የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ 

ቫቲካን፣ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት መመሪያን ይፋ አደረገ

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሂደት ለመከታተል የሚያግዝ መመሪያን አዘጋጅቶ ይፋ አድርጓል። መመሪያው ሌሎችን በንጹሕ ልብ ቀርቦ ማዳመጥ፣ ፍርሃትን አስወግዶ መናገር፣ ከቤተክርስቲያን፣ ከማኅበረሰብ እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር መወያየት የሚሉ ርዕሠ ጉዳዮችን የያዘ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ያሳተመው መመሪያ፣ ሲኖዶሱ የሚመራበትን የቤተክርስቲያን አንድነት መመሪያ መርሆዎችን የሚያመለክት ነው ተብሏል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች እና ቁምስናዎች የሚከበረው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በሮም መስከረም 29/30 2014 ዓ. ም የሚካሄድ ሲሆን፣ በተለይም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድም ጥቅምት 7/2014 ዓ. ም የሚከበር መሆኑ ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ያሳተመው መመሪያው፣ በ2015 ዓ. ም በቫቲካን ውስጥ ለሚገባደደው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ቅድመ ዝግጅት እንዲሆን የታሰበ መሆኑ ታውቋል። ማክሰኞ ጳጉሜ 2/2013 ዓ. ም. ይፋ የሆነው የቅድመ ዝግጅቱ ሰነድ፣ ከጥቅምት 2014 እስከ ሚያዝያ 2014 ዓ. ም ድረስ የሚካሄደውን “የእግዚአብሔርን ሕዝቦች የማዳመጥ እና የምክክር ምዕራፍ” የሚለውን የመጀመሪያ ደረጃ ሂደት የሚያመቻች ነው ተብሏል።

በኅብረት መጓዝ

በኅብረት መጓዝ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስበው የዝግጅት መመሪያው፣ ፈጣን ውጤቶን ለማምጣት የሚረዱ ገንቢ ተሞክሮችን ወይም መድረኮችን አዘጋጅቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገቶች የሚታዩበት ሲኖዶሳዊ ተሐድሶን በክርስቲያን ማህበረሰብ መካከል ለማስተዋውቅ መሆኑን መመሪያው ያብራራል።

የመመሪያው መሠረታዊ ጥያቄዎች

የተለያዩ ደረጃዎች ባሉት የክርስቲያን ማኅበረሰብ ዘንድ የጋራ ጉዞን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል? ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር በተሰጣት ተልዕኮ መሠረት ወንጌልን መመስከር የምትችልበትን መንገድ እንዴት ማዘጋጀት ይቻላል? ቤተክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ እንድታድግ መንፈስ ቅዱስ የሚጋብዘን ደረጃዎች የትኞቹ ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች መመሪያው ከያዛቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸው ተመልክቷል።

ወደ አንድነት የሚመሩ ደረጃዎች

ወደ አንድነት የሚመሩ መንገዶችን አስመልክቶ የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አንዳንድ ተጨባጭ እርምጃዎችን ጠቁሟል። ከእርምጃዎች መካከል በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች እራሳቸውን ከቤተክርስቲያን ያራቁትን ወደ ቤተክርስቲያን በመጥራት፣ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ እና ተደማጭነት እንዲያገኙ ዕድል መስጠት፣ ለቤተሰባዊ ለሰው ልጅ ጥቅም እንዲሆን ከመንፈስ ቅዱስ በነጻ ላገኙት ችሎታ እና በረከት እውቅናን እና አድናቆት መስጠት የሚሉት ተጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪም የቤተክርስቲያ ሃላፊነት፣ ሥልጣን እና በዚህ ሃላፊነት ሥር የሚገኙ የተለያዩ መንፈሳዊ ተቋማት እንዴት በመተዳደር ላይ እንዳሉ፣ ከቅዱስ ወንጌል ትምህርት ውጭ የሚካሄዱ አንዳንድ ተግባራትን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መመሪያው ያሳስባል። መመሪያው በማከልም፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ በማህበራዊ ውይይቶች መካከል ፈውስን፣ እርቅን፣ መካተትን፣ ንቁ ተሳትፎን፣ በዴሞክራሲ መልሶ ግንባታ ፣ በወንድማማችነት እና ማህበራዊ ወዳጅነት ጎዳናዎች ውስጥ ተዓማኒነትን እና አስተማማኝ አጋርነትን በመግለጽ እንዴት ዕውቅናን ማግኘት እንደሚችል መመልከት እንደሚያስፈልግ ያሳስባል።    

ተጨባጭ እርምጃዎቹ የሚከናወኑት፣ ዘመኑ ባመጣቸው አንዳንድ ለውጦች ምክንያት በኅብረተሰቡ ውስጥ በተከሰቱ ታሪካዊ አውዶች፣ ከእነዚህም መካከል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ዓለም አቀፍ ቀውስ፣ የኑሮ አለመመጣጠን እና ኢፍትሃዊነት መሆናቸውን አስታውቋል። የቅድመ ዝግጅቱ መመሪያ እንደዚሁም ቤተክርስቲያን ራሷ ምዕመናን እምነቱን እንዲያጣ የሚያደርግ ምግባረ ብልሹነት በውስጧ እንዳለ ተገንዝባ መጋፈጥ እንዳለባት ያሳስባል። በቤተክርስቲያን ውስጥ ከታዩ ምግባረ ብልሹ ተግባራት መካከል በቤተክህነቱ በኩል በሕጻናት እና ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የቤተክርስቲያን ሥልጣንን እና ሕሊናን አግባብ ባልሆነ መንገድ መጠቀም የሚሉ ተጠቅሰዋል። ሌሎች በርካታ የተሳሳቱ አካሄዶች እንዳሉ የገለጸው መመሪያው፣ “አዲስ የክርስቲያን እና የቤተክርስቲያን ሕይወት ጎዳናን” ለመጀመር የሚያግዙ “አዲስ የእምነት ቋንቋዎች” እና “አዲስ መንገዶች” የሚያስፈልጉ መሆኑን አብራርቷል። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት እና ሌሎች ጉዳዮች፣ ሲኖዶሶ በጠየቀው መሠረት ለምዕመናን በተለይም ለሴቶች እና ለወጣቶች አዲስ ተሳትፎ እና አድናቆት ሰፊ ቦታ የሚሰጥባቸው አጋጣሚዎች መሆናቸውን መመሪያው ጨምሮ አስታውቋል።

ንቁ የወንጌል አገልጋዮች

መመሪያው ምዕመናንን አስመልክቶ ባሰፈረው ሃሳቡ፣ የጥምቀት ምስጢርን የተቀበሉት በሙሉ በወንጌል አገልግሎት በንቃ መሳተፍ እንደሚችሉ ገልጾ፣ በቤተክርስቲያን አንድነት የቤተክርስቲያን አባቶች በአደራ የተቀበሉትን የእግዚአብሔር ሕዝብ ለማዳመጥ ፍርሃት እንዳይዛቸው አሳስቧል። የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን አስተምህሮ የጠቀሰው መመሪያው፣ በሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናንን ጨምሮ ብጹዓን ጳጳሳት እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ጭምር አንዱ ከሌላው መማር የሚችልባቸው ዕድሎች መኖራቸውን ገልጿል። በእውነተኛ መንፈስ አንዱ ሌላውን ማዳመጥ እንደሚገባ፣ ይህም ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ሊኖር የሚገባውን የጠበቀ ግንኙነት የሚያካትት መሆኑን መመሪያው አስረድቷል። የቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ወይም አንድነት ትንቢታዊ ምልክቶች እንዳሉት፣ ከሁሉም በላይ የለጋራ ጥቅም የሚሆኑ መልካም ሃሳቦችን ማቅረብ የማይችሉትንም የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድቷል። በተጨባጭ መልኩ የቅድመ ዝግጅት መመሪያው፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ተወያይቶ መሠረታዊ የሆኑ የመመሪያ ጥያቄዎችን አቅርቧል። “በሀገረ ስብከት ውስጥ ‘የጋራ ጉዞ’ እንዴት ይከናወናል? ፣ ምን ዓይነት ደስታን ያጎናጽፋል? የጋራ ጉዞን የሚያደናቅፉ እንቅፋቶች የትኞቹ ናቸው? ምን ዓይነት ቁስል ይፋ እንዲሆን መንገድ ፈጥሯል? ለውጥን ለማሳየት የሚረዱ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው” የሚሉ ይገኝባቸዋል።

የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ደረጃዎች

የቅድመ ዝግጅቱ መመሪያ የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት የሚገልጹ ሦስት ደረጃዎች ያስቀመጠ ሲሆን የመጀመሪያው ቤተክርስቲያን የምትከተላቸውን የሕይወት መንገዶችች እና አገልግሎቷን የምታቀርብባቸው ስልቶች፣ የቤተክርስቲያን መዋቅሮች እና የሥራ ሂደቶች እናቤተክርስቲያን የተጠየቀችውን የሲኖዶስ ሂደቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የምትገኝበት ደረጃ እና የሃላፊዎቿ ብቃት የሚሉ መሆናቸው ታውቋል።

የበተግባር የሚታዩ የሲኖዶሳዊነት ገጽታዎች

በመጨረሻም የዝግጅት መመሪያው የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት የሚገልጹ 10 ጭብጦችን አስቀምጧል።

1ኛ. “ቤተክርስቲያናችን” ለማለት እንድንችል ከቤተክርስቲያን ወደ ኋላ የቀሩትን እና የተዘነጉ የጉዞ አጋሮች

2ኛ. ወጣቶችን ፣ እናቶችን ፣ ገዳማዊያን እና ገዳማዊያትን ፣ ከቤተክርስቲያን የተገለሉትን ማዳመጥ መቻል፣

3ኛ. ነጻ እና እውነተኛነቱ በሆነ መንገድ በይፋ የመናገር ዕድልን በቤተክርስቲያን እና ተቋሞቿ ውስጥ መመቻቸት፣

4ኛ. የአምልኮ ስርዓቶች እና የጸሎት ዝግጅቶች ውጤታማ በሆነ መንገድ ምዕመናንን በንቃት በማሳተፍ “መንፈሳዊ የጋራ ጉዞን” ማሳደግ እንደሚችሉ ማሰብ፣

5ኛ. የወንጌል ተልዕኮ ሃላፊነትን በጋራ መሸከም፣ ማህበራዊ ፍትህን ፣ ሰብአዊ መብቶችን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ደህንነት ለመጠበቅ በአገልግሎት ላይ የተሰማሩ አባላትን ምዕመናን እንዴት መደገፍ          እንዳለባቸው በማሰብ፣

6ኛ. ከክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ ከሀገረ ስብከቶች፣ ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ማኅበራት፣ ከማያምኑት ሰዎች፣ ከድሆች እና ከመላው ማህበረሰብ ጋር ውይይቶችን ማካሄድ፣

7ኛ. ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞች እና እህቶች ጋር ስላለው ግንኙነት፣ በጋራ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ፣ በተገኙ መልካም ፍሬዎች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በጋራ መመልከት፣

8ኛ. የቤተክርስቲያን መሪዎች ሃላፊነታቸውን እንዴት እየተወጡ እንደሚገኙ፣ የሐዋርያዊ አገልግሎት እውቀት፣ ልምድ አብሮ የመሥራት ባሕል፣ እና የአገልግሎቶ ዓይነቶችንም ማጤን እና መመልከት፣

9ኛ. ውሳኔን ለመውሰድ የሄዱባቸው መንገዶች እና ዘዴዎች የትኞቹ እንደሆኑ፣ ግልጽነትን እና ታማኝነትን ለማሳደግ የተጠቀሙባቸውን መንገዶች የትኞቹ እንደሆኑ ራስን መጠየቅ እና በጥልቅ ማሰላሰል፣

10ኛ. በክርስቲያን ማኅበረሰብ መካከል ሃላፊነት የተጣለባቸው ምዕመናን በትምህርት እና በስልጠና ያገኙትን ዝግጅት እና ብቃት በመመልከት ራስን ለቤተክርስቲያን አንድነት ማዘጋጀት የሚሉት ሃሳቦች              በመመሪያው ሰፍረዋል። ወደ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ድረ-ገጽ በመሄድ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል መመሪያው ያስገነዝባል።   

09 September 2021, 17:55