ብጹዕ ካርዲናል ታግለ “በዚህ አስጨናቂ ጊዜ አስቸኳይ በጎ ተግባሮችን ማበርከት ያስፈልጋል”።

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልል፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት በሕዝቦች መካከል መተጋገዝ እና መተሳሰብ እንዲኖር አሳስበው፣ ካጋጠመን ስጋት እና ፍርሃት መውጣት የምንችለው “በፍቅር ወረርሽኝ” ስንያዝ ነው ብለዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመላው ዓለም ለሚገኙ ወንድሞች እና እህቶች ባቀረቡት መልዕክት፣ ተላላፊውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመግታት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በችግር ውስጥ ለሚገኝ ሁሉ አስቸኳይ ዕርዳታን ማቅረብ አዲስ እንዳልሆነ አስረድተው፣ እንደሚታወቀው በየዓመቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ፣ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ፣ ጎርፍ ፣ ድርቅ እና በሽታ ያጋጥሙ መሆኑን አስታውሰዋል። እነዚህ አደጋዎች በአንዳንድ የተውሰኑ አካባቢዎች የሚከሰቱ እና የተወሰኑ ሰዎችን የሚጎዱ መሆኑን ተናግረው፣ አሁን የታየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግን “ፓንደሚያ” ከሚለው ሁለት የግሪክ ቃል የተወሰደ መሆኑን አስረድተው፣ “ፓን” ማለት ሁሉን፣ ዴሞ ማለት ደግሞ ሕዝብ የሚለውን ትርጉም ያሰማል ብለዋል። በመሆኑም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሁሉን የዓለማችን ሕዝብን እና እያንዳንዳችንን የሚያጠቃ በመሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከል ወይም ለመቋቋም አስቸኳይ ዓለም አቀፍ እና የግል ጥረትን ይጠይቃል ብለዋል።

ወረርሽኙ ሕይወትን ማጥቃት ሲጀምር በመጀመሪያ የግል ሕይወትን ቀጥሎም ስለ ቤተሰባችን ሕይወት ቀጥሎ በቅርብ ስለምናውቃቸው ሰዎች መጨነቅ ተፈጥሯዊ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ፣ የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ብለን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል። ይህ መልካም ተግባር ነው ያሉት ካርዲናል ታግለ የሌሎችን ስቃይ አንደራሳችን አድርገን መቁጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በማከልም ምናልባት በጣም በምንጨነቅበት ጊዜ ለሌሎች ማሰብን አቁመን ለራሳችን  ብቻ ማሰብ እንጀምር ይሆናል ብለው አሁን በምንገኝበት አስጨናቂ ጊዜ አደጋው ሁላችንንም የሚያጠቃ በመሆኑ አንዱ ለሌላው ፍቅርን እና ርህራሄን በተግባር መግለጽ ያስፈልጋል ብለዋል። በድንገት የተከሰተ አደጋ በመሆኑ መዋጋትም የምንችለው ተመጣጣኝ የሆነ ድንገተኛ ተስፋን በመሰነቅ ነው ብለዋል። ይህ ድንገተኛ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ በሰዎች መካከል ድንገተኛ በጎ ተግባራትን መውለድ ያስፈልጋል ብለው፣ በዚህ ትውልድ መካከል የሚታይ የፍቅር ተግባርን ወደ ፊት ታሪክ ይመሰክረዋል ብለዋል። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በበጎ አድራጊዎች በኩል ለታየው የነፍስ አድን ተግባራት ካርዲናሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጤና ባለሞያዎች በኮሮና ቫይረስ ላለመያዝ ከፈለግን እጆቻችንን እንድንታጠብ እና ንጽሕናችንን እንድንጠብቅ ያዙናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ በቀረበ ጊዜ ጴንጤናዊው ጲላጦስም ውሃን በመውሰድ እጁን ከታጠበ በኋላ “እናንተ ውሰዱት፣ እኔ  በዚህ ሰው ደም ተጠያቂ አይደለሁም” በማለት ራሱን ነጻ አደረገ። ማቴ. 27:24. እጆቻችንን መታጠብ አስፈላጊ ነው፣ ነገር ግን ጲላጦስ እንዳደርገው መሆን የለበትም። ረዳት የሌላቸው ድሆችን እያየን አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋዊያንን እያየን፣ ከሥራ ገበታቸው የተነሱትን እያየን፣ ስደተኞችን እና መጠለያ አጥተው ውጭ የሚያድሩትን እያየን፣ የሌሎችን ሕይወት ለማዳን የራሳቸውን ሕይወት የሚሰው የጢታ ባለሞያዎችን እያየን፣ በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ተፈጥሮን፣ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ እያየን ሃላፊነት የልብንም ማለት አንችልም። ከመንፈስ ቅዱስ በምናገኘው ኃይል በመታገዝ በፍቅር የተሞላ አስቸኳይ እርዳታችን ለማቅረብ የምንችልበትን ጸጋ በጸሎት እንጠይቅ በማለት በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ እና ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ በጎ አድራጎት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ አንቶኒዮ ታግለ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 March 2020, 16:32