸው ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ በስብሰባው መክፈቻ ዕለት “ቤተክርስቲያን እና የቤተሰብ ዕድገት” በሚል ርዕሥ ያዘጋጁትን ጥናታዊ ጽሑፍ የሚያቀርብ መሆኑ ታውቋል። ቀጥሎም እ. አ. አ በ2023 ለሚካሄደው ብጹዓን የጳጳሳት ሲኖዶስ ዝግጅት የሚረዳ የውይይት እና የመደማመጥ ጊዜ የተመደበ መሆኑ ታውቋል።    

ትስስርን የሚያሳድግ ፍቅርን መመስከር

የቤተሰብ ዓመት እየተከበረ ባለበት በዚህ ዓመት፣ ሮም ከተማ በሚገኝ “ሳንታ ክሮቼ” ጳጳስዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የማኅበራዊ መገናኛ ፋካልቲ የተመሰረተበት 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን እንደሚያከብሩ የገለጹት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠሪው ክቡር አቶ ዳንኤል አራሳ፣ በቤተሰብ የፍቅር ውበት እና ደስታ ላይ በማሰላሰል ለሌሎች ግንዛቤን ማስያዝ ተገቢ ነው ብለዋል። የፋካልቲው ተጠሪ አክለውም  “ቤተሰብ የኅብረተሰቡ ዋና የማዕዘን ድንጋይ ነው” ብለን እናምናለን ብለው፣ በዚህም መሠረት ብዙውን ጊዜ ተስፋ በሌለበት ዓለም ውስጥ መልስ መስጠት እንዲችል ቤተሰብን መደገፍ እና ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል። “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የፍቅር ሐሴት” ባሉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እንዳስታውሱን፣ ፍቅር በቤተሰብ መካከል ትስስርን በማዳበር፣ የመገናኛ መረቦችን በመፍጠር እና ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነትን በመገንባት ሥራ ውስጥ ማዕከላዊ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።

በስብሰባው ላይ ንግግር የሚያደርጉ እንግዶች

አርብ ጥቅምት 19/2014 ዓ. ም. በሚካሄደው ጥናታዊ የአስተንትኖ ዝግጅት ላይ በሁሉም የጣሊያን ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ የሚገኙ የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል። በተጨማሪም በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤቶች ዳይሬክተር ክቡር አቶ ቪቼንሶ ኮራዶ ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል። የሮም ሀገረ ስብከትን በመወከል ክቡር አባ ዎልተር ኢንሴሮ፣ ከኖላ ሀገረ ስብከት ማርያአንጄላ ፓሪሲ እና ከሚላን ሀገረ ስብከት ክቡር አቶ ስቴፋኖ ፌሚኒሲ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ስብሰባውን የሚመሩት በ“ሳንታ ክሮቼ” ወይም በቅዱስ መስቀል ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ክቡር አቶ ጆቫኒ ትሪደንቴ መሆናቸው ታውቋል።  

21 October 2021, 17:15