አውዳሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክምችት አውዳሚ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ክምችት 

ቅድስት መንበር የጦር መሣሪያ ምርት እንዲቆም የሚያበረታታ ስብሰባ አዘጋጀች

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቲኒዮ ጉቴረዝ በመላው ዓለም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ካሳሰቡ ከአንድ ዓመት በኋላ ነገ ማክሰኞ መጋቢት 14/2013 ዓ. ም. ቅድስት መንበር በአውታረ መረብ አማካይነት ያዘጋጀችውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ስብሰባን የልዩ ልዩ ሐይማኖት መሪዎች የሚካፈሉት መሆኑ ታውቋል። በስብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግር የሚያደርጉት ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፣ ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኣዩሶ እና ብጹዕ ካርዲናል ቶማሲ መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ነገ ማክሰኞ መጋቢት 14/2013 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በጣሊያን አቆጣጠር ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአውታረ መረብ አማካይነት የሚጀምረው ስብሰባ ዋና ርዕሥ፣ “በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የጦር መሣሪያ ትጥቅን የማስፈታት ተግባር ማራመድ” የሚል መሆኑ ታውቋል። የአውታረ መረብ ላይ ስብሰባን በጋራ ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ምክር ቤት ለንደን ከሚገኝ የጦር መሣሪያ ምርትን እና ዕድገትን የሚያስወግድ ስልታዊ ፅንሰ-ሀሳብ ማስፋፊያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው።

ሦስት ክፍለ ያለው ውይይት

በእንግሊዝኛ ቋንቋ በአውታረ መረብ አማካይነት የሚካሄደውን ስብሰባ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት “ዩ ቲዩብ” ማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በቀጥታ መከታተል የሚችል መሆኑ ታውቋል። በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል በቀጥታ በሚተላለፈው ስብሰባ ላይ የሚካፈሉት የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ሳይንሳዊ ተመራማሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና የሐይማኖት መሪዎች መሆናቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ በማከልም ስብሰባው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመታገዝ የጦር መሣሪያ ምርትን ለማስቆም የሚያግዙ ተጨባጭ የሆኑ አማራጭ መልሶችን ለማግኘት የሚያግዝ መሆኑን አስታውቋል። ውይይቱ ሶስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሐላፊ በሆኑት በብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን የሚቀርብ የተለያዩ ተቋማት ማስተዋወቅ መርሃ ግብር ሲሆን በዚህ ክፍል የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን የቪዲዮ መልዕክት እና ለንደን በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናትና ዲፕሎማሲ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ዳን ፓሌሽ የሚያደርጉት ንግግር በቅደም ተከተል የሚቀርብ መሆኑ ታውቋል።

ዓለም አቀፍ ሕግ እና በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት

ሁለተኛው ክፍል ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተከትሎ የጦር መሣሪያ ትጥቅን ለማስፈታት የሚያስችሉ ተጨባጭ ዘዴዎች ላይ ውይይቶች የሚደረግበት መሆኑ ታውቋል። በዚህ ውይይት ላይ ሃሳባቸውን እና ልምዳቸውን የሚያካፍሉት የጦር መሣሪያ ምርት እንዲቆም ጥረት የሚያደርጉ ምሁራን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ማኅበረሰብ ሲሆኑ ማጠቃለያውም ጄኔቫ በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢቫን ጀርኮቪች በሚያቀርቡት ንግግር ይሆናል። ሦስተኛው ክፍል የሚያተኩረው በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት የጦር መሣሪያ ምርት እና ትጥቅ ተወግዶ ሰላም እንዲመጣ በሚያደርገው ከፍተኛ ሚና ላይ የሚወያይ መሆኑ ታውቋል። በሦስተኛው የስብሰባ ክፍል ላይ የሚሳተፉት፣ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ሲልቫኖ ማርያ ቶማሲ፣ የማልታ ሉዓላዊ ደንብ ልዩ ተወካይ እና ልዩ ልዩ የክርስቲያን ተቋማት እና እምነቶች ተወካዮች መሆናቸው ታውቋል። የእነዚህ ሦስት ክፍሎች ማጠቃለያን ንግግር የሚያደረጉት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ማሪ ዱፌ መሆናቸው ታውቋል። በአውታረ መረብ የሚካሄደውን ውይይት በበላይነት የሚመሩት በቅድስት መንበር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ምክር ቤት አስተባባሪ ዶ/ር አሌሲዮ ፔኮራሪዮ መሆናቸው ታውቋል።

የቅድስት መንበር አስተዳርራዊ ክፍሎች ድጋፍ

ጠቅላላ የአውታረ መረብ ስብሰባ እንዲካሄድ ድጋፍ ያደረጉት በቅድስት መንበር ሥር የሚገኙ ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ የአስተዳደ ክፍሎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል በጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ የሐይማኖት ተቋማት አንድነት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽ/ቤት እና የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲምፖዚየም ሲሆኑ፣ ተጨማሪ ድጋፍ ያደረጉት ዓለም አቀፍ የኢየሱስ ሰላም ማኅበር፣ ካቶሊካዊ የሰላም ግንባታ ኅብረት ፣ በአሜሪካ የሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲ ምርምር ተቋም እና በርክሌይ የሃይማኖት ማዕከል ፣ በጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የዓለም ጉዳዮች ምርምር ማዕከል መሆናቸው ታውቋል።

22 March 2021, 09:30