የተፈጥሮ ውበት ከጸሐይ መጠለቅ ጋር፤   የተፈጥሮ ውበት ከጸሐይ መጠለቅ ጋር፤  

ፍጥረታትን መንከባብከብ እና ከጥፋት መታደግ የጋራ ሃላፊነት መሆኑ ተነገረ።

ካቶሊካዊ ምዕመናን እና መላው ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ ከፍጥረታት ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር ከጥፋት እንዲከላከሉ እና አስፈላጊውን እንከብካቤ እንዲሰጡ በማለት በቅድስት መንበር ውስጥ የሚገኙ የልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች መልዕክታቸውን አድርገዋል። ጳጳሳዊ ምክር ቤቶቹ ይህን መልዕክት፣ “የጋራ መኖሪያችንን ከጥፋት ለመጠበቅ የሚደረግ ጥረት” በሚል ርዕስ ሰኔ 11/2012 ዓ. ም. ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል። የጳጳሳዊ ምክር ቤቶች አባላት መልዕክታቸውን ይፋ ያደረጉት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ግንቦት 24/2015 ዓ. ም. ይፋ ያደረጉትን፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን አምስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል።

የቫቲካን ዜና፤

በቅድስት መንበር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ምክር ቤቶች በጋራ ሆነው ይፋ ያደረጉትን መልዕክት በጋራ የተመለከቱት ከምክር ቤቶቹ የተወጣጡ አባላት መሆናቸው ታውቋል። በተጨማሪም በስነ ምሕዳር ጥበቃ እና እንክብካቤ ተግባር ላይ የተሰማሩ፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካዮች መሆናቸው ታውቋል። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት አስቀድሞ የታየው የጳጳሳዊ ምክር ቤቶች መልዕክት፣ በዋናነት መሠረቱን “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ ማድረጉ ታውቋል።

በሥነ-ምህዳር ለውጥ ትምህርት መስጠት፣

በሥነ-ምህዳር ለውጥ ላይ ትምህርት እንዲሰጥ የሚያሳስበው የምክር ቤቶቹ መልዕክት በመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ለሕይወት ጥበቃ እና እንክብካቤ የመስጠት አስፈላጊነት የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል። ምክር ቤቶቹ በማከልም በምድራችን ወይም በዓለማችን ውስጥ እየተከሰተ ያለው ችግር ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው መሆኑንም አስታውቀው፣ የሰው ልጅ ለፍጥረታ ያለውን ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ፣ በአስተንትኖ እና በጸሎት በመታገዝ፣ የግል እና የጋራ ውይይቶችን በማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በቤተሰብ ደረጃ ግንዛቤን ማስጨበጥ፣

ለሰብዕዊ ሕይወት ትልቅ ሥፍራን የሰጠው የምክር ቤቶቹ መልዕክት፣ በቅድሚያ ለሰብዓዊ ፍጥረት አስፈላጊውን ክብር እና ጥበቃ ሳይሰጥ የተቀረውን ፍጥረት ከጥፋት መከላከል አይቻልም ብሎ፣ ገና በጽንስ ደረጃ ላይ ከሚገኝ የሰው ነፍስ ጀምሮ አካላዊ ጉዳት ለሚታይበት የሰው ልጅ በሙሉ ክብር እና እንክብካቤ ሊሰጥ የሚገባ መሆኑን አስታውቀዋል። በመሆኑም ጳጳሳዊ ምክር ቤቶቹ በመልዕክታቸው የሰውን ልጅ ሕይወት ታላቅነት በቤተሰብ ደረጃ ሳይቀር ግንዛቤ ማስጨበጥ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።                 

ትምህርት ተቋማትን ማዕከል ማድረግ።

ትምህርት ቤቶች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በስነ-ምሕዳር ጥበቃ እና እንክብካቤ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳሰበው የጳጳሳቱ ምክር ቤት፣ ተማሪዎች የጋራ መኖሪያ የሆነች ምድራችንን በመንከባከብ እና ከጥፋት በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል ብሏል። መኖሪያ ቤቶችን፣ የትምህርት ተቋማትን እና ቁምስናዎችን በማገናኘት በስነ-ምህዳር ጥበቃ ተግባር አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይችላል ያለው የምክር ቤቱ መልዕክት፣ በወጣቶች መካከል አዲስ ግንኙነትን በመፍጠር ፍጥረታትን በሙሉ እንዲንከባከቡ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቋል።  

20 June 2020, 19:03