የአንድ ሕጻን ሕይወት ከሞት አደጋ ሲተርፍ የአንድ ሕጻን ሕይወት ከሞት አደጋ ሲተርፍ 

ካርዲናል ፓሮሊን፣ ስደተኞችን በፖለቲካ እይታ ሳይሆን በወንጌል ዓይን መመልከት ያስፈልጋል አሉ

በሮም ከተማ ትራስቴቨረ በተባለ አካባቢ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ ስደተኞች የታሰቡበት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል። የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ሲጓዙ በሚያጋጥማቸው የጉዞ ወቅት አደጋ የሞቱትን ስደተኞች ለማስታወስ የቀረበ መሆኑ ታውቋል። በዚህ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የተገኙ ሲሆን፣ የስደተኞችን ጉዳይ በፖለቲካዊ አስተያየት ከመመልከት ይልቅ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ በሚለው ወንጌላዊ ዓይን መመልከት ያስፈልጋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ ከ1990 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ አውሮፓ ለመድረስ በጉዞ ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡ ስደተኞች ቁጥር 43,390 መሆናቸው ታውቋል። ይህ አሃዝ ሌሎች የደረሱበት የማይታወቅ በርካታ ስደተኞችን የማያካትት ነው ተብሏል። በሮም ከተማ የሚገኝ የቅ. ኤጂዲዮ ማኅበር ከሌሎች በጎ አድራጊ ማኅበራት ጋር በመተባበር ለስደተኞች የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወቃል። በሮም ከተማ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ የተካሄደውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ያዘጋጀው የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ሲሆን፣ ማኅበሩ ከዚህ ባሻገር መጭው እሑድ ሰኔ 13/2013 ዓ. ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ለማክበር ዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ውስጥ በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ ወደ አውሮፓ ለመድረስ በሚደረግ የባሕር ጉዞ ሕይወታቸውን ያጡ ስዎች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መገኘታቸው ታውቋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፣ ወደ አውሮፓ ለመድረስ ተስፋን አድርገው በባሕርም ሆነ በየብስ ሲጓዙ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ነፍሳትን አስታውሰዋል። እ. አ. አ ከሰኔ ወር 2020 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቢያንስ የ4071 ሰዎች ሕይወት በአደጋው ምክንያት የጠፋ መሆኑን አስታውሰዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም፣ ስደተኞች ዕርዳታን ለማግኘት ከበርካታ ዓመታት ወዲህ የአውሮፓን በር ሲያንኳኩ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ መልስ ሳያገኝ ሲቀር ለሞት መዳረጋቸው በአውሮፓ የሂሊና ጸጸት ማስከተሉን ገልጸዋል።

የሜዲቴራኒያን ባሕር ለረጂም ዓመታት የሰዎች መገናኛ ማዕከል ሆኖ መቆየቱን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተው፣ ይህ ቦታ የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት፣ ቁጣ እና መከራ የታየበት፣ መቋጫ የሌለው ውይይት የተካሄደበት እና በሰዎች መካከል ልዩነት የታየበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።

በፖለቲካ አካሄድ ሳይሆን በወንጌል እውነት መመራት

የስደተኞችን ጉዳይ በማስመልከት የተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች የሚሰጡት መረጃ ድንጋጤን የሚያስከትል መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸው፣ በተለይም በቅርቡ በሊቢያ የባሕር ወደብ ላይ የተገኘው የሕጻናት አስክሬን መላውን ዓለም ማስደነገጡን ገልጸዋል። ይህ መሆኑ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚፈጥረውን ሐዘን እና ቅረታን በመገንዘብ አገሮች ድንበሮቻቸውን ከመዝጋት ይልቅ ስደተኞችን ተቀብለው የሚያስተናግዱበትን፣ ከድንበር የጸጥታ ጥበቃ ይልቅ አንድነትን፣ ከብሔርተኝነት ይልቅ ዓለም አቀፋዊነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ የሚያስታውስ መሆኑን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን አስረድተዋል።

16 June 2021, 14:31