ብጹዕ ካርዲናል ሚገል ኣዩሶ፣ ለተ. መ. ድ. የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ሲያቀርቡ-በስተቀኝ በኩል፣ ብጹዕ ካርዲናል ሚገል ኣዩሶ፣ ለተ. መ. ድ. የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰነድ ሲያቀርቡ-በስተቀኝ በኩል፣  

ካርዲናል አዩሶ “ሰላም የሚመጣው የፍጥረትን ትክክለኛ ትርጉም ስንረዳ ነው”።

በቅድስት መንበር የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ ትናንት ጥር 19 ቀን 2012 ዓ. ም. በጀኔቭ ከተማ በተካሄደ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ በጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን በሰላም እና በተድላ የምንኖርበት አዲስ ጎዳና እንዳለ ማወቅ የምንችለው የፈጣሪዋን ቸርነት እና እውነተኛ ሰላምን የሚሰጥ ዘለዓለማዊ ጥበብን ስናገኝ ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ ትናንት ከሰዓት በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰላም በጋራ ውይይቶች፣ በእርቅ እና ለሰው ልጆች ተስማሚ በሆኑ የሥነ ምሕዳር ለውጦች የሚመጣ የተስፋ ጉዞ ነው በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን የሰላም መልዕክት አስታውሰው፣ ይህን የተስፋ ጉዞ የሰው ልጅ በሙሉ በልቡ በመያዝ ተግባራዊ ለማድረግ ምኞት ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፣ ትናንት በጀኔቭ ከተማ በሚገኘው በቅዱስ ኒኮላስ ደ ፍለ ቤተክርስቲያን በተዘጋጀው የሐይማኖት ተቋማት ስብሰባ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ከሌሎችም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተወጣጡ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ከጀኔቭ እና በሀገሪቱ ከሚገኙ ሌሎች ሀገረ ስብከቶች የመጡ ተወካዮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ ንግግራቸውን አሰምተዋል። የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት የተገኙበትን ስብሰባ በጸሎት እንዲከፍቱ በማለት ለተሰጣቸው ዕድል ጉባኤውን አመስግነው፣ ለክርስቲያኖች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ብለን የምናደረገው ሰላም ለሰው ልጅ መሠረታዊ መብት ክብርን ለመስጠት የሚያስችል ቀዳሚ መሣሪያ ነው ብለዋል።    

በጋራ መኖሪያ ምድራችን በሕብረት መኖር፣

የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ማስተባበሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ በመልዕክታቸው እንዳስታወሱት፣ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አራተኛ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ቅዱስ ቀለሜንጦስ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው ፣ የማይጠቅሙንን አስተሳሰቦች ከአእምሮአችን አውጥተን፣ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን ባህላችንን በመከተል እና የዓለም ፈጣሪ የሆነውን እግዚአብሔር መመልከት ያስፈልጋል ያሉትን አስታውሰው፣ እግዚአብሔር በሰጠን ታላቅ ስጦታ በመመራት ከሰላም የሚገኘውን ሃብት በጋራ መካፈል ያስፈልጋል ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፣ በጋራ መኖሪያ በሆነች ምድራችን በሰላም እና በደስታ የምንኖርበት አዲስ ጎዳና መኖሩን ለማወቅ ተጠርተናል ብለው፣ በዚህ ጎዳና መራመድ የምንችለው የፍጥረትን ትርጉም በሚገባ ስንረዳ እና እውነተኛ ሰላምን የሚሰጥ ዘለዓለማዊ ጥበብን ስናገኝ ነው ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
29 January 2020, 17:56