በቅድስት መንበር፣ ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አባላት ስብሰባ በቅድስት መንበር፣ ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አባላት ስብሰባ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በቫቲካን ለጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አዲስ አባል መረጡ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጀርመን-ቤርሊን ከተማ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር እና የበሽታ አምጪ ተህዋስያን ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ፕሮፌሰር ኤማኑኤል ማሪ ቻርፔንቲየርን በጳጳሳዊ አካዳሚ ውስጥ አባል አድርገው መርጠዋቸዋል። ፕሮፌሰር ኤማኑኤል ማሪ እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም በኬሚስትሪ ሳይንስ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አዲስ አባል ሆነው የተመረጡት ፕሮፌሰር ኤማኑኤል ማሪ በፈረንሳይ “ጁቪሲ-ሱር-ኦርዥ” ከተማ ተወልደው ትምህርታቸውን ፓሪስ በሚገኝ ፔር ኤ ማሪ ኪዩሪ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው የባዮሎጂ፣ የማይክሮ-ባዮሎጂ፣ የባዮ-ኬሚስትሪ እና የጄነቲክ ሳይንስ ባለ ሙያ ሆነው ተመርቀዋል። ቀጥለውም በጀርመን-ቤርሊን ከተማ በሚገኝ ሁምቦልት ዩኒቨርሲቲ፣ በባዮሎጂ ምርምር ተቋም ውስጥ በመምህርነት የሚያገለግሉ ሲሆን ቀደም ሲል በስዊድን ኡመ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም አስተምረዋል።

ፕሮፌሰር ኤማኑኤል ማሪ በፈረንሳይ በሚገኙ የቴክኖሎጂ እና የሳይንስ አካዳሚ ውስጥ አባል መሆናቸው ሲታወቅ ባለፈው ዓመት ከፕሮፌሰር ጄኒፈር አን ዱድና ጋር ለ “CRISPR-Cas9” የጄኔቲክ ሕዋስ መለያ ዘዴን በማጎልበት በኬሚስትሪ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ይህ ዘዴ በስቶክሆልም በሚገኝ የሳይንስ ምርምር ማዕከል እንደ ከፍተኛ የግኝት ውጤት በመሆን የተመዘገበ ሲሆን፣ ምክንያቱም የእፅዋትን ፣ የእንስሳትን እና የረቂቅ ተሕዋስያን “ዲ ኤን ኤ” ን በማሻሻል ፣ በሕይወት ሳይንስ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረ፣ ለአዳዲስ የካንሰር ሕክምናዎች አስተዋፅኦን በማበርከት ህልሞችን እውን ያደረገ እና በዘር የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመፈወስ የሚያስችል መድኃኒት ማግኘት በማስቻሉ ነው ተብሏል።

ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አወቃቀር

ፕሮፌሰር ኤማኑኤል ማሪ አባል የሆኑበት ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ በሮም ከተማ እ. አ. አ በነሐሴ 17/1603 ዓ. ም. የተቋቋመ ሲሆን መስራቾቹም ፌዴሪኮ ቼሲ፣ ጆቫኒ ሄክ፣ ፍራንችስኮስ ስቴሉቲ እና አናስታሲዮ ዴ ፊሊስ መሆናቸው ታውቋል። አካዳሚው እ. አ. አ ነሐሴ 17/2010 ዓ. ም ጣሊያናዊው ተመራማሪ ጋሊሌዎ ጋሊሌይ አባል የሆነበት እና በኋላም የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 9ኛ እ. አ. አ በ1847 ዓ. ም “በጳጳሳዊ አካዳሚ የአዳዲስ ምርምሮች ማዕከል” የሚል ስም በመስጠት እንደገና የመሠረቱት ተቋም ነው። እ. አ. አ በ1922 ዓ. ም ወደ ቫቲካን ግቢ ተዛውሮ አሁን በሚገኝበት በፒዮስ 4ኛ ሕንጻ ውስጥ እንዲሆን ተደርጓል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 11ኛ እ. አ. አ 1936 ዓ. ም አካዳሚው የሚመራበትን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ ማጽደቃቸው ይታወሳል። የጳጳሳዊ አካዳሚው ተልዕኮ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ትክክለኛ የሳይንስ ምርምሮችን ማክበር ፣ ነፃነቱን ማረጋገጥ እና የምርምር ዕድገቱን ማበረታታት መሆኑ ታውቋል። አካዳሚው በምክር ቤት የሚታገዝ እና በፕሬዚዳንት የሚመራ ሲሆን ተመራማሪዎቹ የዘር እና የሐይማኖት ልዩነት ሳይደረግባቸው በር. ሊ. ጳ የተመረጡ 80 ከፍተኛ የጳጳሳዊ አካዳሚው ተመራማሪዎች ከመላው ዓለም ተሰባስበው በሒሳብ ሳይንስ ዘርፍ ሙከራዎችን የሚያካሂዱበት ከፍተኛ የምርምር ተቋም መሆኑ ታውቋል።    

11 August 2021, 17:23