እውቁ የዜማ ደራሲ፣ ኤንዮ ሞሪኮኔ ማረፉ ተነገረ።
ጣሊያናዊው የዜማ ደራሲ አቶ ኤንዮ ሞሪኮኔ በ91 ዕድሜው ሮም ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ማረፉ ታውቋል። በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፣ አርቲስቱን በማስታወስ ከቫቲካን ኒውስ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
የቫቲካን ዜና፤
ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ በቃለ ምልልሳቸው የዜማ ደራሲ ኤኒዮ ሞሪኮኔ የእምነት ሰው ነበር በማለት ገልጸውታል። በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ በማከልም ለሲኒማ ጥበብ የሚሆን ዜማን በመድረስ የሚታወቀው አርቲስት ኤንዮ ሞሪኮኔ፣ ሁለት ታላላቅ መንፈሳዊ ሥራዎችን አዘጋጅቶ ማቅረቡን አስታውሰው፣ ከእነዚህም መካከል የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን የሚያስታውስ ዝግጅት በፖላንድ ማቅረቡን አስታውሰዋል። ሁለተኛው ከዚህ በፊት ለሠራቸው ተወዳጅ የዜማ ሥራዎች በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም የተዘጋጀለትን የሜዳሊያ ሽልማት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሚያዚያ 15/2019 ዓ. ም. ባበረከቱለት ጊዜ መገናኘታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ አስታውሰው፣ እነዚህ ሁለቱ ሥራዎቹ መንፈሳዊ ሕይወቱን ያስመሰከረባቸው እና ዘወትር የሚታወስባቸው ሥራዎች መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የማሪኮኔ ሥራዎች መንፈስዊነት፣
በዕውቁ አርቲስት ኤንዮ ሞሪኮኔ የዜማ ሥራዎች ውስጥ ሐይማኖታዊ እና መንፈሳዊ ዕሴቶች የታከሉባቸው መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፣ ለፊልም ሥራዎች፣ “The Mission” እና “ዌስተርን” የፊልም ሥራዎች ያቀረባቸው የዜማ ድርሰቶች መንፈሳዊነት እና ሐይማኖታዊ ገላጭነት ያላቸው መሆኑን አስታውሰዋል። በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ራቫዚ በማከልም የዕውቁ አርቲስት ኤንዮ ሞሪኮኔ የዜማ ድርሰቶች ለፊልም ሥራዎች ስኬታማነት ትልቅ አስተዋዖ ማበርከታቸውን ገልጸው፣ እንደ ሙዚቃ ባለሞያ “ቁንጅና”ን በማስመልከት ልምዱን እና አስተያየቱ እንዲያካፍል በካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር እንዲያደርግ መጋበዙን አስታውሰዋል።
በዜማ ሥራው ላይ የተሰጠ አስተያየት፣
ለፊልም ሥራዎች በቀረቡት የአርቲስት ኤንዮ ሞሪኮኔ የዜማ ድርሰት ላይ አስተያየታቸውን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፣ በፊልም ሥራ ውስጥ የምስል መልዕክት ብቻ ሳይሆን አርቲስት ኤንዮ ሞሪኮኔ ያቀረቧቸው የድምጽ መልዕክቶችም በቀላሉ የሚታወሱ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከምስል መልዕክት ጋር ጎን ለጎን የሚሄደው የዜማ መልዕክት ለአንድ ፊልም ውበትን እንደሚያጎናጽፍ የገለጹት ካርዲናል ራቫዚ፣ “The Mission” በተሰኘ ፊልም ላይ የሚደመጥ የዜማ ድርሰት መንፈሳዊ እሴቶች የሚገኙበት በመሆኑ ለፊልሙ ተወዳጅነት ትልቅ አስተዋጽዖን ያበረከተ መሆኑን አስረድተዋል። ስለዚህ ለእውቁ የዜማ ደራሲ ኤንዮ ሞሪኮኔ ታዋቂ ሥራዎቹ አማንያን እና አማንያን ያልሆኑት በሙሉ ምስጋናቸውን ማቅረብ ይገባል ብለው፣ በተለይም ክርስቲያን ምዕመናን ለመንፈሳዊ ሥራዎቹ ኤንዮ ሞሪኮኔን ማመስገን እንደሚገባ በቅድስት መንበር የባሕል ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት፣ ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ ተናግረዋል።